ማርቆስ 10
10
የባልና የሚስት ፍች
10፥1-12 ተጓ ምብ – ማቴ 19፥1-9
1ኢየሱስ ከዚያ ተነሥቶ ከዮርዳኖስ ማዶ ወዳለው ወደ ይሁዳ አውራጃ ሄደ፤ ሕዝቡም እንደ ገና በዙሪያው ተሰበሰበ፤ ከዚህ ቀደም ያደርገው እንደ ነበረውም አስተማራቸው።
2አንዳንድ ፈሪሳውያንም መጥተው፣ “አንድ ባል ሚስቱን እንዲፈታ ተፈቅዷልን?” ብለው ሊፈትኑት ጠየቁት።
3እርሱም መልሶ፣ “ሙሴ ምን ብሎ አዘዛችሁ?” አላቸው።
4እነርሱም፣ “ሙሴማ የፍችውን ጽሕፈት ጽፎ እንዲፈታት ፈቅዷል” አሉ።
5ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “ሙሴ ይህን ሕግ የጻፈላችሁ ልባችሁ ደንዳና በመሆኑ ነው። 6ነገር ግን በፍጥረት መጀመሪያ እግዚአብሔር ‘ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው።’ 7‘ስለዚህ ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል፤ ከሚስቱም ጋራ ይጣመራል፤#10፥7 አንዳንድ የጥንት ቅጆች ከሚስቱ ጋራ ይጣመራል የሚለው የላቸውም። 8ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ።’#10፥8 ዘፍ 2፥24 ከእንግዲህ አንድ ሥጋ ናቸው እንጂ ሁለት አይደሉም። 9ስለዚህ እግዚአብሔር ያጣመረውን ሰው አይለየው።”
10እንደ ገና ወደ ቤት በገቡ ጊዜ፣ ደቀ መዛሙርቱ ይህንኑ አንሥተው ጠየቁት። 11እርሱም፣ “ማንም ሚስቱን ፈትቶ ሌላዪቱን የሚያገባ በርሷ ላይ ያመነዝራል። 12እርሷም ባሏን ፈትታ ሌላ ብታገባ ታመነዝራለች” አላቸው።
ኢየሱስ ሕፃናትን ባረከ
10፥13-16 ተጓ ምብ – ማቴ 19፥13-15፤ ሉቃ 18፥15-17
13ኢየሱስ እንዲዳስሳቸው፣ ሰዎች ሕፃናትን ወደ እርሱ አመጡ፤ ደቀ መዛሙርቱ ግን ገሠጿቸው። 14ኢየሱስም ይህን ሲያይ ተቈጥቶ እንዲህ አላቸው፤ “ሕፃናት ወደ እኔ እንዲመጡ ፍቀዱላቸው፤ አትከልክሏቸውም፤ የእግዚአብሔር መንግሥት እንደ እነዚህ ላሉት ናትና። 15እውነት እላችኋለሁ፤ የእግዚአብሔርን መንግሥት እንደ ሕፃን የማይቀበል ሁሉ ከቶ አይገባባትም።” 16ሕፃናቱንም ዐቀፋቸው፤ እጁንም ጭኖ ባረካቸው።
ሀብታሙ ወጣት
10፥17-31 ተጓ ምብ – ማቴ 19፥16-30፤ ሉቃ 18፥18-30
17ከዚያ ተነሥቶ መንገዱን ሲጀመር፣ አንድ ሰው ወደ እርሱ እየሮጠ መጣ፤ በፊቱም በጕልበቱ ተንበርክኮ፣ “መልካም መምህር ሆይ፤ የዘላለምን ሕይወት ለመውረስ ምን ማድረግ ይገባኛል” አለው።
18ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “ስለ ምን ቸር ትለኛለህ? ከአንዱ ከእግዚአብሔር በቀር መልካም ማንም የለም፤ 19‘አታመንዝር፣ አትግደል፣ አትስረቅ፣ በሐሰት አትመስክር፣ አታታልል፣ አባትህንና እናትህን አክብር’ የሚለውን ትእዛዝ ታውቃለህ።”
