ማርቆስ 11
11
ኢየሱስ በታላቅ ክብር ወደ ኢየሩሳሌም ገባ
11፥1-10 ተጓ ምብ – ማቴ 21፥1-9፤ ሉቃ 19፥29-38
11፥7-10 ተጓ ምብ – ዮሐ 12፥12-15
1ወደ ኢየሩሳሌም በደብረ ዘይት ተራራ አጠገብ ወዳሉት ወደ ቤተ ፋጌና ወደ ቢታንያ በቀረቡ ጊዜ፣ ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ሁለቱን እንዲህ በማለት ላካቸው፤ 2“በፊታችሁ ወዳለው መንደር ሂዱ፣ ሰው ተቀምጦበት የማያውቅ የአህያ ውርንጫ እዚያ ታስሮ ታገኛላችሁ፤ ፈትታችሁ አምጡት፤ 3ማንም፣ ‘ምን ማድረጋችሁ ነው?’ ቢላችሁ፣ ‘ለጌታ ያስፈልገዋል፤ እርሱም ወዲያውኑ መልሶ ይልከዋል’ በሉት።”
4እነርሱም ሄዱ፤ በአንድ ቤት በራፍ መንገድ ላይ የአህያ ውርንጫ ታስሮ አገኙ፤ ፈቱትም። 5በዚያ ከቆሙት አንዳንድ ሰዎች፣ “ውርንጫውን የምትፈቱት ለምንድን ነው?” አሏቸው። 6ደቀ መዛሙርቱም ኢየሱስ ያላቸውን ለሰዎቹ በነገሯቸው ጊዜ ፈቀዱላቸው። 7ውርንጫውንም ወደ ኢየሱስ አምጥተው ልብሶቻቸውን በጀርባው ላይ አደረጉ፤ እርሱም ተቀመጠበት። 8ብዙ ሰዎች ልብሶቻቸውን በመንገድ ላይ አነጠፉ፤ ሌሎች ደግሞ ከሜዳ ቅርንጫፍ እየቈረጡ ያነጥፉ ነበር። 9የቀደሙትና የተከተሉትም በታላቅ ድምፅ እንዲህ ይሉ ነበር፤
“ሆሳዕና!”#11፥9 በዕብራይስጡ አድን! ማለት ሲሆን፣ ምስጋናን የሚገልጽ አባባል ነው፤ እንዲሁም 10 ይመ።
“በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው!”
10“የምትመጣው የአባታችን የዳዊት መንግሥት የተባረከች ናት!”
“ሆሳዕና በአርያም!”
11ኢየሱስም ኢየሩሳሌም ደረሰ፤ ከዚያም ወደ ቤተ መቅደስ ገባ፤ በዙሪያው ያለውንም ሁሉ ተመለከተ፤ ቀኑም ስለ መሸ ከዐሥራ ሁለቱ ጋራ ወደ ቢታንያ ወጣ።
ኢየሱስ ቤተ መቅደስን አጸዳ
11፥12-14 ተጓ ምብ – ማቴ 21፥18-22
11፥15-18 ተጓ ምብ – ማቴ 21፥12-16፤ ሉቃ 19፥45-47፤ ዮሐ 2፥13-16
12በማግስቱም ከቢታንያ ሲወጡ ኢየሱስ ተራበ። 13እርሱም ቅጠል ያላት የበለስ ዛፍ ከሩቅ አየ፤ ምናልባት ፍሬ ይገኝባት እንደ ሆነ ብሎ ወደ እርሷ መጣ፤ ነገር ግን የበለስ ወራት አልነበረምና ከቅጠል በቀር ምንም አላገኘባትም። 14ከዚያም ዛፏን፣ “ከአሁን ጀምሮ ለዘላለም ማንም ከአንቺ ፍሬ አይብላ” አላት። ደቀ መዛሙርቱም ይህን ሲናገር ሰሙ።
15ወደ ኢየሩሳሌምም መጡ፤ ከዚያም ወደ ቤተ መቅደስ ገብቶ፣ የሚሸጡትንና የሚገዙትን ያስወጣ ጀመር። የገንዘብ ለዋጮችን ጠረጴዛና የርግብ ሻጮችን መቀመጫ ገለባበጠ፤ 16ማንም ዕቃ ተሸክሞ በቤተ መቅደሱ ቅጥር ግቢ ውስጥ እንዳያልፍ ከለከለ። 17ሲያስተምራቸውም፣ “ ‘ቤቴ ለሕዝቦች ሁሉ የጸሎት ቤት ይባላል’#11፥17 ኢሳ 56፥7 ተብሎ አልተጻፈምን? እናንተ ግን ‘የወንበዴዎች ዋሻ አደረጋችሁት!’#11፥17 ኤር 7፥11” አላቸው።
