ኢያሱ 15
15
ለይሁዳ ነገድ የተመደበው ድርሻ
15፥15-19 ተጓ ምብ – መሳ 1፥11-15
1ለይሁዳ ነገድ በየጐሣቸው በዕጣ የተመደበው ድርሻ እስከ ኤዶም ምድር የሚወርድ ሲሆን፣ በስተ ደቡብ መጨረሻ እስከ ጺን ምድረ በዳ ድረስ ይዘልቃል።
2የደቡብ ወሰናቸው፣ ከጨው ባሕር#15፥2 በዚህና በቍጥር 5 ላይ የሙት ባሕር ማለት ነው። ደቡባዊ ጫፍ ካለው የባሕር ወሽመጥ ይነሣል፤ 3ከዚያም የአቅረቢምን መተላለፊያ በማቋረጥ በጺን በኩል እስከ ቃዴስ በርኔ ደቡባዊ ክፍል ይደርሳል፤ ደግሞም ሐጽሮንን ዐልፎ ወደ አዳር ይወጣና ወደ ቀርቃ ይታጠፋል፤ 4በዓጽሞን በኩል አድርጎም ወደ ግብጽ ደረቅ ወንዝ ይገባና መቆሚያው ባሕሩ ይሆናል። እንግዲህ በደቡብ በኩል ያለው ወሰናቸው#15፥4 ዕብራይስጡ ወስናችሁ ይላል። ይህ ነው።
5በምሥራቅ በኩል ያለው ወሰናቸው ደግሞ የጨው ባሕር ሲሆን፣ ይህም የዮርዳኖስ ወንዝ እስከሚሠርግበት ይደርሳል።
በሰሜን በኩል ያለው ወሰንም የዮርዳኖስ ወንዝ ከሚሠርግበት የባሕር ወሽመጥ ይነሣና 6ሽቅብ ወደ ቤትሖግላ ይወጣል፤ ከዚያም በሰሜናዊው ቤትዓረባ በኩል አድርጎ የሮቤል ልጅ የቦሀን ድንጋይ እስካለበት ይደርሳል። 7ከዚያም ድንበሩ ከአኮር ሸለቆ ወደ ዳቤር ይወጣና ከወንዙ በስተ ደቡብ ባለው በአዱሚም መተላለፊያ ፊት ለፊት አድርጎ በስተሰሜን ወደ ጌልገላ ይታጠፋል፤ በዓይንሳሚስ ምንጭ በኩል ዐልፎም ወደ ዓይንሮጌል ይወጣል። 8እንደዚሁም የሄኖምን ልጅ ሸለቆ ዐልፎ ይሄድና የኢያቡሳውያን ከተማ እስከ ሆነችው እስከ ኢየሩሳሌም ደቡባዊ ተረተር በመዝለቅ፣ በራፋይም ሸለቆ ሰሜን ጫፍ በኩል አድርጎ ከሄኖም ሸለቆ በስተ ምዕራብ ካለው ኰረብታ ዐናት ላይ ይደርሳል። 9ከዚያም በመቀጠል ከተራራው ዐናት ተነሥቶ ወደ ኔፍቶ ምንጮች በማምራት፣ በዔፍሮን ተራራ ላይ ያሉትን ከተሞች ዐልፎ ይወጣና ቂርያትይዓይሪም ተብሎ ወደሚጠራው ወደ በኣላ ቍልቍል ይወርዳል። 10ከዚያም ከበኣላ በምዕራብ በኩል አድርጎ ወደ ሴይር ይታጠፍና ክሳሎን ተብሎ በሚጠራው በይዓሪም ኰረብታ ሰሜናዊ ተረተር ዐልፎ ቍልቍል ወደ ቤትሳሚስ በመውረድ ወደ ተምና ይሻገራል። 11ደግሞም በአቃሮን ሰሜናዊ ተረተር አድርጎ ወደ ሽክሮን ይታጠፍና በበኣላ ተራራ ላይ ዐልፎ እስከ የብኒኤል ይደርሳል፤ ከዚህ በኋላ ወሰኑ ባሕሩ ላይ ይቆማል።