20ሰውየውም፣ “መምህር ሆይ፤ እነዚህን ሁሉ ከልጅነቴ ጀምሮ ጠብቄአለሁ” አለው።
21ኢየሱስም ተመለከተውና ወደደው፤ “እንግዲያው አንድ ነገር ይጐድልሃል፤ ሂድና ያለህን ሁሉ ሸጠህ ለድኾች ስጥ፤ በሰማይ ሀብት ይኖርሃል፤ ከዚያም መጥተህ ተከተለኝ” አለው።
22ሰውየው ይህን ሲሰማ ክፉኛ አዘነ፤ ብዙ ሀብት ስለ ነበረው እየተከዘ ሄደ።
23ኢየሱስ ዙሪያውን በመመልከት ደቀ መዛሙርቱን፣ “ለሀብታሞች ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት ምንኛ ከባድ ነገር ነው!” አላቸው።
24ደቀ መዛሙርቱም በንግግሩ ተገረሙ፤ ኢየሱስ ግን እንደ ገና መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “ልጆች ሆይ፤#10፥24 አንዳንድ ቅጆች በሀብት ለሚታመኑ የሚል ሐረግ አላቸው። ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት ምንኛ ከባድ ነገር ነው! 25ሀብታም ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ከሚገባ ይልቅ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ቢያልፍ ይቀልለዋል።”
26ደቀ መዛሙርቱም ይበልጥ በመገረም፣ “ታዲያ ማን ሊድን ይችላል?” ተባባሉ።
27ኢየሱስም አያቸውና፣ “ይህ በሰው ዘንድ አይቻልም፤ በእግዚአብሔር ዘንድ ግን እንዲህ አይደለም፤ በእግዚአብሔር ዘንድ ሁሉም ነገር ይቻላል” አላቸው።
28ጴጥሮስም፣ “እነሆ፤ እኛ ሁሉን ትተን ተከትለንሃል!” አለው።
29ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለ፤ “እውነት እላችኋለሁ፤ ስለ እኔና ስለ ወንጌል ሲል ቤትን ወይም ወንድሞችን ወይም እኅቶችን ወይም እናትን ወይም አባትን ወይም ልጆችን ወይም ዕርሻን የተወ ሁሉ፣ 30አሁን በዚህ ዘመን ከስደት ጋራ ቤቶችን፣ ወንድሞችን፣ እኅቶችን፣ እናቶችን፣ ልጆችንና ዕርሻን መቶ ዕጥፍ የማይቀበል፣ በሚመጣውም ዓለም የዘላለም ሕይወት የማይወርስ የለም። 31ነገር ግን ብዙ ፊተኞች ኋለኞች፣ ኋለኞችም ፊተኞች ይሆናሉ።”
ኢየሱስ ዳግም ስለ ሞቱ አስቀድሞ ተናገረ
10፥32-34 ተጓ ምብ – ማቴ 20፥17-19፤ ሉቃ 18፥31-33
32ወደ ኢየሩሳሌም ለመውጣት በመንገድ ላይ ሳሉ፣ ኢየሱስ ፊት ፊታቸው ይሄድ ነበር፤ ደቀ መዛሙርቱ ተገረሙ፣ ሌሎች የተከተሉት ደግሞ ፈርተው ነበር። ደግሞም ዐሥራ ሁለቱን ከሕዝቡ ለይቶ ምን እንደሚደርስበት ነገራቸው፤ 33እንዲህም አላቸው፤ “እንግዲህ ወደ ኢየሩሳሌም እንወጣለን፤ የሰው ልጅ ለካህናት አለቆችና ለጸሐፍት ዐልፎ ይሰጣል፤ እነርሱም የሞት ፍርድ ይፈርዱበታል፤ አሳልፈው ለአሕዛብ ይሰጡታል፤ 34ያፌዙበታል፤ ይተፉበታል፤ ይገርፉታል፤ ከዚያም ይገድሉታል፤ እርሱ ግን ከሦስት ቀን በኋላ ይነሣል።”
