የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ዘፀአት 13

13
በኵር ሁሉ ለእግዚአብሔር መቀደሱ
1 እግዚአብሔር ሙሴን አለው፤ 2“መጀመሪያ የተወለደውን ወንድ ሁሉ ለእኔ ቀድስልኝ፤ ከእስራኤላውያን መካከል የእናቱ የበኵር ልጅ የሆነው ማሕፀን ከፋች ሰውም ሆነ እንስሳ የእኔ ነው።”
3ከዚያም ሙሴ ሕዝቡን እንዲህ አለ፤ “ከባርነት ምድር ከግብጽ የወጣችሁባትን ይህችን ዕለት አስታውሱ፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር በኀያል ክንዱ አውጥቷችኋል። እርሾ ያለበትን ማንኛውንም ነገር አትብሉ። 4እነሆ በዚች ዕለት በአቢብ ወር ወጥታችኋል። 5እግዚአብሔር ለእናንተ ለመስጠት ሲል ቀድሞ ለአባቶቻችሁ ወደ ማለላቸው ማርና ወተት ወደምታፈስሰው ወደ ከነዓናውያን፣ ኬጢያውያን፣ አሞራውያን፣ ኤዊያውያን፣ ኢያቡሳውያን ምድር በምትገቡበት ጊዜ ይህን በዓል በዚህ ወር ታከብራላችሁ። 6ለሰባት ቀን ያለ እርሾ የተጋገረ ቂጣ ትበላላችሁ፤ በሰባተኛውም ቀን ለእግዚአብሔር በዓል ታደርጋላችሁ። 7በእነዚህም ሦስት ቀናት ቂጣ ትበላላችሁ፤ በእናንተ ዘንድ እርሾ ያለበት ነገር ፈጽሞ አይገኝ፤ በምድራችሁም አዋሳኝ በየትኛውም ቦታ እርሾ ፈጽሞ አይኑር። 8በዚያችም ዕለት፣ ‘እኔ ይህን የማደርገው ከግብጽ ምድር በወጣሁበት ጊዜ እግዚአብሔር ስላደረገልኝ ነገር ነው’ ብለህ ለልጅህ ንገረው። 9እግዚአብሔር ሕግ በከንፈራችሁ ላይ እንዲሆን ይህ በዓል ለእናንተ በእጃችሁ ላይ እንደ ታሰረ ምልክት፣ በእግራችሁ ላይ እንደሚገኝ መታሰቢያ ይሆንላችኋል። እግዚአብሔር በኀያል ክንዱ ከግብጽ አውጥቷችኋልና። 10ይህን ሥርዐት በተወሰነው ጊዜ በየዓመቱ ጠብቁት።
11እግዚአብሔር ለእናንተና ለቀደሙት አባቶቻችሁ በመሐላ በሰጠው ተስፋ መሠረት ወደ ከነዓናውያን አገር በሚያስገባችሁና ምድሪቱንም ለእናንተ በሚሰጣችሁ ጊዜ፣ 12የእናቱን ማሕፀን የሚከፍተውን ሁሉ ለእግዚአብሔር ትሰጣላችሁ፤ እንደዚሁም እንስሶቻችሁ በመጀመሪያ የወለዷቸው ወንዶች ሁሉ ለእግዚአብሔር ይሆናሉ። 13ከአህያ በመጀመሪያ የተወለደውን ውርንጫ ግን በጠቦት ትዋጁታላችሁ፤ አህያውን ካልዋጃችሁት ግን ዐንገቱን ስበሩት። ከወንድ ልጆቻችሁ መካከል በኵር የሆኑትን ሁሉ ዋጁ።
14“በሚመጡት ዘመናት ልጅህ፣ ‘ይህ ምን ማለት ነው?’ ብሎ ቢጠይቅህ እንዲህ በለው፤ ‘ከባርነት ምድር ከግብጽ እግዚአብሔር በኀያል ክንዱ አወጣን፤ 15ፈርዖን እኛን አልለቅም ብሎ ልቡን ባደነደነ ጊዜ ከሰው ጀምሮ እስከ እንስሳ ድረስ በኵር ሆኖ በግብጽ የተወለደውን ሁሉ እግዚአብሔር ገደለው። እንግዲህ በመጀመሪያ የእናቱን ማሕፀን የከፈተውን ወንድ ሁሉ ለእግዚአብሔር የምሠዋውና የልጆቼ በኵር ሆኖ የተወለደውን ወንድ ልጅ ሁሉ የምዋጀው በዚህ ምክንያት ነው።’ 16እግዚአብሔር በኀያል ክንዱ እኛን ከግብጽ ያወጣን ስለ ሆነ ይህ ሥርዐት በእጅህም ሆነ በግንባርህ ላይ እንደ ምልክት ይሆናል።”
ቀይ ባሕርን መሻገር
17ፈርዖን ሕዝቡን በለቀቀ ጊዜ አቋራጭ ቢሆንም እንኳ እግዚአብሔር በፍልስጥኤም ምድር በሚያልፈው መንገድ አልመራቸውም፤ “ጦርነት ቢያጋጥማቸው ሐሳባቸውን ለውጠው ወደ ግብጽ ይመለሱ ይሆናል” ብሏልና። 18ስለዚህ እግዚአብሔር ሕዝቡን ዙሪያ በሆነው በምድረ በዳው መንገድ ወደ ቀይ ባሕር#13፥18 በዕብራይስጡ ያም ሱፍ ይላል፤ ትርጕሙም የሸንበቆ ባሕር ማለት ነው። መራቸው፤ እስራኤላውያንም ለጦርነት ዝግጁ ሆነው ከግብጽ ወጡ።
19ዮሴፍ፣ “እግዚአብሔር በርግጥ ይጐበኛችኋል፤ በዚያ ጊዜም ዐፅሜን ይዛችሁ ከዚች ምድር መውጣት አለባችሁ”#13፥19 ዘፍ 50፥25 ይመ ብሎ የእስራኤልን ልጆች አስምሏቸው ስለ ነበር ሙሴ የዮሴፍን ዐፅም ይዞ ወጣ። እግዚአብሔር ሕዝቡን ዙሪያ በሆነው በምድረ በዳው መንገድ ወደ ቀይ ባሕር መራቸው፤ እስራኤላውያንም ለጦርነት ዝግጁ ሆነው ከግብጽ ወጡ።
20እነርሱም ከሱኮት ከተነሡ በኋላ ከምድረ በዳው ጥግ ባለው በኤታም ሰፈሩ። 21ስለዚህ በቀንም ሆነ በሌሊት መጓዝ ይችሉ ዘንድ፣ እግዚአብሔር በቀን በመንገዳቸው ሊመራቸው በደመና ዓምድ፣ በሌሊት ደግሞ ብርሃን ሊሰጣቸው በእሳት ዐምድ በፊታቸው ይሄድ ነበር። 22በቀንም ሆነ በሌሊት የደመናውና የእሳቱ ዐምድ ከሕዝቡ ፊት የተለየበት ጊዜ አልነበረም።

Currently Selected:

ዘፀአት 13: NASV

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