12የምድሪቱ ምዕራባዊ ወሰን የታላቁ ባሕር#15፥12 በዚህና በቍጥር 15፥47 ላይ የተጠቀሰው የሜድትራንያን ባሕር ነው። ጠረፍ ነው።
እንግዲህ በየጐሣው የተደለደለውን የይሁዳን ሕዝብ በዙሪያው የከበቡት ወሰኖቹ እነዚሁ ናቸው።
13ኢያሱ እግዚአብሔር ባዘዘው መሠረት፣ ከይሁዳ ድርሻ ላይ ከፍሎ ኬብሮን የተባለችውን ቂርያት አርባቅን ለዮፎኒ ልጅ ለካሌብ ሰጠው፤ አርባቅም የዔናቅ አባት ነበረ። 14ካሌብም ሦስቱን የዔናቅን ዘሮች ሴሲንን፣ አኪመንንና ተላሚንን ከኬብሮን አሳደዳቸው፤ 15ከዚያም በዳቤር ሕዝብ ላይ ዘመተ፤ ዳቤር ቀድሞ ቂርያትሤፍር ትባል ነበር። 16ካሌብ፣ “ቂርያትሤፍርን ወግቶ ለሚይዝ ሰው ልጄን ዓክሳን እድርለታለሁ” አለ። 17ስለዚህ የካሌብ ወንድም የቄኔዝ ልጅ ጎቶንያል ከተማዪቱን ያዛት፤ ካሌብም ልጁን ዓክሳን ዳረለት።
18ዓክሳ ወደ ጎቶንያል በመጣች ጊዜም፣ ከአባቷ ላይ የዕርሻ መሬት እንዲለምን አጥብቃ ነገረችው።#15፥18 ዕብራይስጥና አንዳንድ የሰብዓ ሊቃናት ትርጕሞች ከዚህ ጋራ ይስማማሉ፤ ብዙ የሰብዓ ሊቃናት ትርጕሞች ግን (መሳ 1፥14 ይመ) አጥብቆ ነገራት ያላሉ። ከአህያዋ ላይ እንደ ወረደች ካሌብ፣ “ምን እንዳደርግልሽ ትፈልጊያለሽ?” ሲል ጠየቃት።
19እርሷም፣ “እባክህ፤ ባርከኝ፤ በኔጌብ መሬት እንደ ሰጠኸኝ ሁሉ፣ አሁንም የውሃ ምንጭ ጕድጓዶች ስጠኝ” አለችው፤ ካሌብም የላይኛውንና የታችኛውን ምንጮች ሰጣት።
20ለይሁዳ ነገድ በየጐሣቸው የተሰጣቸው ርስት ይህ ነው፤
21በኔጌብ አካባቢ በኤዶም ድንበር ላይ በወሰኑ ጫፍ የሚገኙት የይሁዳ ነገድ ደቡባዊ ከተሞች እነዚህ ነበሩ፤
ቀብጽኤል፣ ዔዴር፣ ያጉር፣ 22ቂና፣ ዲሞና፣ ዓድዓዳ፣ 23ቃዴስ፣ ሐጾር፤ ዩትናን፣ 24ዚፍ፣ ጤሌም፣ በዓሎት፣ 25ሐጾርሐዳታ፣ ሐጾር የምትባለው ቂርያትሐጾር 26አማም፣ ሽማዕ፣ ሞላዳ፣ 27ሐጻርጋዳ፣ ሐሽሞን፣ ቤትጳሌጥ፣ 28ሐጻርሹዓል፣ ቤርሳቤህ፣ ቢዝዮትያ 29በኣላ፣ ዒዪም፣ ዔጼም፣ 30ኤልቶላድ፣ ኪሲል፣ ሖርማ፣ 31ጺቅላግ፣ ማድማና፣ ሳንሳና 32ልባዎት፣ ሺልሂም፣ ዓይንና ሪሞን ናቸው፤ በአጠቃላይም ከተሞቹና መንደሮቻቸው ሃያ ዘጠኝ ናቸው።
33በምዕራቡ በኰረብታዎች ግርጌ ያሉት ደግሞ እነዚህ ናቸው፤
