የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ሕዝቅኤል 9

9
የጣዖት አምላኪዎች መገደል
1ከዚያም እኔ እየሰማሁ ከፍ ባለ ድምፅ፣ “እያንዳንዳቸው በእጃቸው የጦር መሣሪያ የያዙ፣ ከተማዪቱን የሚቀጡ ወደዚህ ይምጡ” ብሎ ከፍ ባለ ድምፅ ጮኸ። 2እነሆም፤ አጥፊ የሆነ የጦር መሣሪያ በእጃቸው የያዙ ስድስት ሰዎች በሰሜን አቅጣጫ ካለው ከላይኛው በር መጡ፤ ከእነርሱም ጋራ ቀጭን በፍታ የለበሰ፣ በጐኑም የጽሕፈት ዕቃ ማኅደር ያነገበ ሰው ነበር። እነርሱም ገብተው በናሱ መሠዊያ አጠገብ ቆሙ።
3በዚህ ጊዜ የእስራኤል አምላክ ክብር ከነበረበት ከኪሩብ በላይ ተነሥቶ ወደ ቤተ መቅደሱ መድረክ ሄደ። እግዚአብሔርም በፍታ የለበሰውን በጐኑም የጽሕፈት ዕቃ ማኅደር ያነገበውን ሰው ጠራ፤ 4እግዚአብሔርም፣ “በኢየሩሳሌም ከተማ ሁሉ ሂድና በውስጧ ስለ ተሠራው ጸያፍ ተግባር ሲያዝኑና ሲያለቅሱ በነበሩ ሰዎች ግንባር ላይ ምልክት አድርግ” አለው።
5እኔም እየሰማሁ፣ ለሌሎቹ እንዲህ አለ፤ “በከተማዪቱ ሁሉ እርሱን ተከትላችሁ ግደሉ፤ ዐዘኔታና ርኅራኄ አታሳዩ፤ ግደሉ፤ 6ሽማግሌውን፣ ጕልማሳውንና ልጃገረዲቱን፤ ሴቶችንና ሕፃናትን ፈጽማችሁ አጥፉ፤ ነገር ግን ምልክቱ ያለበትን ሰው አትንኩ፤ ከቤተ መቅደሴም ጀምሩ።” ስለዚህ በቤተ መቅደሱ ፊት ለፊት ከነበሩት ሽማግሌዎች ጀመሩ።
7እርሱም፣ “ቤተ መቅደሴን አርክሱ፤ አደባባዩንም ሬሳ በሬሳ አድርጉ፤ ሂዱ!” አላቸው። እነርሱም ወጥተው በከተማዪቱ ሁሉ እየተዘዋወሩ መግደል ጀመሩ። 8እነርሱ እየገደሉ እኔም ብቻዬን ሳለሁ፣ በግንባሬ ተደፍቼ፣ “ወዮ! ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ በኢየሩሳሌም ላይ መዓትህን አውርደህ የእስራኤልን ቅሬታዎች ሁሉ ልታጠፋ ነውን?” በማለት ጮኽሁ።
9እርሱም እንዲህ ሲል መለሰልኝ፤ “የእስራኤልና የይሁዳ ቤት ኀጢአት እጅግ በዝቷል፤ ምድሪቱ በደም ተጥለቅልቃለች፤ ከተማዪቱም ግፍን ተሞልታለች። እነርሱ፣ ‘እግዚአብሔር ምድሪቱን ትቷታል፤ እግዚአብሔር አያይም’ ይላሉ፤ 10እኔም የሠሩትን ሥራ በራሳቸው ላይ እመልስባቸዋለሁ እንጂ በርኅራኄ ዐይን አላያቸውም፤ ከሚመጣባቸውም ነገር አላድናቸውም።”
11እነሆ በፍታ የለበሰውና በጐኑም የጽሕፈት ዕቃ ማኅደር ያነገበው ሰው ተመልሶ፣ “እንዳዘዝኸው ፈጽሜአለሁ” አለ።

Currently Selected:

ሕዝቅኤል 9: NASV

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