ዘዳግም 9
9
የሕዝቡ አለመታዘዝ
1እስራኤል ሆይ፤ ስማ፤ ሰማይ ጠቀስ ቅጥር ያላቸው ታላላቅ ከተሞች ያሏቸውን፣ ከአንተ ይልቅ ታላቅና ብርቱ የሆኑትን አሕዛብ አስለቅቀህ ለመግባት ዮርዳኖስን አሁን ትሻገራለህ። 2ዔናቃውያን ብርቱና ቁመተ ረዣዥም ሕዝቦች ናቸው፤ ስለ እነርሱ ታውቃለህ፤ “ዔናቃውያንን ማን ሊቋቋማቸው ይችላል?” ሲባልም ሰምተሃል። 3ይሁን እንጂ እንደሚባላ እሳት ከፊትህ ቀድሞ የሚሻገረው አምላክህ እግዚአብሔር መሆኑን ዛሬ ርግጠኛ ሁን፤ እነርሱን ያጠፋቸዋል፤ በፊትህም ድል ያደርጋቸዋል፤ አንተም እግዚአብሔር በሰጠህ ተስፋ መሠረት ታስወጣቸዋለህ፤ በፍጥነትም ትደመስሳቸዋለህ።
4አምላክህ እግዚአብሔር እነርሱን ከፊትህ ካስወጣቸው በኋላ በልብህ፣ “ይህችን ምድር እንድወርስ እግዚአብሔር ወደዚህ ያመጣኝ፣ ከጽድቄ የተነሣ ነው” አትበል። በዚህ አይደለም፤ እነዚህን አሕዛብ እግዚአብሔር ከፊትህ የሚያሳድዳቸው በክፋታቸው ምክንያት ነው። 5ምድራቸውን ገብተህ የምትወርሳት ከጽድቅህ ወይም ከልብህ ቅንነት የተነሣ ሳይሆን፣ ለአባቶችህ ለአብርሃም፣ ለይሥሐቅና ለያዕቆብ የማለላቸውን ቃል ለመፈጸም አምላክህ እግዚአብሔር እነዚህን አሕዛብ ከክፋታቸው የተነሣ ከፊትህ ስለሚያባርራቸው ነው። 6ስለዚህ አምላክህ እግዚአብሔር ይህችን መልካም ምድር እንድትወርሳት የሚሰጥህ ከጽድቅህ የተነሣ አለመሆኑን አስተውል፤ አንተ ዐንገተ ደንዳና ነህና።
የወርቁ ጥጃ
7አምላክህን እግዚአብሔርን በምድረ በዳ እንዴት እንዳስቈጣኸው አስታውስ፤ ከቶም አትርሳ። ከግብጽ ከወጣህበት ዕለት አንሥቶ እዚህ ቦታ እስከ ደረስህበት ጊዜ በእግዚአብሔር ላይ እንዳመፅህ ነህ። 8በኮሬብ እግዚአብሔርን ለቍጣ አነሣሣችሁት፤ እርሱም እናንተን ሊያጠፋችሁ እጅግ ተቈጣ። 9እኔም የድንጋይ ጽላቱን፣ እግዚአብሔር ከእናንተ ጋራ የገባውን የኪዳን ጽላት ለመቀበል ወደ ተራራው በወጣሁ ጊዜ፣ እህል ሳልበላ፣ ውሃም ሳልጠጣ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ቈየሁ፤ 10በእግዚአብሔር ጣት የተጻፈባቸውን ሁለት የድንጋይ ጽላት እግዚአብሔር ሰጠኝ፤ በተሰበሰባችሁበት ዕለት እግዚአብሔር ከተራራው ላይ በእሳት ውስጥ ሆኖ ለእናንተ የነገራችሁ ትእዛዞች ሁሉ በእነርሱ ላይ ነበሩባቸው።
11አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ከተፈጸመ በኋላ፣ እግዚአብሔር ሁለቱን የድንጋይ ጽላት ማለትም የኪዳኑን ጽላት ሰጠኝ። 12ከዚያም እግዚአብሔር፣ “ተነሣ፤ ከግብጽ ያወጣሃቸው ሕዝብህ ረክሰዋልና ፈጥነህ ከዚህ ውረድ፤ እኔ ካዘዝኋቸው ፈጥነው ፈቀቅ ብለዋል፤ ቀልጦ የተሠራ ጣዖትም ለራሳቸው አበጅተዋል” ብሎ ነገረኝ።
13ደግሞም እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፤ “ይህን ሕዝብ አይቼዋለሁ፤ በርግጥ ዐንገተ ደንዳና ሕዝብ ነው፣ 14አጠፋቸውና ስማቸውንም ከሰማይ በታች እደመስሰው ዘንድ ተወኝ፤ አንተንም ከእነርሱ ይልቅ ብርቱና ብዙ ሕዝብ አደርግሃለሁ።”
