ዘፍጥረት 24

24
የይሥሐቅና የርብቃ ጋብቻ
1በዚህ ጊዜ አብርሃም ሸመገለ፤ ዕድሜውም ገፋ፤ እግዚአብሔርም አብርሃምን በሁሉ ነገር ባረከው። 2አብርሃም የንብረቱ ሁሉ ኀላፊ፣ የቤቱ ሁሉ አዛዥ#24፥2 ወይም ታላቅ የሆነውን አረጋዊ አገልጋዩን እንዲህ አለው፤ “እጅህን ከጭኔ በታች አድርግ፤ 3ልጄን፣ በመካከላቸው ከምኖር ከከነዓናውያን ሴቶች ልጆች ጋራ እንዳታጋባው በሰማይና በምድር አምላክ በእግዚአብሔር ማልልኝ። 4ነገር ግን ወደ አገሬ፣ ወደ ገዛ ዘመዶቼ ሄደህ ለልጄ ለይሥሐቅ ሚስት ትፈልግለታለህ።”
5አገልጋዩም፣ “ሴቲቱ ከእኔ ጋራ ወደዚህ ምድር ለመምጣት ፈቃደኛ ባትሆን ምን አደርጋለሁ? ልጅህን አንተ ወደ መጣህበት አገር ልውሰደውን?” ሲል ጠየቀው።
6አብርሃምም እንዲህ አለው፤ “ምንም ቢሆን ልጄን ወደዚያ እንዳትመልሰው ተጠንቀቅ፤ 7ከአባቴ ቤት፣ ከትውልድ አገሬ ያወጣኝና፣ ‘ለዘርህ ይህችን ምድር እሰጣለሁ’ ብሎ በመሐላ ተስፋ የገባልኝ የሰማይ አምላክ እግዚአብሔር መልአኩን ከፊትህ ይልካል፤ ለልጄም ሚስት ከዚያ ታመጣለታለህ። 8ሴቲቱ ዐብራህ ወደዚህ ለመምጣት ፈቃደኛ ካልሆነች ግን ካስማልሁህ መሐላ ነጻ ትሆናለህ፤ ነገር ግን ወደዚያ አትውሰደው” አለው። 9ስለዚህም አገልጋዩ እጁን ከጌታው ከአብርሃም ጭን በታች አድርጎ ስለዚህ ጕዳይ ማለለት።
10አገልጋዩም ከጌታው ግመሎች መካከል ዐሥሩን ወሰደ፤ ምርጥ ምርጡንም ዕቃ ሁሉ ጭኖ፣ የናኮር ከተማ ወደምትገኝበት ወደ ሰሜን ምዕራብ መስጴጦምያ ተጓዘ። 11እዚያም እንደ ደረሰ፣ ግመሎቹን ከከተማው ውጭ የውሃ ጕድጓድ አጠገብ አንበረከከ፤ ጊዜውም ውሃ ለመቅዳት የሚወጣበት ነበር።
12ከዚያም እንዲህ ሲል ጸለየ፣ “የጌታዬ የአብርሃም አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፤ በዛሬው ቀን ጕዳዬን አሳካልኝ፤ ለጌታዬ ለአብርሃም ቸርነትህን አሳየው። 13እነሆ፤ እኔ በዚህ ምንጭ አጠገብ ቆሜአለሁ፤ የከተማዪቱ ሴቶች ልጆች ውሃ ለመቅዳት ወደዚህ ይመጣሉ። 14እንግዲህ፣ ‘እንስራሽን አውርጂና ውሃ አጠጪኝ’ ስላት፣ ‘ዕንካ ጠጣ፤ ግመሎችህንም ላጠጣልህ’ የምትለኝ ቈንጆ እርሷ ለባሪያህ ለይሥሐቅ የመረጥሃት ትሁን፤ በዚህም ለጌታዬ ቸርነትህን እንዳሳየኸው ዐውቃለሁ።”
15እርሱም ገና ጸሎቱን ሳይጨርስ፣ እነሆ፤ ከአብርሃም ወንድም ከናኮርና ከሚስቱ ከሚልካ የተወለደው የባቱኤል ልጅ ርብቃ እንስራዋን በትከሻዋ ላይ አድርጋ ብቅ አለች። 16ልጃገረዲቱ እጅግ ውብና ወንድ ያላወቃት ድንግል ነበረች። ወደ ምንጩም ወርዳ ውሃ በእንስራዋ ሞልታ ተመለሰች።
