የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኢሳይያስ 45

45
1“ለቀባሁት፣ ቀኝ እጁን ለያዝሁት፣
ነገሥታትን ትጥቅ አስፈታ ዘንድ፣
ሕዝብን ሁሉ ላስገዛለት፣
ደጆች እንዳይዘጉ፣
በሮቹን በፊቱ ለምከፍትለት፣
ለቂሮስ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤
2‘በፊትህ እሄዳለሁ፤
ተራሮችን#45፥2 የሙት ባሕር ጥቅልሎችና የሰብዓ ሊቃናት ትርጕም ከዚህ ጋራ ይስማማል፤ በማሶሬቱ ቅጅ ግን የቃሉ ትርጕም አይታወቅም። እደለድላለሁ፤
የናስ በሮችን እሰብራለሁ፤
የብረት መወርወሪያዎችንም እቈርጣለሁ።
3በስምህ የምጠራህ የእስራኤል አምላክ፣
እኔ እግዚአብሔር መሆኔን ታውቅ ዘንድ፣
በተሰወረ ስፍራ የተከማቸውን ሀብት፣
በጨለማም ያለውን ንብረት እሰጥሃለሁ።
4ስለ ባሪያዬ ስለ ያዕቆብ፣
ስለ መረጥሁት ስለ እስራኤል፣
አንተ ባታውቀኝ እንኳ፣
በስምህ ጠርቼሃለሁ፤
የክብርም ስም ሰጥቼሃለሁ።
5እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ ከእኔ ሌላ ማንም የለም፤
ከእኔ በቀር አምላክ የለም።
አንተ ባታውቀኝም እንኳ፣
እኔ አበረታሃለሁ።
6ይኸውም ሰዎች ከፀሓይ መውጫ፣
እስከ መጥለቂያው፣
ከእኔ በቀር ሌላ እንደሌለ እንዲያውቁ ነው፤
እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ ከእኔ ሌላ ማንም የለም።
7እኔ ብርሃንን ሠራሁ፤ ጨለማንም ፈጠርሁ፤
አበለጽጋለሁ፤ አደኸያለሁ፤
ይህን ሁሉ የማደርግ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።’
8“እናንተ ሰማያት፣ ጽድቅን ከላይ አዝንቡ፤
ደመናትም ወደ ታች አንጠብጥቡ፤
ምድር ትከፈት፤
ድነት ይብቀል፤
ጽድቅም ዐብሮት ይደግ፤
እኔ እግዚአብሔር ፈጥሬዋለሁ።
9“ከዐፈር ሸክላዎች መካከል፣
ከሠሪው ጋራ ክርክር ለሚገጥም ወዮለት!
ጭቃ፣ ሸክላ ሠሪውን፣
‘ምን እየሠራህ ነው?’ ይለዋልን?
የምትሠራውስ ሥራ፣
‘እጅ የለህም’ ይልሃልን?
10አባቱን፣
‘የወለድኸው ምንድን ነው?’ ለሚል፣
እናቱንም፣
‘ምን ወለድሽ?’ ለሚል ወዮለት!
11“የእስራኤል ቅዱስ፣ ሠሪውም የሆነ እግዚአብሔር
ስለሚመጡ ነገሮች እንዲህ ይላል፤
‘ስለ ልጆቼ ትጠይቁኛላችሁን?
ስለ እጆቼስ ሥራ ታዝዙኛላችሁን?
12ምድርን የሠራሁ እኔ ነኝ፤
ሰውንም በላይዋ ፈጥሬአለሁ፤
እጆቼ ሰማያትን ዘርግተዋል፤
የሰማይንም ሰራዊት አሰማርቻለሁ።
13ቂሮስን#45፥13 ዕብራይስጡ፣ እርሱን ይላል። በጽድቅ አስነሥቻለሁ፤
መንገዱን ሁሉ አስተካክዬለታለሁ፤
ከተማዬን እንደ ገና ይሠራታል፤
ምርኮኞቼን ያለ ክፍያ ወይም ያለ ዋጋ፣
