የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኢሳይያስ 19

19
ስለ ግብጽ የተነገረ ትንቢት
1ስለ ግብጽ የተነገረ ንግር፤
እነሆ፤ እግዚአብሔር በፈጣን ደመና ላይ ተቀምጦ
ወደ ግብጽ ይመጣል፤
የግብጽ ጣዖቶች በፊቱ ይርዳሉ፤
የግብጻውያንም ልብ በውስጣቸው ይቀልጣል።
2“ግብጻዊውን በግብጻዊው ላይ አስነሣለሁ፤
ወንድም ወንድሙን፣
ባልንጀራ ባልንጀራውን፣
ከተማም ከተማን፣
መንግሥትም መንግሥትን ይወጋል።
3የግብጻውያን ልብ ይሰለባል፤
ዕቅዳቸውንም መና አስቀራለሁ፤
እነርሱም ጣዖታትንና የሙታንን መናፍስት፣
መናፍስት ጠሪዎችንና ጠንቋዮችን ምክር ይጠይቃሉ።
4ግብጻውያንን አሳልፌ
ለጨካኝ ጌታ ክንድ እሰጣቸዋለሁ፤
አስፈሪ ንጉሥም ይገዛቸዋል”
ይላል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር
5የአባይ ወንዝ ይቀንሳል፤
ውሃውም እየጐደለ ይሄዳል።
6መስኖዎቹ ይከረፋሉ፤
የግብጽ ጅረቶች ይጐድላሉ፤ ይጠፋሉም።
ደንገሉና ቄጠማውም ይጠወልጋል፤
7እንዲሁም በአባይ ዳር፣
በወንዙ መፋሰሻ ላይ ያሉት ተክሎች ይጠወልጋሉ።
በአባይ ዳር የተዘራው ዕርሻ ሁሉ፣
በነፋስ ይወሰዳል፤ ምንም አይቀርም።
8ዓሣ አጥማጆች ያዝናሉ፤
በአባይ ወንዝ ላይ መንጠቋቸውን የሚወረውሩ ሁሉ ያለቅሳሉ፤
በውሃ ላይ መረባቸውን የሚጥሉ ሁሉ፣
ጕልበታቸው ይዝላል።
9የተነደፈ የተልባ እግር የሚፈትሉ፣
የተባዘተ ጥጥ የሚሠሩ ሸማኔዎችም ተስፋ ይቈርጣሉ።
10ልብስ ሠሪዎች ያዝናሉ፤
ደመወዝተኞችም ልባቸው ይሰበራል።
11የጣኔዎስ አለቆች በጣም ቂሎች ናቸው፤
የፈርዖን ጠቢባን ምክራቸው የማይረባ ነው፤
ፈርዖንን፣ “እኔ ከጥበበኞች አንዱ ነኝ፤
የጥንት ነገሥታትም ደቀ መዝሙር ነኝ”
እንዴት ትሉታላችሁ?
12የእናንተ ጠቢባን አሁን የት አሉ?
የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር
በግብጽ ላይ ያሰበውን ነገር፣
እስኪ ያሳዩአችሁ፤ ያሳውቋችሁም።
13የጣኔዎስ አለቆች ተሞኝተዋል፤
የሜምፊስ ሹማምት ተታልለዋል፤
የሕዝቧ ዋና ዋናዎች፣
ግብጽን አስተዋታል።
14 እግዚአብሔር የድንዛዜን መንፈስ አፍስሶባቸዋል፤
ሰካራም በትፋቱ ዙሪያ እንደሚንገዳገድ፣
ግብጽንም በምታደርገው ነገር ሁሉ
እንድትንገዳገድ አደረጓት።
15ራስም ይሁን ጅራት፣ የዘንባባ ዝንጣፊም ይሁን ደንገል፣
ለግብጽ የሚያደርጉላት አንዳች ነገር የለም።
16በዚያ ቀን ግብጻውያን እንደ ሴት ይሆናሉ፤ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር በእነርሱ ላይ በሚያንቀሳቅሰው ክንዱ ፊት ይፈራሉ፤ ይንቀጠቀጣሉም። 17የይሁዳ ምድር በግብጽ ላይ ሽብር ትነዛለች፤ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር በእነርሱ ላይ ካቀደው የተነሣ፣ ስለ ይሁዳ ወሬ የሰማ ሁሉ ይሸበራል።
18በዚያ ቀን ዐምስት የግብጽ ከተሞች በከነዓን ቋንቋ ይናገራሉ፤ የሰራዊት ጌታ የእግዚአብሔርም ወገን ለመሆን ቃል ኪዳን ይገባሉ፤ ከእነዚህም ከተሞች አንዲቱ የጥፋት ከተማ ተብላ ትጠራለች።
19በዚያ ቀን በግብጽ ምድር መካከል ለእግዚአብሔር መሠዊያ ይሠራል፤ በድንበሯም ላይ ለእግዚአብሔር ዐምድ ይቆማል። 20ይህም በግብጽ ምድር ለሰራዊት ጌታ ለእግዚአብሔር ምልክትና ምስክር ይሆናል፤ ከሚያስጨንቋቸውም የተነሣ ወደ እግዚአብሔር ሲጮኹ፣ አዳኝና ታዳጊ ይልክላቸዋል፤ እርሱም ያድናቸዋል። 21እግዚአብሔር ራሱን ለግብጻውያን ይገልጣል፤ እነርሱም በዚያ ቀን እግዚአብሔርን ያውቁታል፤ በመሥዋዕትና በእህል ቍርባንም ያመልኩታል። ለእግዚአብሔር ስእለት ይሳላሉ፤ የተሳሉትንም ይፈጽሙታል። 22እግዚአብሔር ግብጽን በመቅሠፍት ይመታታል፤ መትቶም፤ ይፈውሳቸዋል። እነርሱም ወደ እግዚአብሔር ይመለሳሉ፤ እርሱም ልመናቸውን ሰምቶ ይፈውሳቸዋል።
23በዚያ ቀን ከግብጽ ወደ አሦር አውራ መንገድ ይዘረጋል፤ አሦራውያን ወደ ግብጽ፣ ግብጻውያንም ወደ አሦር ይሄዳሉ፤ ግብጻውያንና አሦራውያን በአንድነት ያመልካሉ። 24በዚያ ቀን እስራኤል፣ ከግብጽና ከአሦር ጋራ የምድር በረከት ለመሆን በሦስተኛነት ትቈጠራለች። 25የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔርም፣ “ሕዝቤ ግብጽ፣ የእጄ ሥራ አሦር፣ ርስቴም እስራኤል የተባረኩ ይሁኑ” ብሎ ይባርካቸዋል።

Currently Selected:

ኢሳይያስ 19: NASV

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