17አገልጋዩም ወደ እርሷ ፈጥኖ ቀረበና፣ “እባክሽ ከእንስራሽ ጥቂት ውሃ አጠጪኝ” አላት።
18እርሷም፣ “ጌታዬ፤ ጠጣ” አለችው፤ ፈጥናም እንስራዋን ወደ እጇ አውርዳ አጠጣችው።
19እርሱን ካጠጣችው በኋላ፣ “ግመሎችህም ጠጥተው እስኪጠግቡ ድረስ ውሃ እቀዳላቸዋለሁ” አለች። 20ፈጥናም በእንስራው ውስጥ የነበረውን ውሃ በገንዳ ውስጥ ገለበጠች፤ እየሮጠች ከጕድጓዱ ውሃ እያመላለሰች ግመሎቹ እስኪበቃቸው ድረስ አጠጣቻቸው። 21አገልጋዩም አንዲት ቃል ሳይናገራት፣ እግዚአብሔር መንገዱን አሳክቶለት እንደ ሆነ ወይም እንዳልሆነ ለማወቅ ልጅቱን በአንክሮ ይከታተል ነበር።
22ግመሎቹ ጠጥተው ካበቁ በኋላ ሰውየው ግማሽ ሰቅል#24፥22 5.5 ግራም ያህል ነው። የሚመዝን የወርቅ ቀለበትና ዐሥር ሰቅል#24፥22 110 ግራም ያህል ነው። የሚመዝኑ ሁለት የወርቅ አምባሮች አውጥቶ፣ 23“ለመሆኑ አንቺ የማን ልጅ ነሽ? በአባትሽ ቤት የምናድርበት ስፍራ ይገኝ እንደ ሆነ፣ እባክሽ ንገሪኝ” ብሎ ጠየቃት።
24እርሷም፣ “እኔ፣ ሚልካ ለናኮር የወለደችለት፣ የባቱኤል ልጅ ነኝ” አለችው፤ 25ደግሞም፣ “በቤታችን በቂ ገለባና ድርቈሽ እንዲሁም ለእናንተ የሚሆን ማደሪያ አለን” አለችው።
26ሰውየውም ተደፍቶ ለእግዚአብሔር ሰገደ፤ 27እንዲህም አለ፤ “ቸርነቱንና ታማኝነቱን ከጌታዬ ያላጓደለ፣ እኔንም ወደ ጌታዬ ዘመዶች ቤት የመራኝ፣ የጌታዬ የአብርሃም አምላክ እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን።”
28ልጅቷ ሮጣ ሄዳ፣ የሆነውን ሁሉ ለእናቷ ቤተ ሰቦች ነገረች። 29ርብቃም ላባ የተባለ ወንድም ነበራት፤ እርሱም ሰውየው ወዳለበት የውሃ ጕድጓድ ፈጥኖ ሄደ። 30እኅቱ ያደረገችውን የወርቅ ቀለበትና አምባሮች እንዳየ፣ እንዲሁም ርብቃ ሰውየው ያላትን ስትናገር እንደ ሰማ፣ ወዲያውኑ ወደ ሰውየው ሄደ፤ በምንጩም ዳር ከግመሎቹ አጠገብ ቆሞ አገኘው፤ 31እርሱንም “አንተ የእግዚአብሔር ቡሩክ ሆይ፤ ና፤ እዚህ ውጭ የቆምኸው ለምንድን ነው? እነሆ፤ ለአንተ ማረፊያ ለግመሎችህም ማደሪያ አዘጋጅቻለሁ” አለው።
32ሰውየው ከላባ ጋራ ወደ ቤት ሄደ፤ የግመሎቹ ጭነት ተራግፎ ገለባና ድርቈሽ ተሰጣቸው፤ ለርሱና ዐብረውት ለነበሩት ሰዎች የእግር ውሃ ቀረበላቸው። 33ለሰውየውም ማእድ ቀረበለት፤ እርሱ ግን፣ “የመጣሁበትን ጕዳይ ሳልናገር እህል አልቀምስም” አለ።
ላባም፣ “ዕሺ፤ ተናገር” አለው።
