የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ዘፀአት 9

9
የእንስሳት ዕልቂት
1ከዚያም እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ “ወደ ፈርዖን ሂድና እንዲህ በለው፤ ‘የዕብራውያን አምላክ እግዚአብሔር የሚለው ይህ ነው፤ “ያመልኩኝ ዘንድ ሕዝቤን ልቀቅ።” 2አሁንም እንዳይሄዱ ብታደርግና ብትከለክላቸው፣ 3እግዚአብሔር እጅ በመስክ ላይ ባሉት እንስሳት፣ በፈረሶችህና በአህዮችህ፣ በግመሎችህና በቀንድ ከብቶችህ፣ በበጎችህና በፍየሎችህ ላይ አስከፊ መቅሠፍት ያመጣብሃል። 4ነገር ግን እግዚአብሔር በእስራኤልና በግብጽ እንስሳት መካከል ልዩነት ያደርጋል፤ ይኸውም የእስራኤል የሆነ ማንኛውም እንስሳ እንዳይሞት ነው።’ ”
5 እግዚአብሔር ጊዜን ወስኖ፣ እንዲህ አለ፤ “በነገው ዕለት እግዚአብሔር በምድሪቱ ላይ ይህን ያደርጋል።” 6በማግስቱም እግዚአብሔር ነገሩን ፈጸመው፤ የግብጻውያን እንስሳት በሙሉ ዐለቁ፤ ነገር ግን የእስራኤላውያን ከሆኑት እንስሳት አንድም አልሞተም። 7ፈርዖን ያጣሩ ዘንድ ሰዎች ልኮ ከእስራኤላውያኑ እንስሳት አንድም እንኳ አለመሞቱን ተገነዘበ። ያም ሆኖ ልቡ እንደ ደነደነ ስለ ነበር፣ ሕዝቡን አልለቀቀም።
የዕባጭ መቅሠፍት
8ከዚያም እግዚአብሔር ሙሴንና አሮንን አላቸው፤ “ከምድጃው ዕፍኝ ዐመድ ወስዳችሁ፣ ሙሴ በፈርዖን ፊት ወደ ሰማይ ይበትነው። 9በግብጽ ምድር ሁሉ ትቢያ ይሆናል፤ በምድሪቱ ሁሉ በሚገኙት ሰዎችና እንስሳት ላይ መግል የያዘ ዕባጭ ይወጣል።”
10ስለዚህ ከምድጃው ዐመድ ወስደው በፈርዖን ፊት ቆሙ፤ ሙሴም ወደ ሰማይ በተነው፤ መግል የያዘ ዕባጭም በሰዎችና በእንስሳት ላይ ወጣ። 11በእነርሱና በግብጻውያን ሁሉ ላይ ዕባጭ ወጥቶ ስለ ነበር፣ አስማተኞቹ በሙሴ ፊት መቆም አልቻሉም። 12እግዚአብሔር ግን የፈርዖንን ልብ አደነደነ፤ እግዚአብሔር ለሙሴ እንደ ተናገረውም፣ ሙሴንና አሮንን መስማት አልፈለገም።
የበረዶ መቅሠፍት
13ከዚያም እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ “ማልደህ በጧት ተነሣ፤ ከፈርዖን ፊት ቀርበህ እንዲህ በለው፤ የዕብራውያን አምላክ እግዚአብሔር የሚለው ይህ ነው፤ ‘ያመልኩኝ ዘንድ ሕዝቤን ልቀቅ፤ 14አለዚያ በአንተ በሹማምትህና በሕዝብህ ላይ የመቅሠፍቴን መዓት ሁሉ አሁን አወርድብሃለሁ፤ ይኸውም በምድር ሁሉ እንደ እኔ ያለ ማንም እንደሌለ ታውቅ ዘንድ ነው። 15አሁን እጄን ዘርግቼ አንተንና ሕዝብህን ከገጸ ምድር ሊያጠፋችሁ በሚችል መቅሠፍት በመታኋችሁ ነበር። 16ነገር ግን ኀይሌን እንዳሳይህና ስሜም በምድር ሁሉ እንዲታወቅ ለዚህ አስነሣሁህ።#9፥16 ወይም፣ ለዚህ ምሕረቴን አሳይቼሃለሁ 17እስካሁንም በሕዝቤ ላይ እንደ ተነሣህ ነው፤ ይሄዱም ዘንድ አትለቅቃቸውም። 