ዘፍጥረት 46

46
ያዕቆብ ወደ ግብጽ ሄደ
1እስራኤልም ጓዙን ሁሉ ጠቅልሎ ተነሣ፤ ቤርሳቤህም ሲደርስ፣ ለአባቱ ለይሥሐቅ አምላክ መሥዋዕት ሠዋ።
2እግዚአብሔርም ሌሊት በራእይ ለእስራኤል ተገልጦ “ያዕቆብ ያዕቆብ” ብሎ ጠራው።
እርሱም፣ “እነሆ፤ አለሁ” አለ።
3እግዚአብሔርም እንዲህ አለው፤ “እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ የአባትህ አምላክ ነኝ፤ ወደ ግብጽ ለመውረድ አትፍራ፤ በዚያ ታላቅ ሕዝብ አደርግሃለሁና፤ 4ዐብሬህ ወደ ግብጽ እወርዳለሁ፤ ከዚያም መልሼ አወጣሃለሁ፤ የዮሴፍ የራሱ እጆችም ዐይኖችህን ይገጥሟቸዋል።”
5ከዚህ በኋላ ያዕቆብ ከቤርሳቤህ ተነሣ፤ የእስራኤል ወንዶች ልጆችም አባታቸውን ያዕቆብን፣ ልጆቻቸውንና ሚስቶቻቸውን ፈርዖን ለያዕቆብ በላካቸው ሠረገላዎች ላይ አወጧቸው። 6ከብቶቻቸውንና በከነዓን ምድር ያፈሩትን ሀብት ንብረታቸውን ይዘው፣ ያዕቆብና ዘሮቹ በሙሉ ወደ ግብጽ ወረዱ። 7ወደ ግብጽም የወረደው፣ ወንዶች ልጆቹንና ወንዶች የልጅ ልጆቹን፣ ሴቶች ልጆቹንና ሴቶች የልጅ ልጆቹን፣ ማለትም ዘሮቹን ሁሉ ይዞ ነው።
8ወደ ግብጽ የወረዱት የእስራኤል ልጆች፣ ያዕቆብና ዘሮቹ እነዚህ ናቸው፦
የያዕቆብ የበኵር ልጅ ሮቤል።
9የሮቤል ልጆች፦
ሄኖኅ፣ ፈሉስ፣ አስሮን እና ከርሚ ናቸው።
10የስምዖን ልጆች፦
ይሙኤል፣ ያሚን፣ ኦሃድ፣ ያኪን፣ ጾሐርና ከከነዓናዊቷ ሴት የተወለደው ሳኡል ናቸው።
11የሌዊ ልጆች፦
ጌርሶን፣ ቀዓት እና ሜራሪ ናቸው።
12የይሁዳ ልጆች፦
ዔር፣ አውናን፣ ሴሎም፣ ፋሬስ እና ዛራ ናቸው። ነገር ግን ዔርና አውናን በከነዓን ምድር ሞቱ።
የፋሬስ ልጆች፦
ኤስሮምና ሐሙል ናቸው።
13የይሳኮር ልጆች፦
ቶላ፣ ፉዋ፣#46፥13 ከኦሪተ ሳምራውያንና ከሱርስቱ ጋራ ተመሳሳይ ሲሆን (1ዜና 7፥1 ይመ) የማሶሬቲክ ጽሑፍ ግን ፋቫ ይለዋል። ዮብና ሺምሮን ናቸው፤
14የዛብሎን ልጆች፦
ሴሬድ፣ ኤሎንና ያሕልኤል ናቸው፤
15እነዚህ ወንዶች ልጆች ያዕቆብ በሰሜን ምዕራብ መስጴጦምያ ሳለ፣ ልያ የወለደችለት ናቸው። ሴቷን ዲናን ጨምሮ፣ የወንዶችና የሴቶች ልጆቹ ቍጥር ሠላሳ ሦስት ነው።
16የጋድ ልጆች፦
ጽፎን፣#46፥16 ከኦሪተ ሳምራውያንና ከሰብዓ ሊቃናት ጋራ ተመሳሳይ ሲሆን (ዘኍ 26፥15 ይመ) የማሶሬቲክ ጽሑፍ ግን ጸሬን ይለዋል። ሐጊ፣ ሹኒ፣ ኤስቦን፣ ዔሪ፣ አሮዲና አርኤሊ ናቸው፤
17የአሴር ልጆች፦
ዪምና፣ የሱዋ፣ የሱዊና በሪዓ ናቸው፤ እኅታቸውም ሤራሕ ናት፤
የበሪዓ ልጆች፦
ሔቤርና መልኪኤል ናቸው፤
18እነዚህ ዐሥራ ስድስት ልጆች ሁሉ፣ ላባ ለልጁ ለልያ ከሰጣት ከዘለፋ ላይ ያዕቆብ የወለዳቸው ናቸው።