34እርሱም እንዲህ አለ፤ “እኔ የአብርሃም አገልጋይ ነኝ፤ 35እግዚአብሔር ጌታዬን እጅግ ባርኮታል፤ እርሱም በልጽጓል፤ በጎችና ከብቶች፣ ብርና ወርቅ፣ ወንድና ሴት አገልጋዮች፣ ግመሎችና አህዮች ሰጥቶታል። 36የጌታዬ ሚስት ሣራ በስተርጅናዋ#24፥36 ወይም በስተርጅናው ወንድ ልጅ ወልዳለታለች፤ ጌታዬም ያለውን ሀብት ሁሉ ለልጁ ሰጥቶታል። 37ጌታዬ እንዲህ ሲል አማለኝ፤ ‘ከዚህ ከምኖርበት አገር፣ ከከነዓናውያን ሴቶች ልጆች ጋራ ልጄን አታጋባው፤ 38ነገር ግን ወደ አባቴ ቤት፣ ወደ ገዛ ወገኖቼ ሄደህ ለልጄ ሚስት አምጣለት።’
39“እኔም ጌታዬን፣ ‘ሴቲቱ ከእኔ ጋራ ወደዚህ ለመምጣት ባትፈቅድስ?’ ብዬ ጠየቅሁት።
40“እርሱም እንዲህ አለኝ፤ ‘አካሄዴን በፊቱ ያደረግሁ እግዚአብሔር መልአኩን ከአንተ ጋራ ይልካል፤ ከገዛ ወገኖቼና ከአባቴ ቤት፣ ለልጄ ሚስት እንድታመጣለት መንገድህን ያቃናል። 41ወደ ወገኖቼ ከሄድህ፣ ከመሐላው የተፈታህ ትሆናለህ፤ እነርሱ እንኳ ልጅቱን አንሰጥም ቢሉህ፣ ከመሐላው ንጹሕ ትሆናለህ’ አለኝ።
42“እኔም ዛሬ ወደ ውሃው ጕድጓድ ስደርስ እንዲህ ብዬ ጸለይሁ፤ ‘የጌታዬ የአብርሃም አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፤ ፈቃድህ ቢሆን የመጣሁበትን ጕዳይ አቃናልኝ፤ 43እነሆ፤ በምንጩ አጠገብ ቆሜአለሁ፤ ውሃ ልትቀዳ የምትመጣውን ኮረዳ፣ “ከእንስራሽ ውሃ አጠጪኝ” ስላት፣ 44“ዕሺ ጠጣ፤ ለግመሎችህም እቀዳላቸዋለሁ” የምትለኝ እርሷ እግዚአብሔር ለጌታዬ ልጅ የመረጣት ትሁን።’
45“በልቤ የምጸልየውን ጸሎት ገና ሳልጨርስ፣ ርብቃ እንስራዋን በትከሻዋ ላይ አድርጋ ብቅ አለች፤ ወደ ምንጩም ወርዳ ውሃ ቀዳች። እኔም፣ ‘እባክሽ፤ ውሃ አጠጪኝ’ አልኋት።
46“እርሷም ፈጥና እንስራዋን ከትከሻዋ አውርዳ፣ ‘ጠጣ፤ ግመሎችህንም አጠጣለሁ’ አለች። እኔም ጠጣሁ፤ ግመሎቹንም አጠጣች።
47“ለመሆኑ ‘የማን ልጅ ነሽ’ ብዬ ጠየቅኋት።
“እርሷም፣ ‘ሚልካ ለናኮር የወለደችለት፣ የባቱኤል ልጅ ነኝ’ አለችኝ።
“ከዚያም ቀለበቱን አደረግሁላት፤ አምባሩንም በእጇ አስገባሁላት። 48ተደፍቼም ለእግዚአብሔር ሰገድሁ፤ ለጌታዬ ወንድም የልጅ ልጅ የሆነችውን ቈንጆ፣ ለጌታዬ ልጅ እንዳገኝለት በቀና መንገድ የመራኝን የጌታዬ የአብርሃምን አምላክ እግዚአብሔርን አመሰገንሁ። 49እንግዲህ አሁን ለጌታዬ በጎነትና ታማኝነት የምታሳዩ ከሆነ ሐሳባችሁን አስታውቁኝ፤ ካልሆነ ግን ቍርጡን ንገሩኝና የምሄድበትን ልወስን።”
