ኢሳይያስ 44
44
የተመረጠው እስራኤል
1“ነገር ግን አሁንም ባሪያዬ ያዕቆብ፣
የመረጥሁህ እስራኤል ሆይ፣ ስማ፤
2የፈጠረህ፣ በማሕፀን የሠራህ፣
የሚረዳህ፣
እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤
ባሪያዬ ያዕቆብ፣
የመረጥሁህ ይሹሩን#44፥2 ይሽሩን ማለት ቀና የሆነው ማለት ሲሆን እስራኤልን የሚያመላክት ነው። ሆይ፣ አትፍራ።
3በተጠማ ምድር ላይ ውሃ፤
በደረቅ መሬት ላይ ወንዞችን አፈስሳለሁና፤
መንፈሴን በዘርህ፣
በረከቴንም በልጅ ልጅህ ላይ አወርዳለሁ።
4እነርሱም በለመለመ መስክ ላይ እንደ ሣር፣
በወንዝ ዳር እንደ አኻያ ዛፍ ይበቅላሉ።
5አንዱ፣ ‘እኔ የእግዚአብሔር ነኝ’ ይላል፤
ሌላው ራሱን በያዕቆብ ስም ይጠራል፤
ሌላው ደግሞ በእጁ ላይ ‘የእግዚአብሔር ነኝ’ ብሎ ይጽፋል፤
ራሱን በእስራኤል ስም ይጠራል።
አምላክ እግዚአብሔር ብቻ ነው
6“የእስራኤል ንጉሥና ቤዛ እግዚአብሔር፣
የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤
የፊተኛውም እኔ ነኝ፤ የኋለኛውም እኔ ነኝ፤
ከእኔ በቀር ሌላ አምላክ የለም።
7እስኪ እንደ እኔ ማን አለ? ይናገር፤
ሕዝቤን ከጥንት ስመሠርት ምን እንደ ነበረ፣
ገና ወደ ፊት ምን እንደሚሆን፣
ይናገር፤ በፊቴ ያስረዳ፤
ስለሚመጣውም ነገር አስቀድሞ ይናገር።
8አትፍሩ፤ አትደንግጡ፤
ይህን አልነገርኋችሁምን? ቀድሞስ አላሳወቅኋችሁምን?
ለዚህ እናንተ ምስክሮቼ ናችሁ። ከእኔ በቀር ሌላ አምላክ አለን? ፈጽሞ!
ወይም ሌላ ዐለት አለ? የለም! ማንንም አላውቅም።”
9ጣዖት የሚሠሩ ሁሉ ከንቱዎች፣
የሚሠሩባቸውም ነገሮች ዋጋ ቢስ ናቸው፤
የሚናገሩላቸው ዕውሮች ናቸው፤
ዕውቀት የላቸውም ያፍራሉም።
10ለምንም የማይጠቅመውን አምላክ የሚቀርጽ፣
ጣዖትን የሚያበጅስ ማነው?
11የእጅ ጥበብ ባለሙያው ሰው እንጂ ሌላ አይደለም፤
እርሱና መሰሎቹም ያፍራሉ፤
ሁሉም ተሰብስበው በአንድ ላይ ይቁሙ፤
ይደነግጣሉ፤ ይዋረዳሉም።
12የብረት የእጅ ጥበብ ባለሙያ መሥሪያን ይይዛል፤
በከሰል ፍም ላይ ይሠራዋል፤
ጣዖትን በመዶሻ ቅርጽ ይሰጠዋል፤
በክንዱም ኀይል ያበጀዋል።
ከዚያም ይራባል፤ ጕልበት ያጣል፤
ውሃ ይጠማል፤ ይደክማል።
13የእጅ ጥበብ ባለሙያ በገመድ ይለካል፤
በጠመኔ ንድፍ ያወጣል፤
በመሮ ይቀርጸዋል፤
በጸርከል ምልክት ያደርግበታል።
በሰው አምሳል ይቀርጸዋል፤
የሰውንም ውበት ያለብሰዋል፤
በማምለኪያም ስፍራ ያስቀምጠዋል።
14ዝግባ ይቈርጣል፤
ሾላ ወይም ወርካ ይመርጣል፤
በደን ውስጥ ካሉት ዛፎች ጋራ እንዲያድግ ይተወዋል፤
ወይም ጥድን ይተክላል፤ ያንም ዝናም ያሳድገዋል።
15ሰው ለማገዶ ይጠቀምበታል፤