ነጻ ያወጣል፤’
ይላል የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር።”
14 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤
“የግብጽ ሀብትና የኢትዮጵያ#45፥14 የላይኛውን የአባይ ወንዝ አካባቢን የሚያመላክት ነው። ንግድ፣
ቁመተ ረዣዥሞቹ የሳባ ሰዎች፣
ወደ አንተ ይመጣሉ፤
የአንተ ይሆናሉ፤
ከኋላ ይከተሉሃል፤
በሰንሰለትም ታስረው ወደ አንተ በመምጣት፣
በፊትህ እየሰገዱ፣
‘በእውነት እግዚአብሔር ከአንተ ጋራ ነው፤
ከርሱም በቀር ሌላ አምላክ የለም’ ብለው ይለምኑሃል።”
15አዳኙ የእስራኤል አምላክ ሆይ፤
አንተ በእውነት ራስህን የምትሰውር አምላክ ነህ።
16የእጅ ጥበብ ባለሙያዎች ሁሉ ያፍራሉ፤ ይቀልላሉ፤
በአንድነት ይዋረዳሉ።
17እስራኤል ግን በእግዚአብሔር
በዘላለም ድነት ይድናል፤
እናንተም ለዘላለም፣
አታፍሩም፤ አትዋረዱም።
18ሰማያትን የፈጠረ፣
እርሱ እግዚአብሔር ነው፤
ምድርን ያበጃት፣ የሠራት፣
የመሠረታት፣
የሰው መኖሪያ እንጂ፣
ባዶ እንድትሆን ያልፈጠራት፣
እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፤
“እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤
ከእኔም በቀር ሌላ የለም።
19በጨለማ ምድር፣
በምስጢር አልተናገርሁም፤
ለያዕቆብም ዘር፣
‘በከንቱ ፈልጉኝ’ አላልሁም።
እኔ እግዚአብሔር ጽድቅን እናገራለሁ፤
ትክክለኛውንም ነገር ዐውጃለሁ።
20“በአንድነት ተሰብሰቡ፤ ቅረቡም፤
እናንተ ከአሕዛብ የኰበለላችሁ፣ ኑ።
የዕንጨት ጣዖት የሚሸከሙ፣
ማዳን ወደማይችል አምላክ የሚጸልዩ፣ ዕውቀት የላቸውም።
21ጕዳያችሁን ተናገሩ፤ አቅርቡ፤
ተሰብስበውም ይማከሩ።
ይህን አስቀድሞ ማን ዐወጀ?
ከጥንትስ ማን ተናገረ?
እኔ እግዚአብሔር አይደለሁምን?
ጻድቅና አዳኝ የሆነ አምላክ፣
ከእኔ በቀር ማንም የለም፤
ከእኔ ሌላ አምላክ የለም።
22“እናንተ የምድር ዳርቻ ሁሉ፣
እኔ አምላክ ነኝ፤ ከእኔም በቀር ሌላ የለምና፤
ትድኑ ዘንድ ወደ እኔ ተመለሱ።
23ጕልበት ሁሉ ለእኔ ይንበረከካል፤
ምላስም ሁሉ በእኔ ይምላል፤
ብዬ በራሴ ምያለሁ፤
የማይታጠፍ ቃል፣
ከአፌ በጽድቅ ወጥቷል።
24ስለ እኔም ሲናገሩ፣ ‘ጽድቅና ኀይል፣
እግዚአብሔር ብቻ ነው’ ይላሉ።”
በርሱ ላይ በቍጣ የተነሡ ሁሉ፣
ወደ እርሱ መጥተው ያፍራሉ።
25ነገር ግን የእስራኤል ዘር ሁሉ፣
እግዚአብሔር ይጸድቃሉ፤
ሞገስንም ያገኛሉ።

Currently Selected:

ኢሳይያስ 45: NASV

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