ኤሽታኦል፤ ጾርዓ፣ አሽና 34ዛኖዋ፣ ዓይንገኒም፣ ታጱዋ፣ ዓይናም፣ 35ያርሙት፣ ዓዶላም፣ ሦኮን፣ ዓዜቃ፣ 36ሽዓራይም፣ ዓዲታይም፣ ግዴራ፣ ግዴሮታይም ናቸው፤ ከተሞቹም ከነመንደሮቻቸው ዐሥራ አራት ናቸው።
37ጽናን፣ ሐዳሻ፣ ሚግዳልጋድ፣ 38ዲልዓን፣ ምጽጳ፣ ዮቅትኤል፣ 39ለኪሶ፣ ቦጽቃት፣ ዔግሎን፣ 40ከቦን፣ ለሕማስ፣ ኪትሊሽ፣ 41ግዴሮት፣ ቤትዳጎን፣ ናዕማና መቄዳ ናቸው፤ ከተሞቹም ከነመንደሮቻቸው ዐሥራ ስድስት ናቸው።
42ልብና፣ ዔቴር፣ ዓሻን 43ይፍታሕ፣ አሽና፣ ንጺብ፣ 44ቅዒላ፣ አክዚብና መሪሳ ናቸው፤ ከተሞቹም ከነመንደሮቻቸው ዘጠኝ ናቸው።
45አቃሮን በዙሪያዋ ካሉ ሰፈሮችና መንደሮቿ ጋራ፣ 46እንዲሁም ከአቃሮን በስተ ምዕራብ በአሽዶድ አካባቢ ያሉ ሰፈሮችና መንደሮቻቸው ሁሉ፣ 47አሽዶድ በዙሪያዋ ካሉ ሰፈሮችና መንደሮች ጋራ፣ ጋዛ እስከ ግብጽ ደረቅ ወንዝና እስከ ታላቁ ባሕር ጠረፍ በመለስ ካሉት ሰፈሮቿና መንደሮቿ ጋራ።
48በኰረብታማዋም አገር የሚገኙ ከተሞች ደግሞ እነዚህ ናቸው፤
ሳምር፣ የቲር፣ ሶኮ 49ደና፣ ዳቤር የምትባለው ቂርያትስና 50ዓናብ፣ ኤሽትሞዓ፣ ዓኒም፣ 51ጎሶም፣ ሖሎንና ጊሎ፤ እነዚህም ዐሥራ አንዱ ከተሞችና መንደሮቻቸው ናቸው።
52አራብ፣ ዱማ፣ ኤሽዓን፣ 53ያኒም፣ ቤትታጱዋ፣ አፌቃ 54ሑምጣ፣ ኬብሮን የተባለችው ቂርያት አርባቅና ጺዖር ናቸው፤ እነዚህም ዘጠኝ ከተሞችና መንደሮቻቸው ናቸው።
55ማዖን፣ ቀርሜሎስ፣ ዚፍ፣ ዩጣ 56ኢይዝራኤል፣ ዮቅድዓም፣ ዛኖዋሕ፣ 57ቃይን፣ ጊብዓና ተምና ናቸው፤ እነዚህም ዐሥር ከተሞችና መንደሮቻቸው ናቸው።
58ሐልሑል፣ ቤትጹር፣ ጌዶር፣ 59ማዕራት፣ ቤትዓኖትና ኤልትቆን ናቸው፤ እነዚህም ስድስት ከተሞችና መንደሮቻቸው ናቸው።
60ቂርያትይዓይሪም የተባለችው ቂርያትበኣልና ረባት፤ እነዚህም ሁለት ከተሞችና መንደሮቻቸው ናቸው።
61በምድረ በዳው ደግሞ እነዚህ ናቸው፤
ቤትዓረባ፣ ሚዲን፣ ስካካ፣ 62ኒብሻን፣ የጨው ከተማና ዓይንጋዲ፤ እነዚህም ስድስት ከተሞችና መንደሮቻቸው ናቸው።
63ነገር ግን የይሁዳ ዘሮች በኢየሩሳሌም የሚኖሩትን ኢያቡሳውያን ከቦታቸው ሊያስለቅቋቸው አልቻሉም፤ ኢያቡሳውያንም እስከ ዛሬ ድረስ ከይሁዳ ሕዝብ ጋራ በኢየሩሳሌም ዐብረው ይኖራሉ።
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.