ከዚያም ጥቂት ወስዶ በማንደድ ይሞቀዋል፤
እንጀራም ይጋግርበታል።
ከዚሁ ጠርቦ አምላክ ያበጃል፤
ያመልከዋል፤
ጣዖትን ይሠራል፤ ወድቆም ይሰግድለታል።
16ግማሹን ዕንጨት ያነድደዋል፤
በላዩ ምግቡን ያበስልበታል፤
ሥጋ ጠብሶበት እስኪጠግብ ይበላል፤
እሳቱን እየሞቀ እንዲህ ይላል፤
“ዕሠይ ሞቀኝ፤ እሳቱም ይታየኛል።”
17በቀረው ዕንጨት የጣዖት አምላኩን ይሠራበታል፤
ወድቆ ይሰግድለታል፤ ያመልከዋል፤
ወደ እርሱም እየጸለየ፣
“አንተ አምላኬ ነህ፤ አድነኝ!” ይላል።
18ምንም አያውቁም፤ አያስተውሉም፤
እንዳያዩ ዐይናቸው ተሸፍኗል፤
እንዳያስተውሉ ልባቸው ተዘግቷል።
19ማንም ቆም ብሎ አላሰበም፤
ዕውቀት ወይም ማስተዋል ስለሌለው እንዲህ ማለት አልቻለም፤
“ግማሹን በእሳት አቃጥዬዋለሁ፤
በፍሙ እንጀራ ጋግሬበታለሁ፤
ሥጋ ጠብሼበት በልቻለሁ፤
ታዲያ፣ በቀረው እንዴት ጸያፍ ነገር እሠራለሁ?
ለግንድስ መስገድ ይገባኛልን?”
20ዐመድ ይቅማል፤ ተታላይ ልብ አስቶታል፤
ራሱን ለማዳን አይችልም፤
“ይህ በቀኝ እጄ ያለው ነገር ሐሰት አይደለምን?”
ለማለት አልቻለም።
21“እስራኤል ሆይ፤ ባሪያዬ ነህና፣
ያዕቆብ ሆይ፤ ይህን ዐስብ።
እኔ ሠርቼሃለሁ፤ አንተም ባሪያዬ ነህ፤
እስራኤል ሆይ፤ አልረሳህም።
22መተላለፍህን እንደ ደመና፣
ኀጢአትህን እንደ ማለዳ ጭጋግ ጠርጌ አስወግጃለሁ፤
ተቤዥቼሃለሁና
ወደ እኔ ተመለስ።”
23ሰማያት ሆይ፤ እግዚአብሔር ይህን አድርጓልና ዘምሩ፤
የምድር ጥልቆች ሆይ፤ በደስታ ጩኹ።
እናንተ ተራሮች፣
እናንተ ደኖችና ዛፎቻችሁ ሁሉ እልል በሉ፤
እግዚአብሔር ያዕቆብን ተቤዥቷል፣
በእስራኤልም ክብሩን ገልጧልና።
ኢየሩሳሌም የሰው መኖሪያ ትሆናለች
24“ከማሕፀን የሠራህ፣ የተቤዠህም፣
እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤
“ሁሉን ነገር የፈጠርሁ፣
ብቻዬን ሰማያትን የዘረጋሁ፣
ምድርን ያንጣለልሁ፣
እኔ እግዚአብሔር ነኝ።
25የሐሰተኞችን ነቢያት ምልክቶች አከሽፋለሁ፤
ሟርተኞችን አነሆልላለሁ፤
የጥበበኞችን ጥበብ እገለባብጣለሁ፤
ዕውቀታቸውንም ከንቱ አደርጋለሁ።
26የባሪያዎቼን ቃል እፈጽማለሁ፤
የመልእክተኞቼን ምክር አጸናለሁ።
“ኢየሩሳሌምን ‘የሰው መኖሪያ ትሆኛለሽ፣’
የይሁዳ ከተሞችንም፣ ‘ይታነጻሉ’፣
ፍርስራሻቸውን፣ ‘አድሳለሁ’ እላለሁ።
27ጥልቁን ውሃ፣ ‘ደረቅ ሁን፤
ወንዞችህን አደርቃለሁ’ እላለሁ።
28ቂሮስንም፣ ‘እርሱ እረኛዬ ነው፤
ፈቃዴን ሁሉ ይፈጽማል፤
ኢየሩሳሌምም፣ “እንደ ገና ትሠራ፣”
ቤተ መቅደሱም፣ “መሠረቱ ይጣል” ይላል’ እላለሁ።”
Currently Selected:
ኢሳይያስ 44: NASV
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.