19የያዕቆብ ሚስት የራሔል ልጆች፦
ዮሴፍና ብንያም ናቸው፤
20በግብጽም የሄልዮቱ#46፥20 ሆሲዮፓሊስን ያመለክታል። ከተማ ካህን የጶጥፌራ ልጅ አስናት፣ ምናሴንና ኤፍሬምን ለዮሴፍ ወለደችለት።
21የብንያም ልጆች፦
ቤላ፣ ቤኬር፣ አስቤል፣ ጌራ፣ ናዕማን፣ አኪ፣ ሮስ፣ ማንፌን ሑፊምና አርድ ናቸው።
22እነዚህ ዐሥራ አራቱ፣ ራሔል ለያዕቆብ የወለደችለት ልጆችና የልጅ ልጆች ናቸው።
23የዳን ልጅ፦
ሑሺም ነው፤
24የንፍታሌም ልጆች፦
ያሕጽኤል፣ ጉኒ፣ ዬጽርና ሺሌም ናቸው።
25እነዚህ ሰባቱ ልጆች ሁሉ ላባ ለልጁ ለራሔል ከሰጣት ከባላ ላይ ያዕቆብ የወለዳቸው ናቸው።
26ከያዕቆብ ጋራ ወደ ግብጽ የሄዱት የገዛ ዘሮቹ ብዛት ስድሳ ስድስት ሲሆን ይህ ቍጥር ግን የልጆቹን ሚስቶች አይጨምርም። 27ዮሴፍ በግብጽ የወለዳቸውን ሁለት ልጆች#46፥27 ከዕብራይስጡ ጋራ ተመሳሳይ ሲሆን ሰብዓ ሊቃናት ግን ዘጠኙ ልጆች ይለዋል። ጨምሮ፣ ወደ ግብጽ የወረደው የያዕቆብ ቤተ ሰብ ቍጥር ሰባ#46፥27 ከዕብራይስጡ ጋራ ተመሳሳይ ሲሆን (ዘፀ 1፥5 እና ማብ ይመ)፣ ሰብዓ ሊቃናት ግን (ሐሥ 7፥14 ይመ) ሰባ ዐምስት ይለዋል። ነበር።
28ያዕቆብም ወደ ጌሤም ለመሄድ መመሪያን ይቀበል ዘንድ ይሁዳን አስቀድሞ ወደ ዮሴፍ ላከው። እነርሱም ጌሤም ሲደርሱ፣ 29ዮሴፍ ሠረገላውን አዘጋጅቶ፤ አባቱን እስራኤልን ለመቀበል ወደ ጌሤም አመራ። ዮሴፍ አባቱ ዘንድ እንደ ደረሰ፣ ዐንገቱ ላይ#46፥29 ዕብራይስጡ በላዩ ላይ ይለዋል። ተጠምጥሞ ለረዥም ጊዜ አለቀሰ።
30እስራኤልም ዮሴፍን፣ “በሕይወት መኖርህን ስላየሁ፣ ከእንግዲህ ብሞትም አይቈጨኝ” አለው።
31ከዚህ በኋላ ዮሴፍ ወንድሞቹንና የአባቱን ቤተ ሰዎች እንዲህ አላቸው፤ “ወደ ፈርዖን ወጥቼ አናግረዋለሁ፤ እንዲህም እለዋለሁ፣ ‘በከነዓን ምድር የሚኖሩት ወንድሞቼና የአባቴ ቤተ ሰዎች ወደ እኔ መጥተዋል። 32ሰዎቹ ከብት የሚጠብቁ ስለ ሆኑ እረኞች ናቸው፤ ሲመጡም በጎቻቸውን፣ ፍየሎቻቸውንና ከብቶቻቸውን እንዲሁም ያላቸውን ሁሉ ይዘው መጥተዋል።’ 33ፈርዖን አስጠርቷችሁ፣ ‘ሥራችሁ ምንድን ነው?’ ብሎ ቢጠይቃችሁ፣ 34እናንተ፣ ‘እኛ ባሮችህ ሥራችን ከልጅነታችን ጀምሮ ልክ እንደ አባቶቻችን ከብት ማርባት ነው’ ብላችሁ መልሱለት። ከዚያም ግብጻውያን ከብት አርቢዎችን እንደ ጸያፍ ስለሚቈጥሩ፣ በጌሤም ምድር እንድትኖሩ ይፈቅድላችኋል።”

Currently Selected:

ዘፍጥረት 46: NASV

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