ዘፀአት 14
14
1ከዚያም እግዚአብሔር ሙሴን አለው፤ 2“እስራኤላውያን ተመልሰው በሚግዶልና በባሕሩ መካከል ባለው በፊሀሒሮት አጠገብ እንዲሰፍሩ ንገራቸው፤ በበኣልዛፎንም አንጻር በባሕሩ አጠገብ ይስፈሩ። 3‘ፈርዖን እስራኤላውያን ግራ ተጋብተው በምድረ በዳ በመቅበዝበዝ ይንከራተታሉ’ ብሎ ያስባል። 4እኔም የፈርዖንን ልብ ስለማደነድነው ያሳድዳቸዋል፤ ነገር ግን በፈርዖንና በሰራዊቱ ሁሉ ለራሴ ክብርን አገኛለሁ፤ ግብጻውያንም እኔ እግዚአብሔር መሆኔን ያውቃሉ።” እስራኤላውያንም ይህንኑ አደረጉ።
5የግብጽ ንጉሥ ሕዝቡ መሄዳቸው በተነገረው ጊዜ፣ ፈርዖንና ሹማምቱ ስለ እነርሱ የነበራቸውን ሐሳብ በመለወጥ፣ “ምን ማድረጋችን ነው? እስራኤላውያን እንዲሄዱ ለቀቅናቸው፤ አገልግሎታቸውንም ዐጣን” አሉ። 6ስለዚህ ሠረገላው እንዲዘጋጅለት አደረገ፤ ሰራዊቱንም ይዞ ተንቀሳቀሰ። 7ስድስት መቶ ምርጥ ሠረገላዎችን ከሌሎች የግብጽ ሠረገላዎች ጋራ ከነጦር አዛዦቻቸው አሰልፎ ተነሣ። 8እግዚአብሔር የንጉሡን የፈርዖንን ልብ ስለ አደነደነው በልበ ሙሉነት ከግብጽ የሚወጡትን እስራኤላውያን አሳደዳቸው። 9ግብጻውያን፣ ይኸውም የፈርዖን ፈረሶችና ሠረገላዎች፣#14፥9 በዚህ ስፍራና ሠረገለኞች በ17፣ 18፣ 23፣ 26 እንዲሁም በ28 ፈረሰኞችና እግረኞች ሁሉ እስራኤላውያንን አሳደዷቸው፤ በበኣልዛፎን አንጻር በባሕሩ አጠገብ በፊሀሒሮት ሰፍረው ሳሉ ደረሱባቸው።
10ፈርዖን በቀረበ ጊዜ እስራኤላውያን ቀና ብለው ተመለከቱ፤ እነሆ፣ ግብጻውያን ይከታተሏቸው ነበር፤ እነርሱም በታላቅ ፍርሀት ወደ እግዚአብሔር ጮኹ። 11እነርሱም ሙሴን እንዲህ አሉት፤ “በምድረ በዳ እንድንሞት ያመጣኸን በግብጽ መቃብር ቦታ ጠፍቶ ነውን? ከግብጽ አውጥተህ ምን አደረግህልን? 12በግብጽ ሳለን፣ ‘ተወን እባክህ፤ ግብጻውያንን እናገልግል’ አላልንህም ነበርን? በምድረ በዳ ከምንሞት ግብጻውያንን ብናገለግል ይሻል ነበር!”