18የካህናት አለቆችና ጸሐፍትም፣ ይህን ሲሰሙ እንዴት እንደሚያጠፉት መንገድ ይፈልጉ ጀመር፤ ሕዝቡ ሁሉ በትምህርቱ በመገረማቸው ፈርተውታልና።
19በመሸም ጊዜ ከከተማዪቱ ወጥተው ሄዱ#11፥19 አንዳንድ ቅጆች ወጥቶ ሄደ ይላሉ።።
የበለሷ ዛፍ ደረቀች
11፥20-24 ተጓ ምብ – ማቴ 21፥19-22
20በማግስቱም ጧት በመንገድ ሲያልፉ፣ በለሲቱ ከነሥሯ ደርቃ አዩ። 21ጴጥሮስ ነገሩ ትዝ አለውና ኢየሱስን፣ “መምህር ሆይ፤ እነሆ፤ የረገምሃት በለስ ደርቃለች!” አለው።
22ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “በእግዚአብሔር እመኑ፤#11፥22 አንዳንድ የጥንት ቅጆች በእግዚአብሔር ላይ እምነት ካላችሁ ይላሉ። 23እውነት እላችኋለሁ፤ ማንም ይህን ተራራ፣ ‘ተነቅለህ ወደ ባሕር ተወርወር’ ቢለውና ይህንም በልቡ ሳይጠራጠር ቢያምን ይሆንለታል። 24ስለዚህ በጸሎት የምትለምኑትን ሁሉ እንደ ተቀበላችሁት አድርጋችሁ እመኑ፤ ይሆንላችሁማል። 25እንዲሁም ለጸሎት በምትቆሙበት ጊዜ፣ የሰማዩ አባታችሁ በደላችሁን ይቅር እንዲልላችሁ፣ እናንተም በሰው ላይ ያላችሁን ሁሉ ይቅር በሉ። [26ይቅር ባትሉ ግን የሰማዩ አባታችሁ በደላችሁን ይቅር አይላችሁም።#11፥26 አንዳንድ ቅጆች 26 የላቸውም።”]
በኢየሱስ ሥልጣን ላይ ጥያቄ ተነሣ
11፥27-33 ተጓ ምብ – ማቴ 21፥23-27፤ ሉቃ 20፥1-8
27እንደ ገና ወደ ኢየሩሳሌም መጡ፤ ኢየሱስ በቤተ መቅደሱ ቅጥር ግቢ ውስጥ በሚዘዋወርበት ጊዜ፣ የካህናት አለቆች፣ ጸሐፍትና የሕዝብ ሽማግሌዎች ወደ እርሱ ቀርበው፣ 28“እነዚህን ነገሮች የምታደርገው በምን ሥልጣን ነው? እነዚህን እንድታደርግስ ይህን ሥልጣን የሰጠህ ማን ነው?” አሉት።
29ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፤ “እኔም አንድ ጥያቄ ልጠይቃችሁ፤ መልሱልኝ፤ እኔም እነዚህን ነገሮች በምን ሥልጣን እንደማደርግ እነግራችኋለሁ። 30የዮሐንስ ጥምቀት ከሰማይ ነበረችን ወይስ ከሰው? መልሱልኝ!”
31እነርሱም እርስ በርሳቸው እንዲህ ተባባሉ፤ “ ‘ከሰማይ ነው’ ብንል፣ ‘ታዲያ ለምን አላመናችሁበትም?’ ይለናል፤ 32‘ከሰው ነው’ ብንል …” ሕዝቡ ሁሉ ዮሐንስ እውነተኛ ነቢይ እንደ ሆነ ይቈጥር ስለ ነበር ፈሩ።
33ስለዚህ ለኢየሱስ፣ “አናውቅም” ብለው መለሱለት።
ኢየሱስም፣ “እንግዲያውስ እኔም እነዚህን ነገሮች በምን ሥልጣን እንደማደርግ አልነግራችሁም” አላቸው።
Currently Selected:
ማርቆስ 11: NASV
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.