ሕዝቅኤል 8
8
ባዕድ አምልኮ በቤተ መቅደስ
1በስድስተኛው ዓመት፣ በስድስተኛው ወር፣ በዐምስተኛው ቀን በቤቴ ተቀምጬ ሳለሁ፣ የይሁዳም ሽማግሌዎች በፊቴ ተቀምጠው ሳሉ፣ በዚያ የጌታ እግዚአብሔር እጅ በላዬ መጣች። 2እኔም አየሁ፤ እነሆ፤ የሰውን ልጅ የሚመስል#8፥2 ወይም እሳት የሚመስል አየሁ ነበረ፤ ወገቡ ከሚመስለው ጀምሮ ወደ ታች እንደ እሳት ያለ ነበር፤ ወገቡንም ከሚመስለው ጀምሮ ወደ ላይ እንደ ጋለ ብረት ያበራ ነበር። 3እርሱም እጅ መሳይ ዘርግቶ የራስ ጠጕሬን ያዘ፤ መንፈስም በምድርና በሰማይ መካከል አነሣኝ፤ እርሱም ቅናት የሚያነሣው ጣዖት ወደ ቆመበት፣ ወደ ውስጠኛው አደባባይ መግቢያ ወደ ሰሜን በር ወደ ኢየሩሳሌም በእግዚአብሔር ራእይ ወሰደኝ። 4እነሆ፤ በረባዳው ስፍራ በራእይ ያየሁት የእስራኤል አምላክ ክብር በዚያ ነበረ።
5እርሱም፣ “የሰው ልጅ ሆይ፤ ወደ ሰሜን ተመልከት” አለኝ። እኔም ተመለከትሁ፤ እነሆ ከመሠዊያው በር በሰሜን በኩል መግቢያው ላይ ይህ የቅናት ጣዖት ነበረ።
6ደግሞም፣ “የሰው ልጅ ሆይ፤ የእስራኤል ቤት ከመቅደሴ ያርቀኝ ዘንድ በዚህ የሚያደርገውን እጅግ አስጸያፊ ነገር ታያለህን? ከዚህም የባሰ አስጸያፊ ነገር ታያለህ” አለኝ።
7ከዚያም በኋላ ወደ አደባባዩ መግቢያ አመጣኝ፤ እኔም ግንቡን ተመለከትሁ፤ ቀዳዳም ነበረበት። 8እርሱም፣ “የሰው ልጅ ሆይ፤ ግንቡን ንደለው” አለኝ፤ እኔም ግንቡን ነደልሁት፤ አንድ በርም አገኘሁ።
9እርሱም፣ “ግባና በዚህ የሚፈጽሙትን እጅግ የከፋ ርኩሰት ተመልከት አለኝ።” 10እኔም ገብቼ አየሁ፤ እነሆ የሚሳቡ ፍጥረታትና የርኩሳን አራዊት ዐይነት ሁሉ፣ የእስራኤልም ቤት ጣዖታት ሁሉ ዙሪያውን በግንቡ ላይ ተቀርጸው ነበር። 11በእነዚህም ፊት ከእስራኤል ቤት ሰባ ሽማግሌዎች ቆመው ነበር፤ በመካከላቸውም የሳፋን ልጅ ያእዛንያ ቆሞ ነበር፤ እያንዳንዳቸውም በእጃቸው ጥና ይዘዋል፤ መልካም መዐዛ ያለው የዕጣን ጢስም እየተትጐለጐለ ይወጣ ነበር።
12እርሱም፣ “የሰው ልጅ ሆይ፤ የእስራኤል ቤት ሽማግሌዎች እያንዳንዳቸው በጣዖታቸው ምስል ጓዳ ውስጥ በጨለማ የሚያደርጉትን አይተሃልን? እነርሱ፣ ‘እግዚአብሔር አያየንም፤ እግዚአብሔር ምድሪቱን ትቷል ይላሉ’ ” አለኝ። 13ደግሞም፣ “ከእነዚህ የባሰ አስጸያፊ ነገር ሲሠሩ ታያለህ” አለኝ።
14ከዚህም በኋላ በሰሜን በኩል ወዳለው ወደ እግዚአብሔር ቤት በር መግቢያ አመጣኝ፤ በዚያም ሴቶች ተቀምጠው ተሙዝ ለተባለው ጣዖት ሲያለቅሱ አየሁ። 15እርሱም፣ “የሰው ልጅ ሆይ፤ ይህን አይተሃልን? ከዚህም የባሰ አስጸያፊ ነገር ታያለህ” አለኝ።
16ደግሞም ወደ እግዚአብሔር ቤት ወደ ውስጠኛው አደባባይ አመጣኝ፤ እነሆም በመተላለፊያውና በመሠዊያው መካከል በቤተ መቅደሱ መግቢያ ላይ ሃያ ዐምስት ሰዎች ያህል ነበሩ፤ ጀርባቸውን ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ፣ ፊታቸውን ወደ ምሥራቅ አድርገው ለምትወጣዋ ፀሓይ ይሰግዱ ነበር።
17እርሱም እንዲህ አለኝ፤ “የሰው ልጅ ሆይ፤ ይህን አይተሃልን? የይሁዳ ቤት በዚህ ቦታ የሚፈጽሙት ጸያፍ ተግባር ቀላል ነገር ነውን? ምድሪቱንስ በዐመፅ በመሙላት ዘወትር ያስቈጡኝ ዘንድ ይገባልን? እነሆ፤ ቅርንጫፉን ወደ አፍንጫቸው አቅርበዋል! 18ስለዚህ በቍጣ እመጣባቸዋለሁ፤ በርኅራኄ ዐይን አላያቸውም፤ ከሚመጣባቸው ነገር አላድናቸውም፤ ወደ ጆሮዬም ቢጮኹ አልሰማቸውም።”
Currently Selected:
ሕዝቅኤል 8: NASV
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.