50ላባና ባቱኤል እንዲህ ሲሉ መለሱ፤ “ነገሩ ከእግዚአብሔር ስለ ሆነ በዚህም ሆነ በዚያ ምንም ማለት አንችልም። 51ርብቃ ይቻትልህ፤ ይዘሃት ሂድ፤ እግዚአብሔር እንደ ተናገረው ለጌታህ ልጅ ሚስት ትሁነው።”
52የአብርሃም አገልጋይ ያሉትን በሰማ ጊዜ በምድር ላይ ተደፍቶ ለእግዚአብሔር ሰገደ። 53ከዚያም የወርቅና የብር ጌጣጌጥ፣ እንዲሁም ልብሶች አውጥቶ ለርብቃ ሰጣት፤ ደግሞም ለወንድሟና ለእናቷ ከፍ ያለ ዋጋ ያላቸው ስጦታዎች ሰጣቸው። 54እርሱና ዐብረውት የነበሩ ሰዎችም በልተው፣ ጠጥተው እዚያው ዐደሩ።
በማግስቱም ጧት ሲነሡ፣ የአብርሃም አገልጋይ፣ “እንግዲህ ወደ ጌታዬ እንድመለስ አሰናብቱኝ” አለ።
55ወንድሟና እናቷም፣ “ልጅቷ ከእኛ ጋራ ቢያንስ ዐሥር ቀን ያህል ትቈይና ከዚያ በኋላ ልትሄድ#24፥55 ወይም ልትሄጂ ትችላለች።” ብለው መለሱ።
56እርሱ ግን፣ “እግዚአብሔር መንገዴን አቅንቶልኛልና አታዘግዩኝ፤ ወደ ጌታዬ እንድመለስ አሰናብቱኝ” አላቸው።
57እነርሱም፣ “ለማንኛውም ልጅቱን እንጥራትና ትጠየቅ” አሉ። 58ስለዚህ ርብቃን ጠርተው፣ “ከዚህ ሰው ጋራ መሄድ ትፈቅጃለሽ?” ሲሉ ጠየቋት።
እርሷም፣ “አዎን፤ እሄዳለሁ” አለች።
59ከዚያም እኅታቸውን ርብቃን ከሞግዚቷ ጋራ፣ እንዲሁም የአብርሃምን አገልጋይና ዐብረውት የነበሩትን ሰዎች አሰናበቷቸው። 60ርብቃንም እንዲህ ብለው መረቋት፤
“እኅታችን ሆይ፤ እልፍ አእላፋት ሁኚ፤
ዘርሽ የጠላቶቹን ደጆች ይውረስ”።
61ከዚያም ርብቃና አገልጋዮቿ ተዘጋጁ፤ ግመሎቻቸውም ላይ ወጥተው ሰውየውን ተከተሉት፤ በዚህ ሁኔታ አገልጋዩ ርብቃን ይዟት ሄደ።
62በዚህ ጊዜ፣ ይሥሐቅ በኔጌብ ይኖር ስለ ነበር፣ ከብኤርላሃይሮኢ መጥቶ ነበር። 63ይሥሐቅም አንድ ምሽት ላይ በጥሞና#24፥63 በዕብራይስጥ የዚህ ቃል ትርጕም አይታወቅም። ለመቈየት ወደ መስክ ወጣ አለ፤ ቀና ብሎ ሲመለከትም፣ ግመሎች ከሩቅ ሲመጡ አየ። 64ርብቃም እንደዚሁ አሻግራ ስትመለከት፣ ይሥሐቅን አየች፤ ከግመልም ወረደች፤ 65አገልጋዩንም፣ “ይህ ሊገናኘን በመስኩ ውስጥ ወደዚህ የሚመጣው ሰው ማን ነው?” ስትል ጠየቀችው።
አገልጋዩም፣ “ጌታዬ ነው” ብሎ መለሰላት፤ እርሷም መሸፈኛዋን ተከናነበች።
66አገልጋዩም ያደረገውን ሁሉ ለይሥሐቅ ነገረው። 67ይሥሐቅም ርብቃን ወደ እናቱ ወደ ሣራ ድንኳን ይዟት ገባ፤ አገባት፣ ሚስትም ሆነችው፤ እርሱም ወደዳት። ይሥሐቅም ከእናቱ ሞት ተጽናና።

Currently Selected:

ዘፍጥረት 24: NASV

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