15ስለዚህ ተራራው በእሳት እየተቀጣጠለ ሳለ፣ ሁለቱን የቃል ኪዳን ጽላት በሁለቱም እጆቼ እንደ ያዝሁ#9፥15 ወይም፣ ሁለቱም የቃል ኪዳን ጽላት ከእኔ ጋራ ነበሩ፤ አንዱም በአንዱ፣ ሌላውም በሌላው እጄ ነበር ተብሎ መተርጐም ይችላል። ከተራራው ተመልሼ ወረድሁ። 16በርግጥ በአምላካችሁ በእግዚአብሔር ላይ ኀጢአት ሠርታችሁ እንደ ነበር ተመለከትሁ፤ ቀልጦ የተሠራ የጥጃ ምስልም ለራሳችሁ አበጃችሁ፤ እግዚአብሔር እናንተን ካዘዛችሁ መንገድ በፍጥነት ወጥታችሁ ነበር። 17ስለዚህ ሁለቱን ጽላት ወስጄ ከእጆቼ አሽቀንጥሬ በፊታችሁ ሰባበርኋቸው።
18ከዚያም በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነገርን በመፈጸም ለቍጣ እንዲነሣሣ የሚያደርገውን ኀጢአት ሁሉ ስለ ሠራችሁ፣ እህል ውሃ ሳልቀምስ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት እንደ ገና በእግዚአብሔር ፊት በግንባሬ ተደፋሁ። 19እናንተን ሊያጠፋችሁ ክፉኛ ተቈጥቶ ነበርና፣ እኔም የእግዚአብሔርን ቍጣና መዓት ፈራሁ፤ እግዚአብሔር ግን እንደ ገና ሰማኝ። 20እግዚአብሔር አሮንን ሊያጠፋው ክፉኛ ተቈጥቶ ነበር፤ በዚያ ጊዜ ለአሮንም ጸለይሁ። 21ደግሞም ያን የኀጢአት ሥራችሁን፣ ያበጃችሁትን ጥጃ ወስጄ በእሳት አቃጠልሁት፤ ከዚያም ሰባብሬ እንደ ትቢያ ዱቄት እስኪሆን ድረስ ፈጭቼ ከተራራው በሚወርደው ጅረት ውስጥ በተንሁት።
22በተቤራም፣ በማሳህና በቂብሮት ሃታአባ እግዚአብሔርን አስቈጣችሁት።
23 እግዚአብሔር ከቃዴስ በርኔ ባስወጣችሁ ጊዜ፣ “ውጡ፤ የሰጠኋችሁንም ምድር ርስት አድርጋችሁ ውረሷት” አላችሁ። እናንተ ግን በአምላካችሁ በእግዚአብሔር ትእዛዝ ላይ ዐመፃችሁ፤ እርሱን አልታመናችሁበትም፤ አልታዘዛችሁትምም። 24እኔ እናንተን ካወቅኋችሁ ጊዜ ጀምሮ፣ በእግዚአብሔር ላይ እንዳመፃችሁ ናችሁ።
25 እግዚአብሔር እናንተን እንደሚያጠፋችሁ ተናግሮ ስለ ነበር፣ በእነዚያ አርባ ቀናትና አርባ ሌሊቶች በእግዚአብሔር ፊት በግንባሬ ተደፋሁ፤ 26እንዲህም በማለት ወደ እግዚአብሔር ጸለይሁ፤ “ጌታ እግዚአብሔር ሆይ በታላቅ ኀይልህ የተቤዠኸውንና በኀያል ክንድህ ከግብጽ ያወጣኸውን፣ ያንተ ርስት የሆነውን ሕዝብህን አታጥፋ። 27ባሪያዎችህን አብርሃምን፣ ይሥሐቅንና ያዕቆብን ዐስብ፤ የዚህን ሕዝብ ልበ ደንዳናነት፣ ክፋትና ኀጢአት አትመልከት። 28አለዚያ እኛን ካመጣህበት ምድር ያሉ ሰዎች ‘እግዚአብሔር ተስፋ ወደ ሰጣቸው ምድር ሊያገባቸው ስላልቻለና ስለ ጠላቸው፣ በምድረ በዳ ሊገድላቸው አወጣቸው’ ይላሉ። 29ነገር ግን እነርሱ በታላቅ ኀይልህና በተዘረጋች ክንድህ ያወጣሃቸው ሕዝብህና ርስትህ ናቸው።”
Currently Selected:
ዘዳግም 9: NASV
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.