የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ዘፀአት 10

10
የአንበጣ መንጋ መቅሠፍት
1ከዚያም እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ “ተመልሰህ ወደ ፈርዖን ሂድ፤ እነዚህን ታምራዊ ምልክቶች በመካከላቸው ለማድረግ የፈርዖንንና የሹማምቱን ልብ አደንድኛለሁና፤ 2ይኸውም ግብጻውያንን እንዴት አድርጌ እንደ ቀጣኋቸውና በመካከላቸውም ምልክቶቼን እንዴት እንዳደረግሁ ለልጆቻችሁና ለልጅ ልጆቻችሁ እንድትነግሩና እኔ እግዚአብሔር መሆኔንም እንድታውቁ ነው።”
3ሙሴና አሮን ወደ ፈርዖን ሄደው እንዲህ አሉት፤ “የዕብራውያን አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ራስህን በፊቴ ለማዋረድ እስከ መቼ እንቢ ትላለህ? ሕዝቤ ያመልኩኝ ዘንድ ልቀቃቸው። 4እንዳይሄዱ ብትከለክላቸው ነገ በአገርህ ላይ አንበጣዎችን አመጣለሁ። 5አንበጣዎቹም ምድሪቱ እስከማትታይ ድረስ ይሸፍኗታል፤ በመስክህ ላይ እያቈጠቈጠ ያለውን ዛፍ ሁሉ ሳይቀር ከበረዶ የተረፈውንም ጥቂቱን ሁሉ ይበሉታል። 6የአንተን፣ የሹማምትህንና የግብጻውያንን ቤቶች ሁሉ ይሞሏቸዋል፤ ይህም አባቶችህም ሆኑ ቅድመ አያቶችህ በዚህች ምድር ከሰፈሩበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ድረስ ከቶ አይተውት የማያውቁት ነው።’ ” ሙሴም ተመለሰና ከፈርዖን ተለይቶ ሄደ።
7የፈርዖንም ሹማምት፣ “ይህ ሰው እስከ መቼ ወጥመድ ይሆንብናል? አምላካቸውን እግዚአብሔርን እንዲያመልኩ ሰዎቹን ልቀቃቸውና ይሂዱ። ግብጽ መጥፋቷን እስካሁን አልተገነዘብህምን?” አሉት።
8ከዚያም ሙሴና አሮን ወደ ፈርዖን እንዲመጡ ተደረገ፤ “ሂዱ አምላካችሁን እግዚአብሔርን አምልኩ፤ ነገር ግን መሄድ የሚገባቸው የትኞቹ ናቸው?” አለ።
9ሙሴም፣ “ለእግዚአብሔር በዓል ልናከብር ስለ ሆነ ወጣቶቻችንንና ሽማግሌዎቻችንን፣ ወንድና ሴት ልጆቻችንን፣ የበግና የፍየል መንጋዎቻችንን እንዲሁም የቀንድ ከብቶቻችንን ይዘን እንሄዳለን” አለ።
10ፈርዖንም እንዲህ አለ፤ “ከሴቶቻችሁና ከልጆቻችሁ ጋራ እንድትሄዱ እለቅቃችኋለሁ፤ እግዚአብሔር ከእናንተ ጋራ ይሁን፤ ነገር ግን ተንኰል ዐስባችኋል።#10፥10 ወይም፣ ተጠንቀቁ፤ ችግር ተዘጋጅቶላችኋል 11አይሆንም፤ ወንዶቹ ብቻ እንዲሄዱና እግዚአብሔርን እንዲያመልኩ አድርጉ፤ የጠየቃችሁት ይህንኑ ነው።” ከዚያም ሙሴና አሮን ከፈርዖን ፊት እንዲወጡ ተደረገ።
12 እግዚአብሔር ሙሴን፣ “የአንበጣ መንጋ ምድሪቱን እንዲወርር ከበረዶ የተረፈውን ሁሉና በማሳም ላይ የበቀለውን ሁሉ ጠርጎ እንዲበላ እጅህን በግብጽ አገር ላይ ዘርጋ” አለው።