18ስለዚህ ነገ በዚህ ጊዜ ከተመሠረተችበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ድረስ በግብጽ ላይ ወርዶ የማያውቅ አስከፊ የበረዶ ማዕበል እልካለሁ። 19ከብቶችህና በመስክ ላይ ያለህ ማንኛውም ነገር ወደ መጠለያ ይገቡ ዘንድ አሁን ትእዛዝ ስጥ፤ ምክንያቱም በረዶው ወደ መጠለያ ባልገቡትና በመስክ ላይ በቀሩት በማንኛውም ሰውና እንስሳት ላይ ወርዶባቸው ስለሚሞቱ ነው።’ ”
20እግዚአብሔርን ቃል የፈሩት የፈርዖን ሹማምት፣ ባሮቻቸውንና ከብቶቻቸውን ለማስገባት ተጣደፉ። 21እግዚአብሔርን ቃል ችላ ያሉት ግን ባሮቻቸውንና ከብቶቻቸውን በመስክ ላይ እንደ ነበሩ ተዉአቸው።
22ከዚያም እግዚአብሔር ሙሴን፣ “በመላዪቱ የግብጽ ምድር ባሉት ሰዎች፣ በእንስሳት እንዲሁም በምድሪቱ ላይ በሚበቅሉት ነገሮች ሁሉ ላይ በረዶ እንዲወርድ እጅህን ወደ ሰማይ አንሣ” አለው። 23ሙሴ በትሩን ወደ ሰማይ ባነሣ ጊዜ እግዚአብሔር ነጐድጓድና በረዶ አወረደ፤ መብረቅም በምድሪቱ ላይ ሆነ። እግዚአብሔር በግብጽ ምድር በረዶ አዘነበ፤ 24በረዶ ወረደ፤ መብረቅም አብረቀረቀ፤ ግብጽ አገር ከሆነችበት ዘመን አንሥቶ በምድሪቱ ሁሉ እንደዚህ ያለ አስከፊ ማዕበል ሆኖ አያውቅም። 25በመላው ግብጽ በረዶ በመስክ ላይ ያለውን ሁሉ፣ ሰዎችንና እንስሳትንም መታ፤ በመስክ ላይ የበቀለውን ሁሉ አጠፋ፤ ዛፉን ሁሉ ባዶ አስቀረ። 26በረዶ ያልወረደበት ቢኖር እስራኤላውያን የሚኖሩበት የጌሤም ምድር ብቻ ነበር።
27ከዚያም ፈርዖን ሙሴንና አሮንን አስጠራ፤ እንዲህም አላቸው፤ “አሁንስ በድያለሁ፤ እግዚአብሔር ትክክል ነው፤ እኔና ሕዝቤ ግን ስተናል። 28መብረቅና በረዶ በዝቶብናልና ወደ እግዚአብሔር ጸልዩልን፤ እንድትሄዱ እለቃችኋለሁ፤ ከዚህ በኋላ በዚህ የመኖር ግዴታ የለባችሁም።”
29ሙሴም መልሶ፣ “ከከተማዋ በወጣሁ ጊዜ፣ እጆቼን ለጸሎት ወደ እግዚአብሔር እዘረጋለሁ፤ አንተም ምድር የእግዚአብሔር እንደ ሆነች ታውቅ ዘንድ መብረቁ ያቆማል፤ ከእንግዲህ በኋላ በረዶ አይኖርም። 30ሆኖም አንተና ሹማምትህ አሁንም ቢሆን እግዚአብሔር አምላክን እንደማትፈሩ ዐውቃለሁ።”
31ተልባው አብቦ፣ ገብሱም ፍሬ ይዞ ስለ ነበር፣ ተልባውና ገብሱ ከጥቅም ውጭ ሆኑ። 32ስንዴውና አጃው ግን በዚያ ወቅት ባለማፍራቱ አልጠፋም ነበር።
33ከዚያም ሙሴ ከፈርዖን ተለይቶ ከከተማው ወጣ። እጁን ወደ እግዚአብሔር ዘረጋ፤ ነጐድጓዱና በረዶው ቆመ፤ ዝናቡም በምድሪቱ ላይ መዝነቡን አቆመ። 34ፈርዖንም ዝናቡ፣ በረዶውና ነጐድጓዱ መቆሙን ባየ ጊዜ እንደ ገና በደለ፤ እርሱና ሹማምቱ ልባቸውን አደነደኑ። 35ስለዚህ የፈርዖን ልብ ደነደነ፤ እግዚአብሔር ለሙሴ እንደ ተናገረውም እስራኤላውያን ይሄዱ ዘንድ አልለቀቃቸውም።

Currently Selected:

ዘፀአት 9: NASV

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