የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ዘፍጥረት 27

27
ይሥሐቅ ያዕቆብን ባረከው
1ይሥሐቅ አርጅቶ፣ ዐይኖቹ ደክመው ማየት በተሳናቸው ጊዜ፣ ታላቁን ልጁን ዔሳውን ጠርቶ፣ “ልጄ ሆይ” አለው።
እርሱም፣ “እነሆ፤ አለሁ” አለ።
2ይሥሐቅም እንዲህ አለ፤ “ይኸው እኔ አርጅቻለሁ፤ የምሞትበትንም ቀን አላውቅም 3ስለዚህ የዐደን መሣሪያህን፦ የፍላጻ ኰረጆህንና ቀስትህን ይዘህ ወደ ዱር ሂድ፤ አድነህም አምጣልኝ። 4ከመሞቴ በፊት እንድመርቅህ የምወድደውን ዐይነት ጣዕም ያለው ምግብ አዘጋጅተህ አብላኝ።”
5ይሥሐቅ ለልጁ የተናገረውን ርብቃ ትሰማ ስለ ነበር፣ ዔሳው የታዘዘውን ለማምጣት ለዐደን እንደ ወጣ፣ 6ርብቃ ለልጇ ለያዕቆብ እንዲህ አለችው፤ “አባትህ ዔሳውን፣ 7‘ከመሞቴ በፊት በእግዚአብሔር ፊት እንድመርቅህ፣ ጥሩ ጣዕም ያለው ምግብ እንድበላ አዘጋጅልኝ።’ ሲለው ሰምቻለሁ፤ 8ልጄ ሆይ፤ እንግዲህ የምነግርህን በጥሞና ስማኝ፤ የምልህንም አድርግ። 9ተነሣና ወደ መንጋው ሄደህ ሁለት ፍርጥም ያሉ የፍየል ጠቦቶች አምጣልኝ፤ እኔም አባትህ የሚወድደውን ዐይነት ምግብ አዘጋጅለታለሁ፤ 10እርሱም ከመሞቱ በፊት እንዲመርቅህ ይዘህለት ግባና ይብላ።”
11ያዕቆብም እናቱን ርብቃን እንዲህ አላት፤ “ወንድሜ ዔሳው ሰውነቱ ጠጕራም ነው፤ የእኔ ገላ ግን ለስላሳ ነው። 12ታዲያ፣ አባቴ ቢዳስሰኝ እንዳታለልሁት ያውቃል፤ ይህ ከሆነ ደግሞ፣ በምርቃት ፈንታ ርግማን አተርፋለሁ ማለት ነው።”
13እናቱም፣ “ልጄ ሆይ፤ የአንተ ርግማን በእኔ ላይ ይድረስ፤ ግድ የለህም፤ እንደ ነገርሁህ ሄደህ ጠቦቶቹን አምጣልኝ” አለችው።
14እርሱም ሄዶ ጠቦቶቹን ለእናቱ አመጣላት፤ እርሷም ልክ አባቱ እንደሚወድደው ዐይነት አጣፍጣ ጥሩ ምግብ አዘጋጀችለት። 15ከዚያም ርብቃ በቤት ያስቀመጠችውን የታላቁን ልጇን የዔሳውን ምርጥ ልብስ አንሥታ ለታናሹ ልጇ ለያዕቆብ አለበሰችው። 16እንዲሁም የዐንገቱን ለስላሳ ክፍል የጠቦቶቹን ቈዳ አለበሰችው። 17ከዚያም ያሰናዳችውን ጣፋጭ መብልና እንጀራ ለያዕቆብ ሰጠችው።
18ያዕቆብም ወደ አባቱ ሄዶ፣ “አባቴ ሆይ” አለ፤ ይሥሐቅም፣ “እነሆ፤ አለሁ ልጄ፤ ለመሆኑ አንተ ማን ነህ?” አለው።