13ስለዚህ ሙሴ በግብጽ አገር ላይ በትሩን ዘረጋ፤ እግዚአብሔርም በዚያ ቀንና ሌሊት በሙሉ በምድሪቱ ላይ የምሥራቅ ነፋስ እንዲነፍስ አደረገ፤ በማግስቱም ነፋሱ አንበጣዎችን አመጣ። 14እነርሱም ግብጽን በሙሉ ወረሩ፤ ስፍር ቍጥር የሌላቸው ሆነው የሀገሪቱን ዳር ድንበር ሁሉ አለበሱ። እንዲህ ያለ የአንበጣ መዓት ከዚህ ቀደም አልነበረም፤ ወደ ፊትም ደግሞ አይኖርም። 15ምድሩ ሁሉ ጠቍሮ እስኪጨልም ድረስ አለበሱት። ከበረዶ የተረፈውን፣ በመስክ ላይ የበቀለውንና በዛፍ ላይ ያለውን ፍሬ ሁሉ ጠርገው በሉ። በግብጽ ምድር ሁሉ በዛፍ ላይ ወይም በተክል ላይ አንዳች ቅጠል አልተረፈም ነበር።
16ከዚያም ፈርዖን ሙሴንና አሮንን በፍጥነት አስጠርቶ እንዲህ አላቸው፤ “በአምላካችሁ በእግዚአብሔር በእናንተም ላይ ኀጢአት ሠርቻለሁ፤ 17እንግዲህ አሁን አንድ ጊዜ ደግሞ ኀጢአቴን ይቅር በሉኝና ይህን ቀሣፊ መዓት እንዲያስወግድልኝ አምላካችሁን እግዚአብሔርን ለምኑልኝ።”
18ሙሴም ከፈርዖን ዘንድ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ። 19ከዚያም እግዚአብሔር ነፋሱን ወደ ብርቱ የምዕራብ ነፋስ ለወጠው፤ ያም ነፋስ አንበጣዎቹን እየነዳ ወደ ቀይ ባሕር#10፥19 ዕብራይስጡ “ያም ሱፍ” ይለዋል የሸንበቆ ባሕር ማለት ነው። ከተታቸው፤ በግብጽ ምድር በየትኛውም ቦታ አንድም አንበጣ አልቀረም። 20እግዚአብሔር ግን የፈርዖንን ልብ አደነደነ፤ ፈርዖንም እስራኤላውያን እንዲሄዱ አልፈቀደም።
የጨለማ መቅሠፍት
21ከዚያም እግዚአብሔር ሙሴን፣ “በግብጽ ላይ ድቅድቅ ጨለማ እንዲወርድ እጅህን ወደ ሰማይ ዘርጋ” አለው። 22ሙሴም እጁን ወደ ሰማይ ዘረጋ፤ በመላው ግብጽ ላይ ለሦስት ቀናት ድቅድቅ ያለ ጨለማ ሆነ። 23በእነዚያ ሦስት ቀናት ውስጥ አንዱ ሌላውን ማየት ወይም ከነበረበት ቦታ መንቀሳቀስ አይችልም ነበር። ይሁን እንጂ እስራኤላውያን በሚኖሩበት ስፍራ ሁሉ ብርሃን ነበር።
24ከዚያም ፈርዖን ሙሴን አስጠርቶ፣ “ሄዳችሁ እግዚአብሔርን አምልኩ፤ ሴቶቻችሁና ልጆቻችሁ ሳይቀሩ ዐብረዋችሁ ይሂዱ፤ በጎቻችሁ፣ ፍየሎቻችሁና የጋማ ከብቶቻችሁ ብቻ እዚሁ ይቅሩ” አለው።
25ሙሴም እንዲህ አለው፤ “ለአምላካችን ለእግዚአብሔር መሥዋዕትና የሚቃጠል መሥዋዕት እንድንሠዋ ፍቀድልን፤ 26እንስሶቻችን ሁሉ ዐብረው መሄድ አለባቸው። አንድ ሰኰና እንኳ አይቀርም። ከእንስሶቻችን መካከል ለአምላካችን ለእግዚአብሔር አምልኮ የምናቀርባቸው ይኖራሉ፤ ሆኖም እዚያ ከመድረሳችን በፊት እግዚአብሔርን ለማምለክ የምናቀርባቸው እንስሳት የትኞቹ እንደ ሆኑ አስቀድመን ለይተን ማወቅ አንችልም።”
27ነገር ግን እግዚአብሔር የፈርዖንን ልብ አደነደነ፤ ፈርዖንም ሕዝቡን መልቀቅ አልፈቀደም። 28ፈርዖን ሙሴን፣ “ከፊቴ ጥፋ! ሁለተኛ እኔ ዘንድ እንዳትደርስ! ፊቴን ባየህበት በዚያ ቀን ፈጽመህ እንደምትሞት ዕወቅ” አለው።
29ሙሴም፣ “እንዳልከው ይሁን፤ እኔም ዳግመኛ ከፊትህ አልደርስም” አለው።

Currently Selected:

ዘፀአት 10: NASV

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