ዘፀአት 8
8
የጓጕንቸር መቅሠፍት
1ከዚያም እግዚአብሔር ሙሴን አለው፤ “ወደ ፈርዖን ዘንድ ሄደህ፣ እንዲህ በለው፤ ‘እግዚአብሔር የሚለው ይህ ነው፤ “እኔን ያመልኩኝ ዘንድ ሕዝቤን ልቀቅ። 2እነርሱን ለመልቀቅ እንቢ ብትል አገርህን ሁሉ በጓጕንቸር መቅሠፍት እመታዋለሁ። 3አባይ በጓጕንቸሮች ይሞላል፤ ወጥተውም ወደ ቤተ መንግሥትህና ወደ መኝታ ክፍልህ፣ ወደ ዐልጋህም ወደ ሹማምቶችህና ወደ ሕዝብህ ቤቶች፣ ወደ ምድጆችህና ወደ ቡሖቃዎችህ ይገባሉ። 4ጓጕንቸሮቹ ወደ አንተና ወደ ሕዝብህ ወደ ሹማምትህም ሁሉ ይመጡባችኋል።” ’ ”
5ከዚያም እግዚአብሔር ሙሴን አለው፣ “አሮንን፣ ‘በትርህን ይዘህ በምንጮች፣ በቦዮችና በኵሬዎች ላይ እጅህን ዘርጋ፤ ጓጕንቸሮችም በግብጽ ምድር ላይ እንዲወጡ አድርግ’ ” በለው።
6አሮንም በግብጽ ውሆች ላይ እጁን ዘረጋ፤ ጓጕንቸሮችም ወጥተው ምድሪቱን ሸፈኑ። 7ሆኖም ግን አስማተኞቹ በድብቅ ጥበባቸው ተመሳሳይ ነገር ሠሩ፤ እነርሱም በግብጽ ምድር ላይ ጓጕንቸሮች እንዲወጡ አደረጉ።
8ፈርዖንም ሙሴንና አሮንን አስጠርቶ እንዲህ አላቸው፤ “ጓጕንቸሮቹን ከእኔና ከሕዝቤ ያርቅ ዘንድ ወደ እግዚአብሔር ጸልዩልኝ፤ ከዚያም ለእግዚአብሔር መሥዋዕትን ትሠዉ ዘንድ ሕዝቡ እንዲሄዱ እፈቅዳለሁ”።
9ሙሴም ፈርዖንን፣ “በአባይ ወንዝ ካሉት በቀር ከአንተና ከቤቶችህ ጓጕንቸሮቹ እንዲወገዱ ለአንተ፣ ለሹማምትህና ለሕዝብህ የምንጸልይበትን ጊዜ እንድትወስን ለአንተ ትቼዋለሁ” አለው።
10ፈርዖንም፣ “ነገ ይሁን” አለው።
ሙሴም እንዲህ ብሎ መለሰ፤ “እንደ አምላካችን እንደ እግዚአብሔር ያለ ማንም እንደሌለ ታውቅ ዘንድ አንተ እንዳልኸው ይሆናል። 11ጓጕንቸሮቹም ከአንተና ከቤቶችህ፣ ከሹማምትህና ከሕዝብህ ተወግደው በአባይ ወንዝ ብቻ ይወሰናሉ።”
12ሙሴና አሮን ከፈርዖን ዘንድ ከተመለሱ በኋላ፣ በፈርዖን ላይ ስላመጣቸው ጓጕንቸሮች ሙሴ ወደ እግዚአብሔር ጮኸ። 13እግዚአብሔር ሙሴ እንደ ለመነው አደረገ፤ ጓጕንቸሮቹም በየቤቱ ውስጥ፣ በየዐጥር ግቢውና በየሜዳው ሞቱ። 14በአንድ ላይ ሰብስበው ከመሯቸው፤ ምድሪቱም ከረፋች። 15ፈርዖን ችግሩ ጋብ ማለቱን ባየ ጊዜ ግን ልክ እግዚአብሔር እንደ ተናገረው ልቡን በማደንደን ሙሴንና አሮንን አልሰማቸውም።
የተባይ መቅሠፍት
16ከዚያም እግዚአብሔር ሙሴን፣ “አሮንን ‘በትርህን ሰንዝረህ የምድርን ትቢያ ምታ’ በለው፤ ከዚያም በግብጽ ምድር ያለው ትቢያ ሁሉ ተናካሽ ትንኝ ይሆናል” አለው። 17እነርሱም እንዲሁ አደረጉ፣ አሮን በትሩን እንደ ያዘ እጁን ሲዘረጋና የምድሩን ትቢያ ሲመታ፣ በግብጽ ምድር ያለው ትቢያ ሁሉ ተናካሽ ትንኝ ሆነ። ሰውንም ሆነ እንስሳውን ተናካሽ ትንኝ ወረረው። 18ነገር ግን አስማተኞቹ በድብቅ ጥበባቸው ተናካሽ ትንኞችን ለመፍጠር ሲሞክሩ አልቻሉም።
