ዘፀአት 17
17
ከዐለት የፈለቀ ውሃ
1መላው የእስራኤል ማኅበር ከሲና ምድረ በዳ ተነሥቶ እግዚአብሔር እንዳዘዘው ከስፍራ ወደ ስፍራ ተጕዞ በራፊዲም ሰፈረ፤ ነገር ግን ሕዝቡ የሚጠጡት ውሃ አልነበረም። 2ስለዚህ፣ “የምንጠጣውን ውሃ ስጠን” በማለት ሙሴን ተጣሉት።
ሙሴም፣ “እኔን ለምን ትጣሉኛላችሁ? እግዚአብሔርንስ ለምን ትፈታተኑታላችሁ?” አለ።
3ነገር ግን ሕዝቡ በዚያ ተጠምተው ስለ ነበር፣ በሙሴ ላይ አጕረመረሙ። እነርሱም፣ “እኛና ልጆቻችን እንዲሁም ከብቶቻችን በውሃ ጥም እንድናልቅ፣ ከግብጽ ለምን አወጣኸን?” አሉት።
4ከዚያም ሙሴ፤ “በዚህ ሕዝብ ምን ላድርግ? በድንጋይ ሊወግሩኝ ተዘጋጅተዋል” ብሎ ወደ እግዚአብሔር ጮኸ።
5 እግዚአብሔር ለሙሴ እንዲህ መለሰለት፤ “ከሕዝቡ ፊት ሂድ፤ ከእስራኤል አለቆች አንዳንዶቹን እንዲሁም አባይን የመታህባትን በትር ያዝና ሂድ። 6ኮሬብ አጠገብ ባለው ዐለት በዚያ እኔ በአንተ ፊት እቆማለሁ። ዐለቱን ምታው፤ ከርሱም ሕዝቡ የሚጠጡት ውሃ ይወጣል።” ስለዚህ ሙሴ በእስራኤል አለቆች ፊት ይህንኑ አደረገ። 7ስፍራውንም ማሳህና#17፥7 ማሳህ ማለት መፈተን ማለት ነው። መሪባ#17፥7 መሪባ ማለት መጣላት ማለት ነው። ብሎ ጠራው፤ እስራኤላውያን ጠብ ፈጥረው፣ “እግዚአብሔር ከእኛ ጋራ ነው ወይስ አይደለም” በማለት እግዚአብሔርን ተፈታትነዋልና።
አማሌቃውያን ተሸነፉ
8አማሌቃውያን መጥተው እስራኤላውያንን ራፊዲም ላይ ወጉ፤ 9ሙሴም ኢያሱን፣ “ከሰዎቻችን አንዳንዶቹን ምረጥና አማሌቃውያንን ለመውጋት ውጣ፤ በነገው ዕለት የእግዚአብሔርን በትር በእጆቼ ይዤ በኰረብታው ጫፍ ላይ እቆማለሁ።”
10ስለዚህ ኢያሱ ሙሴ ባዘዘው መሠረት ከአማሌቃውያን ጋራ ተዋጋ፤ ሙሴ፣ አሮንና ሖርም ወደ ኰረብታው ጫፍ ወጡ። 11ሙሴ እጆቹን ወደ ላይ በሚያነሣበት ጊዜ ሁሉ እስራኤላውያን ድል ያደርጉ ነበር። እጆቹን ባወረደ ጊዜ ግን አማሌቃውያን ያሸንፉ ነበር። 12የሙሴ እጆች እየዛሉ በሄዱ ጊዜ ድንጋይ ወስደው ከበታቹ አደረጉ፤ እርሱም ተቀመጠበት፤ አሮንና ሖርም አንዱ በአንዱ በኩል ሌላውም በሌላ በኩል ሆነው እጆቹን ወደ ላይ ያዙ። ይኸውም እጆቹ ፀሓይ እስክትጠልቅ ድረስ ጸንተው እንዲቈዩ ነው። 13ስለዚህ ኢያሱ የአማሌቃውያንን ሰራዊት በሰይፍ ድል አደረገ።
14ከዚያም እግዚአብሔር ሙሴን፣ “ሲታወስ እንዲኖር ይህን በጥቅልል መጽሐፍ ላይ ጻፈው፤ ኢያሱም መስማቱን አረጋግጥ፤ ምክንያቱም የአማሌቃውያንን ዝክር ከሰማይ በታች ፈጽሜ እደመስሳለሁ” አለው።
15ሙሴም መሠዊያውን ሠርቶ፣ “እግዚአብሔር ዐርማዬ ነው” ብሎ ሰየመው። 16“እጆች ወደ እግዚአብሔር ዙፋን ተዘርግተዋልና፤#17፥16 ወይም፣ ምክንያቱም እጅ በእግዚአብሔር ዙፋን ላይ ተዘርግቷል… እግዚአብሔር አማሌቃውያንን ከትውልድ እስከ ትውልድ ይዋጋቸዋል” አለ።
Currently Selected:
ዘፀአት 17: NASV
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.