19ያዕቆብም አባቱን፣ “እኔ የበኵር ልጅህ ዔሳው ነኝ፤ ያዘዝኸኝን አድርጌአለሁ፤ እስኪ ቀና በልና እንድትመርቀኝ ዐድኜ ካመጣሁት ብላ” አለ።
20ይሥሐቅ ልጁን፣ “ልጄ ሆይ፤ ከመቼው ቀንቶህ መጣህ?” ሲል ጠየቀው። ያዕቆብም፣ “እግዚአብሔር አምላክህ አሳካልኝ” ብሎ መለሰለት።
21ይሥሐቅም ያዕቆብን፣ “ልጄ ሆይ፤ አንተ በርግጥ ልጄ ዔሳው መሆንህን እንዳውቅ፣ እስኪ ቀረብ በልና ልዳብስህ” አለው።
22ያዕቆብም ወደ አባቱ ወደ ይሥሐቅ ተጠጋ፤ አባቱም በእጁ እየዳሰሰው፣ “ይህ ድምፅ የያዕቆብ ድምፅ ነው፤ እጆቹ ግን የዔሳው እጆች ናቸው” አለ። 23እጆቹ እንደ ወንድሙ እንደ ዔሳው እጆች ጠጕራም ስለ ሆኑ፣ ይሥሐቅ ያዕቆብን ለይቶ ማወቅ አልቻለም፤ ስለዚህ ባረከው። 24ይሥሐቅም፣ “በርግጥ አንተ ልጄ ዔሳው ነህ?” ሲል ጠየቀው።
ያዕቆብም፣ “አዎን፤ ነኝ” ብሎ መለሰ።
25ከዚያም፣ “በል እንግዲህ ልጄ፤ እንድመርቅህ፣ ዐድነህ ካመጣኸው አቅርብልኝና ልብላ” አለው።
ያዕቆብም ምግቡን ለአባቱ አቀረበለት፤ የወይን ጠጅም አመጣለት፤ እርሱም በላ፤ ጠጣም። 26ከዚያም አባቱ ይሥሐቅ፣ ያዕቆብን፣ “ልጄ ሆይ፤ እስኪ ቀረብ በልና ሳመኝ” አለው።
27ያዕቆብም ቀርቦ ሳመው፤ ይሥሐቅ የያዕቆብን ልብስ ካሸተተ በኋላ እንዲህ ብሎ መረቀው፤
“እነሆ፤ የልጄ ጠረን፣
እግዚአብሔር እንደ ባረከው፣
እንደ መስክ መዐዛ ነው።
28እግዚአብሔር የሰማይን ጠል፣
የምድርንም በረከት፣
የተትረፈረፈ እህልና የወይን ጠጅ ይስጥህ።
29መንግሥታት ይገዙልህ፤
ሕዝቦችም ተደፍተው እጅ ይንሡህ፤
የወንድሞችህ ጌታ ሁን፤
የእናትህም ልጆች ተደፍተው እጅ ይንሡህ፤
የሚረግሙህ የተረገሙ ይሁኑ፤
የሚባርኩህ የተባረኩ ይሁኑ።”
30ይሥሐቅ ያዕቆብን መርቆ እንዳበቃ፣ ያዕቆብ ገና ከአባቱ ዘንድ ሳይወጣ ወዲያውኑ፣ ወንድሙ ዔሳው ከዐደን ተመለሰ። 31እርሱም ደግሞ ጣፋጭ ምግብ በማዘጋጀት ለአባቱ አቅርቦ፣ “አባቴ ሆይ፤ እንድትመርቀኝ፣ እስኪ ቀና በልና ካደንሁት ብላ” አለው።
32አባቱ ይሥሐቅም፣ “አንተ ደግሞ ማን ነህ?” ሲል ጠየቀው። እርሱም፣ “እኔማ የበኵር ልጅህ ዔሳው ነኝ” አለው።
33በዚህ ጊዜ ይሥሐቅ ክፉኛ እየተንቀጠቀጠ፣ “ታዲያ ቀደም ሲል ዐድኖ ያመጣልኝ ማን ነበር? አንተ ከመምጣትህ በፊት በልቼ መረቅሁት፤ እርሱም በርግጥ የተባረከ ይሆናል” አለው።