ተናካሽ ትንኞቹም ከሰውና ከእንስሳው ላይ አልወረዱም ነበር። 19አስማተኞቹም ፈርዖንን፣ “ይህ የእግዚአብሔር ጣት ነው” አሉት፤ ነገር ግን የፈርዖን ልብ ደንድኖ ስለ ነበር፣ ልክ እግዚአብሔር እንደ ተናገረው አልሰማቸው አለ።
የዝንብ መቅሠፍት
20ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ “በጧት ተነሥተህ ፈርዖን ወደ ውሃ በሚወርድበት ጊዜ ከፊቱ ቀርበህ እንዲህ በለው፤ ‘እግዚአብሔር የሚለው ይህ ነው፤ ያመልኩኝ ዘንድ ሕዝቤን ልቀቅ። 21ሕዝቤ እንዲሄዱ ባትለቅቃቸው፣ በአንተና በሹማምትህ ላይ፣ በሕዝብህና በቤቶችህ ላይ የዝንብ መንጋ እሰድዳለሁ። ያረፉበት መሬት እንኳ ሳይቀር፣ የግብጻውያን ቤቶች ሁሉ ዝንብ ብቻ ይሆናሉ።
22“ ‘በዚያች ዕለት ግን ሕዝቤ የሚኖርባትን የጌሤምን ምድር የተለየች አደርጋታለሁ፤ እኔ እግዚአብሔር በዚህች ምድር እንዳለሁ ታውቅ ዘንድ የዝንብ መንጋ በዚያ አይኖርም። 23በሕዝቤና በሕዝብህ መካከል ልዩነት አደርጋለሁ፤ ይህ ታምራዊ ምልክት ነገ ይሆናል#8፥23 የሰብዓ ሊቃናቱና የቫልጌቱ ትርጕም እንዲሁ ሲሉ፣ ዕብራይስጡ ግን ነገ ዐርነት ይሆናል ይላል።።’ ”
24 እግዚአብሔርም እንዲሁ አደረገ፤ አስጨናቂ የዝንብ መንጋ በፈርዖን ቤተ መንግሥትና በሹማምቱ ቤቶች ላይ ወረደ፤ መላው የግብጽ ምድር ከዝንቡ የተነሣ ተበላሽቶ ነበር።
25ከዚያም ፈርዖን ሙሴንና አሮንን አስጠርቶ፣ “ሂዱና በዚሁ ምድር ለአምላካችሁ ሠዉ” አላቸው።
26ሙሴ ግን እንዲህ አለ፤ “ይህ ትክክል አይሆንም፤ ለአምላካችን ለእግዚአብሔር የምናቀርበው መሥዋዕት በግብጻውያን ዘንድ አስጸያፊ ነው፤ ታዲያ በእነርሱ ዐይን አስጸያፊ የሆነውን መሥዋዕት ብናቀርብ አይወግሩንምን? 27ለአምላካችን ለእግዚአብሔር እርሱ እንዳዘዘን መሥዋዕት ለመሠዋት ወደ ምድረ በዳ የሦስት ቀን መንገድ መሄድ አለብን።”
28ፈርዖንም፣ “ለአምላካችሁ ለእግዚአብሔር በምድረ በዳ መሥዋዕት እንድትሠዉ እፈቅድላችኋለሁ፤ ነገር ግን ርቃችሁ እንዳትሄዱ። ለእኔም ጸልዩልኝ” አላቸው።
29ሙሴም እንዲህ አለ፤ “ከአንተ እንደ ተለየሁ ወዲያውኑ ወደ እግዚአብሔር እጸልያለሁ፤ ነገም ዝንቡ ሁሉ ከፈርዖን፣ ከሹማምቱና ከሕዝቡ ይወገዳል። ብቻ ሕዝቡ ለእግዚአብሔር መሥዋዕት እንዲሠዉ ባለመፍቀድ ከዚህ ቀደም ፈርዖን አታልሎ እንዳደረገው አሁንም እንዳያደርግ ርግጠኛ ይሁን።”
30ከዚያም ሙሴ ከፈርዖን ተለይቶ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ። 31እግዚአብሔር ሙሴ የለመነውን አደረገ። የዝንቡም መንጋ ከፈርዖን፣ ከሹማምቱና ከሕዝቡ ተወገደ፤ አንድም ዝንብ እንኳ አልቀረም። 32በዚህም ጊዜ እንኳ ፈርዖን ልቡን አደነደነ እንጂ፣ ሕዝቡን አልለቀቀም።
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.