13ሙሴም ለሕዝቡ መለሰላቸው፤ “አትሸበሩ፣ ጸንታችሁ ቁሙ፤ እግዚአብሔር ዛሬ የሚያደርግላችሁን መታደግ ታያላችሁ፤ ዛሬ የምታዩአቸውን ግብጻውያንን ዳግም አታዩአቸውም። 14እግዚአብሔር ስለ እናንተ ይዋጋል፤ እናንተ ያለባችሁ መታገሥ ብቻ ነው።”
15ከዚያም እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ “ለምን ትጮኹብኛላችሁ? ይልቅስ እስራኤላውያንን ወደ ፊት እንዲጓዙ ንገራቸው፤ 16ውሃውን ለመክፈል በትርህን አንሣና እጅህን በባሕሩ ላይ ዘርጋ፤ እስራኤላውያን በባሕሩ ውስጥ በየብስ ይሻገራሉ። 17ተከትለዋቸው እንዲገቡም የግብጻውያንን ልብ አጸናለሁ፤ በፈርዖንና በሰራዊቱ ሁሉ፣ በሠረገሎቹና በፈረሰኞቹ ለራሴ ክብርን አገኛለሁ። 18በፈርዖንና በሰራዊቱ ሁሉ በከበርሁ ጊዜ፣ ግብጻውያን እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።”
19ከዚያም ከእስራኤል ሰራዊት ፊት ፊት ሆኖ ሲሄድ የነበረው የእግዚአብሔር መልአክ ተመለሰና ወደ ኋላቸው መጣ፤ የደመናውም ዐምድ እንዲሁ ከፊት ተነሥቶ ከኋላቸው ቆመ፤ 20በግብጽና በእስራኤል ሰራዊት መካከል በመሆን፣ ሌሊቱን ሙሉ ደመናው በአንድ በኩል ጨለማን ሲያመጣ፣ በሌላው በኩል ብርሃን አመጣ፤ ስለዚህ ሌሊቱን በሙሉ አንዱ ወደ ሌላው ሊጠጋ አልቻለም።
21ሙሴ እጁን በባሕሩ ላይ ዘረጋ፤ እግዚአብሔር ሌሊቱን በሙሉ ብርቱ የምሥራቅ ነፋስ አስነሥቶ ባሕሩን ወደ ኋላ በማሸሽ ደረቅ ምድር አደረገው፤ ውሃውም ተከፈለ። 22እስራኤላውያን ውሃው በግራና በቀኝ እንደ ግድግዳ ሆኖ በየብስ በባሕሩ ውስጥ ዐለፉ።
23ግብጻውያንም አሳደዷቸው፤ የፈርዖን ፈረሶች፣ ሠረገሎችና ፈረሰኞች በሙሉ ተከትለዋቸው ወደ ባሕሩ ገቡ። 24ሲነጋጋም እግዚአብሔር በእሳትና በደመና ዐምድ ሆኖ የግብጻውያንን ሰራዊት ቍልቍል ተመለከተ፤ በግብጻውያን ሰራዊት ላይም ሽብር ላከባቸው። 25መንዳት እንዳይችሉም የሠረገላዎቹን መሽከርከሪያዎች አቈላለፈባቸው፤#14፥25 ወይም፤ የሠረገላዎቻቸው መሽከርከሪያዎች ዘለው ወጡ ግብጻውያኑም፣ “ከእስራኤላውያን እንሽሽ! እግዚአብሔር ግብጽን እየተዋጋላቸው ነው” አሉ።
26ከዚያም እግዚአብሔር ሙሴን፣ “ውሃው ግብጻውያንን ሠረገሎቻቸውንና ፈረሰኞቻቸውን ተመልሶ እንዲሸፍናቸው እጅህን በባሕሩ ላይ ዘርጋ” አለው። 27ሙሴም እጁን በባሕሩ ላይ ዘረጋ፤ ንጋት ላይም ባሕሩ ወደ ቀድሞ ቦታው ተመለሰ። ግብጻውያን ከውሃው ሸሹ፤#14፥27 ወይም፣ ወደ ውሃው ሸሹ እግዚአብሔርም ግብጻውያንን በባሕሩ ውስጥ ጣላቸው። 28ውሃውም ተመልሶ እስራኤላውያንን ተከትለው ወደ ባሕሩ የገቡትን ሠረገሎች፣ ፈረሰኞች፣ መላውን የፈርዖን ሰራዊት ሁሉ ሸፈነ። አንድም እንኳ አልተረፈም።
29እስራኤላውያን ግን ውሃው ግራና ቀኝ እንደ ግድግዳ ሆኖ፣ በደረቅ ምድር ባሕሩን ተሻገሩ። 30በዚያች ዕለት እግዚአብሔር እስራኤልን ከግብጻውያን እጅ አዳናቸው፤ እስራኤልም የግብጻውያን ሬሳ በባሕሩ ዳርቻ ወድቆ ተመለከቱ። 31እስራኤላውያን እግዚአብሔር በግብጻውያን ላይ ያደረገውን ታላቅ ኀይል ባዩ ጊዜ፣ እግዚአብሔርን ፈሩ፤ በእግዚአብሔርና በባሪያው በሙሴም አመኑ።
Currently Selected:
ዘፀአት 14: NASV
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.