34ዔሳው የአባቱን ቃል ሲሰማ፣ ድምፁን ከፍ በማድረግ ምርር ብሎ አለቀሰ፤ አባቱንም፣ “አባቴ ሆይ፤ እኔንም ደግሞ እባክህ መርቀኝ” አለው።
35ይሥሐቅም፣ “ወንድምህ መጥቶ አታልሎኝ ምርቃትህን ወስዶብሃል” አለው።
36ዔሳውም፣ “ይህ ሰው ያዕቆብ መባሉ ትክክል አይደለምን? እኔን ሲያታልለኝ ይህ ሁለተኛ ጊዜው ነው፤ መጀመሪያ ብኵርናዬን ወሰደብኝ፤ አሁን ደግሞ ምርቃቴን ቀማኝ” አለ። ቀጥሎም፣ “ታዲያ ለእኔ ያስቀረኸው ምንም ምርቃት የለም?” ብሎ ጠየቀ።
37ይሥሐቅም ለዔሳው፣ “በአንተ ላይ የበላይነት እንዲኖረው፣ ወንድሞቹ ሁሉ አገልጋዮቹ እንዲሆኑ፣ እህሉ፣ የወይን ጠጁም የተትረፈረፈ እንዲሆንለት መርቄዋለሁ። ታዲያ ልጄ፣ ለአንተ ምን ላደርግልህ እችላለሁ?” ሲል መለሰለት።
38ዔሳውም አባቱን፣ “አባቴ ሆይ፤ ምርቃትህ ይህችው ብቻ ናትን? እባክህ አባቴ፣ እኔንም መርቀኝ” አለው፤ ድምፁንም ከፍ አድርጎ አለቀሰ።
39አባቱ ይሥሐቅም እንዲህ ሲል መለሰለት፤
“መኖሪያህ
ከምድር በረከት፣
ከላይም ከሰማይ ጠል የራቀ ይሆናል፤
40በሰይፍ ትኖራለህ፤
የወንድምህም አገልጋይ ትሆናለህ።
አምርረህ በተነሣህ ጊዜ ግን፣
ቀንበሩን ከጫንቃህ ላይ፣
ወዲያ ትጥላለህ።”
ያዕቆብ ወደ ላባ ሸሸ
41አባቱ ያዕቆብን ስለ መረቀው፣ ዔሳው በያዕቆብ ላይ ቂም ያዘ፤ በልቡም፣ “ግድ የለም፤ የአባቴ መሞቻው ተቃርቧል፤ ከልቅሶው በኋላ ወንድሜን ያዕቆብን እገድላለሁ” ብሎ ዐሰበ።
42ርብቃ፣ ታላቁ ልጇ ዔሳው ያሰበው በተነገራት ጊዜ ታናሹን ልጇን ያዕቆብን አስጠርታ እንዲህ አለችው፤ “ወንድምህ ዔሳው ሊገድልህ ጊዜ እየጠበቀ ነው፤ 43አሁንም ልጄ ሆይ፤ እኔ የምልህን አድርግ፤ በካራን ምድር ወደሚኖረው ወደ ላባ ቶሎ ሽሽ። 44የወንድምህ ቍጣ እስከሚበርድ እዚያው ቈይ፤ 45ነገር ግን ቍጣው በርዶለት ያደረግህበትን ከረሳ በኋላ፣ እንድትመለስ እልክብህና ትመጣለህ። ሁለታችሁንም በአንድ ቀን ለምን ልጣ?”
46ከዚያም ርብቃ ይሥሐቅን፣ “ዔሳው ባገባቸው በኬጢያውያን ሴቶች ምክንያት መኖር አስጠልቶኛል፤ ያዕቆብም ከዚሁ አገር ከኬጢያውያን ሴቶች ሚስት የሚያገባ ከሆነ፣ ሞቴን እመርጣለሁ” አለችው።

Currently Selected:

ዘፍጥረት 27: NASV

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