የያዕቆብና የዮሐንስ ጥያቄ
10፥35-45 ተጓ ምብ – ማቴ 20፥20-28
35ከዚያም የዘብዴዎስ ልጆች ያዕቆብና ዮሐንስ ወደ እርሱ ቀርበው፣ “መምህር ሆይ፤ የምንለምንህን ሁሉ እንድታደርግልን እንፈልጋለን” አሉት።
36እርሱም፣ “ምን እንዳደርግላችሁ ትፈልጋላችሁ?” አላቸው።
37እነርሱም፣ “በክብርህ ጊዜ አንዳችን በቀኝህ፣ አንዳችን በግራህ እንድንቀመጥ ፍቀድልን” አሉት።
38ኢየሱስም፣ “የምትለምኑትን አታውቁም፤ እኔ የምጠጣውን ጽዋ ልትጠጡ፣ የምጠመቀውንስ ጥምቀት ልትጠመቁ ትችላላችሁን?” አላቸው።
39እነርሱም፣ “አዎን እንችላለን” አሉት።
ኢየሱስም፣ “እኔ የምጠጣውን ጽዋ ትጠጣላችሁ፤ እኔ የምጠመቀውንም ጥምቀት ትጠመቃላችሁ፤ 40ነገር ግን በቀኜ ወይም በግራዬ መቀመጥ ለተዘጋጀላቸው የሚሆን እንጂ እኔ የምሰጠው ነገር አይደለም” አላቸው።
41ዐሥሩ ይህን ሲሰሙ፣ ያዕቆብንና ዮሐንስን መቈጣት ጀመሩ። 42ኢየሱስም ወደ ራሱ ጠርቶ እንዲህ አላቸው፤ “የአሕዛብ ገዦች ተብለው የሚታሰቡት እንደሚገዟቸው፣ ባለሥልጣኖቻቸውም በእነርሱ ላይ እንደሚሠለጥኑባቸው ታውቃላችሁ፤ 43በእናንተ ዘንድ ግን እንዲህ አይደለም፤ ከመካከላችሁ ታላቅ መሆን የሚፈልግ ሁሉ አገልጋይ ይሁን፤ 44ፊተኛ ለመሆን የሚፈልግ ሁሉ፣ የሁሉ ባሪያ ይሁን፤ 45የሰው ልጅ እንዲያገለግሉት ሳይሆን፣ ለማገልገልና ነፍሱንም ለብዙዎች ቤዛ አድርጎ ለመስጠት መጥቷልና።”
ኢየሱስ ዐይነ ስውሩን በርጤሜዎስን ፈወሰ
10፥46-52 ተጓ ምብ – ማቴ 20፥29-34፤ ሉቃ 18፥35-43
46ከዚህ በኋላ ወደ ኢያሪኮ መጡ። ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ከብዙ ሕዝብ ጋራ ከኢያሪኮ ሲወጡ ዐይነ ስውሩ የጤሜዎስ ልጅ በርጤሜዎስ በመንገድ ዳር ተቀምጦ ይለምን ነበር። 47እርሱም የናዝሬቱ ኢየሱስ መሆኑን በሰማ ጊዜ፣ “የዳዊት ልጅ፣ ኢየሱስ ሆይ፤ ማረኝ!” እያለ ይጮኽ ጀመር።
48ብዙዎችም ዝም እንዲል ገሠጹት፤ እርሱ ግን፣ “የዳዊት ልጅ ሆይ፤ ማረኝ!” እያለ የባሰ ጮኸ።
49ኢየሱስም ቆም ብሎ፣ “ጥሩት” አላቸው።
እነርሱም ዐይነ ስውሩን፣ “አይዞህ፤ ተነሥ፤ ይጠራሃል!” አሉት። 50እርሱም ልብሱን ጥሎ፣ ዘልሎ ተነሥቶ ወደ ኢየሱስ መጣ።
51ኢየሱስም፣ “ምን እንዳደርግልህ ትፈልጋለህ?” አለው።
ዐይነ ስውሩም፣ “መምህር ሆይ፤ ዳግም እንዳይ እፈልጋለሁ” አለው።
52ኢየሱስም፣ “ሂድ፣ እምነትህ አድኖሃል” አለው፤ ወዲያውም ዐይኑ በራለት፤ በመንገድም ኢየሱስን ተከትሎት ሄደ።
Currently Selected:
ማርቆስ 10: NASV
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.