ኢያሱ 14
14
ከዮርዳኖስ በስተ ምዕራብ ስላለው ምድር አከፋፈል
1ካህኑ አልዓዛር፣ የነዌ ልጅ ኢያሱና የእስራኤል የየነገዱ ጐሣ አባቶች የደለደሉላቸው፣ እስራኤላውያንም በከነዓን ምድር የወረሱት ርስት ይህ ነው። 2ርስታቸውም እግዚአብሔር በሙሴ አማካይነት በሰጠው ትእዛዝ መሠረት፣ ለዘጠኙ ነገድና ለእኩሌታው ነገድ በዕጣ ተከፋፈለ። 3ሙሴ ለሁለቱ ነገድና ለእኩሌታው፣ የዮርዳኖስን ምሥራቅ ክፍል ርስት አድርጎ ሰጣቸው፤ ሌዋውያኑ ግን ዐብረዋቸው እንዲካፈሉ አላደረገም፤ 4የዮሴፍ ልጆች ምናሴና ኤፍሬም ሁለት ነገዶች ሆነው ነበርና፤ ለሌዋውያኑ ግን ከሚኖሩባቸው ከተሞች እንዲሁም ለበግ፣ ለፍየልና ለከብት መንጎቻቸው መሰማሪያ እንዲሆን ዐብሮ የተከለለላቸውን ምድር ብቻ እንጂ ሌላ አልሰጣቸውም። 5ስለዚህ እስራኤላውያን እግዚአብሔር ሙሴን ባዘዘው መሠረት፣ ምድሪቱን ተካፈሉ።
ኬብሮን ለካሌብ ተሰጠች
6የይሁዳም ሰዎች በጌልገላ ወደ ኢያሱ ቀረቡ፤ ከዚያም የቄኔዛዊው የዮፎኒ ልጅ ካሌብ እንዲህ አለው፤ “እግዚአብሔር በቃዴስ በርኔ ስለ አንተና ስለ እኔ፣ የእግዚአብሔር ሰው ለሆነው ለሙሴ የተናገረውን ታውቃለህ። 7የእግዚአብሔር ባሪያ ሙሴ ምድሪቱን እንድሰልል ከቃዴስ በርኔ በላከኝ ጊዜ የአርባ ዓመት ሰው ነበርሁ፤ እኔም ትክክለኛውን ማስረጃ ይዤለት መጣሁ፤ 8ዐብረውኝ ወደዚያ የወጡት ወንድሞቼ ግን፣ የሕዝቡ ልብ በፍርሀት እንዲቀልጥ አደረጉ፤ ሆኖም እኔ አምላኬን እግዚአብሔርን በፍጹም ልቤ ተከተልሁት። 9ስለዚህም ሙሴ በዚያች ዕለት፣ ‘አምላኬን እግዚአብሔርን በፍጹም ልብህ ተከትለኸዋልና እግርህ የረገጣት ምድር ለዘላለም የአንተና የዘርህ ርስት ትሆናለች’#14፥9 ዘዳ 1፥36 ይመ። ብሎ ማለልኝ።
10“አሁንም እነሆ፤ ልክ እግዚአብሔር እንዳለው ይህን ለሙሴ ከተናገረበት ጊዜ አንሥቶ እስራኤል በምድረ በዳ ሲንከራተት እኔን አርባ ዐምስት ዓመት በሕይወት ጠብቆ አኑሮኛል፤ ይኸው ዛሬ ሰማንያ ዐምስት ዓመት ሆነኝ። 11ሙሴ በላከኝ ጊዜ የነበረኝ ብርታት ዛሬም ዐብሮኝ አለ፤ ልክ እንደዚያን ጊዜ ሁሉ አሁንም ወደ ጦርነት ለመሄድ፣ ለመውጣትም ለመግባትም ኀይሉም ብርታቱም አለኝ። 12አሁንም እግዚአብሔር በዚያች ዕለት ቃል የገባልኝን ይህችን ኰረብታማ አገር ሰጠኝ። ዔናቃውያን በዚያ እንደ ነበሩና ከተሞቻቸውም ታላላቅና የተመሸጉ እንደ ሆኑ ያን ጊዜ አንተው ራስህ ሰምተሃል፤ ሆኖም ልክ እርሱ እንዳለው በእግዚአብሔር ርዳታ አሳድጄ አወጣቸዋለሁ።”
13ከዚያም ኢያሱ የዮፎኒን ልጅ ካሌብን ባረከው፤ ኬብሮንንም ርስት አድርጎ ሰጠው። 14ስለዚህም ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ኬብሮን የቄኔዛዊው የዮፎኒ ልጅ የካሌብ ርስት ሆነች፤ የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን በፍጹም ልቡ ተከትሏልና። 15ኬብሮን ቀድሞ ከዔናቃውያን ሁሉ ታላቅ በሆነው ሰው በአርባቅ ስም ቂርያት አርባቅ ተብላ ትጠራ ነበር።
ከዚያም ምድሪቱ ከጦርነት ዐረፈች።
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.