ዘፀአት 18
18
ዮቶር ወደ ሙሴ መጣ
1የምድያም ካህን የሙሴ ዐማት ዮቶር፣ እግዚአብሔር ለሙሴና ለሕዝቡ ለእስራኤል ያደረገላቸውን ሁሉ እንዲሁም እግዚአብሔር እስራኤልን ከግብጽ እንዴት እንዳወጣቸው ሰማ።
2ሙሴ ሚስቱን ሲፓራን ከመለሳት በኋላ ዐማቱ ዮቶር እርሷንና ሁለት ወንድ ልጆቿን ተቀብሏቸው ነበር። 3ሙሴ፣ “በባዕድ አገር መጻተኛ ነኝ” ለማለት የመጀመሪያ ልጁን ስም ጌርሳም#18፥3 በዕብራይስጥ ጌርሳም የሚለው የቃል ድምፅ፣ መጻተኛ በዚያ አለ ከሚለው ሐረግ ጋራ ተመሳሳይ ድምፅ አለው። አለው። 4“የአባቴ አምላክ ረዳቴ ነው፤ ከፈርዖን ሰይፍ አድኖኛልና” ለማለት ደግሞ ሁለተኛውን ልጁን አልዓዛር#18፥4 አልዓዛር ማለት፣ አምላኬ ረዳት ነው ማለት ነው። አለው።
5የሙሴ ዐማት ዮቶር ከሙሴ ወንድ ልጆችና ሚስት ጋራ ሆኖ በምድረ በዳ ከእግዚአብሔር ተራራ አጠገብ ወደ ሰፈረበት ወደ ሙሴ መጣ። 6ዮቶር ወደ ሙሴ፣ “እኔ ዐማትህ ዮቶር፣ ከሚስትህና ከሁለት ወንዶች ልጆቿ ጋራ እየመጣን ነው” ሲል መልእክት ላከበት።
7ስለዚህ ሙሴ ዐማቱን ሊቀበለው ወጣ፤ ዝቅ ብሎ እጅ በመንሣትም ሳመው፤ ከዚያም ሰላምታ ተለዋውጠው ወደ ድንኳኑ ገቡ። 8ሙሴም እግዚአብሔር ለእስራኤል ሲል በፈርዖንና በግብጻውያን ላይ ያደረገውን ሁሉ፣ በመንገድም ላይ ስላጋጠማቸው መከራ ሁሉና እግዚአብሔርም እንዴት እንዳዳናቸው ለዐማቱ ነገረው።
9ዮቶርም እግዚአብሔር እነርሱን ከግብጻውያን እጅ በመታደግ ለእስራኤል ያደረገውን በጎ ነገር ሁሉ በመስማቱ ተደሰተ። 10እንዲህም አለ፤ “ከግብጻውያን እጅና ከፈርዖን ለታደጋችሁ፣ ከግብጻውያን እጅ ሕዝቡን ለታደገ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን። 11እግዚአብሔር ከአማልክት ሁሉ በላይ ኀያል እንደ ሆነ አሁን ዐወቅሁ፤ እስራኤልን በትዕቢት ይዘው በነበሩት ሁሉ ላይ ይህን አድርጓልና።” 12ከዚያም የሙሴ ዐማት ዮቶር የሚቃጠል መሥዋዕትና ሌሎች መሥዋዕቶች ለእግዚአብሔር አቀረበ፤ አሮንም ከሙሴ ዐማት ጋራ በእግዚአብሔር ፊት እንጀራ ለመብላት ከእስራኤል አለቆች ሁሉ ጋራ መጣ።
13በማግስቱም ሙሴ ሕዝቡን ለመዳኘት ተቀመጠ፤ እነርሱም በዙሪያው ከጧት እስከ ማታ ድረስ ቆሙ። 14ዐማቱም ሙሴ ለሕዝቡ የሚያደርገውን ሁሉ ባየ ጊዜ፣ “ምን ማድረግህ ነው? እነዚህ ሁሉ ሰዎች ከጧት እስከ ማታ በዙሪያህ ቆመው ሳለ፣ ብቻህን በፍርድ ወንበር ላይ ለምን ትቀመጣለህ?” አለው።
15ሙሴም እንዲህ ብሎ መለሰለት፤ “ምክንያቱም ሰዎቹ የእግዚአብሔር ፈቃድ በመፈለግ ወደ እኔ ይመጣሉ። 16ክርክር በኖራቸው ቍጥር ጕዳያቸው ወደ እኔ ይመጣል፤ ለግራና ለቀኙ የሚሆነውን እኔ ወስኜ የእግዚአብሔርን ሥርዐትና ሕጎች እነግራቸዋለሁ።”
17የሙሴ ዐማት መልሶ እንዲህ አለው። “የምትሠራው መልካም አይደለም። 18አንተና ወደ አንተ የሚመጡት እነዚህ ሰዎች የምታደርጉት ነገር ቢኖር ራሳችሁን ማድከም ነው፤ ሥራው ለአንተ ከባድ ሸክም ነው፤ ብቻህን ልትወጣው አትችልም። 19ምክር እሰጥሃለሁና አሁን እኔን ስሙኝ፤ እግዚአብሔር ከአንተ ጋራ ይሁን። አንተ በእግዚአብሔር ፊት ሕዝብን የምትወክል መሆን አለብህ፤ ክርክራቸውን ወደ እርሱ ታቀርባለህ። 20ሥርዐቶቹንና ሕጎቹን አስተምራቸው፤ እንዴት መኖር እንዳለባቸውና ምን መሥራት እንደሚገባቸው አሳያቸው። 21ነገር ግን ችሎታ ያላቸውን ሰዎች ከሕዝቡ ሁሉ ምረጥ፤ እነዚህም ሰዎች እግዚአብሔርን የሚፈሩ፣ ታማኞችና በማታለል የሚገኘውን ጥቅም የሚጸየፉ ይሁኑ። የሺሕ፣ የመቶ፣ የዐምሳ፣ የዐሥር፣ አለቃ አድርገህ ሹማቸው። 22በማንኛውም ጊዜ ሕዝቡን ይዳኙ፤ ቀላሉን ነገር እነርሱ ይወስኑ፤ አስቸጋሪ የሆነውን ጕዳይ ሁሉ ግን ለአንተ እንዲያቀርቡ አድርግ፤ ሥራውን ስለሚያግዙህ ሸክምህ ይቃለላል። 23አንተ ይህን ብታደርግና እግዚአብሔርም ይህንኑ ቢያዝዝህ፣ ድካምህን መቋቋም ትችላለህ፤ እነዚህም ሰዎች ሁሉ ረክተው ወደ ቤታቸው ይሄዳሉ።”
24ሙሴ ዐማቱን ሰማ፤ ያለውንም ሁሉ ፈጸመ። 25ሙሴም ከእስራኤል መካከል ችሎታ ያላቸውን ሰዎች መረጠና፤ የሕዝብ መሪዎች፣ በሺሕዎች፣ በመቶዎች፣ በዐምሳዎች በዐሥሮች ላይም አለቆች አደረጋቸው። 26ሁልጊዜም የሕዝብ ዳኞች ሆነው አገለገሉ፤ አስቸጋሪ ጕዳዮችን ወደ ሙሴ አመጡ፤ ቀላል የሆነውን ራሳቸው ወሰኑ።
27ከዚያም ሙሴ ዐማቱን በጕዞው ሸኘው፤ ዮቶርም ወደ አገሩ ተመለሰ።
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.