የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ፊልሞና 1

1
1የክርስቶስ ኢየሱስ እስረኛ ከሆነው ከጳውሎስና ከወንድማችን ከጢሞቴዎስ፤
ለተወደደው እና ዐብሮን ለሚሠራው ለፊልሞና፣ 2ለእኅታችን ለአፍብያ፣ ዐብሮን ወታደር ለሆነው ለአርክጳ፣ በቤትህም ላለችው ቤተ ክርስቲያን፤
3ከአባታችን ከእግዚአብሔር፣ ከጌታም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ#1፥3 የግሪኩ ቃል እዚህና በቍጥር 22 እና 25 ላይ ብዙ ቍጥርን የሚያመለክት ሲሆን በሌሎቹ ቦታዎች አንተ የሚለው ቃል በነጠላ ተገልጧል። ይሁን።
ምስጋናና ጸሎት
4አንተን በጸሎቴ በማስብህ ጊዜ አምላኬን ሁልጊዜ አመሰግናለሁ፤ 5ምክንያቱም በጌታ በኢየሱስ ያለህን እምነትና ለቅዱሳንም ሁሉ ያለህን ፍቅር ሰምቻለሁ። 6በክርስቶስ ስላለን መልካም ነገር ሁሉ በሚገባ ትረዳ ዘንድ፣ እምነትህን ለሌሎች በማካፈል እንድትተጋ እጸልያለሁ። 7ወንድሜ ሆይ፤ የቅዱሳንን ልብ ስላሳረፍህ ከፍቅርህ ታላቅ ደስታና መጽናናት አግኝቻለሁ።
ጳውሎስ ስለ አናሲሞስ ያደረገው ልመና
8ስለዚህ ማድረግ የሚገባህን እንድታደርግ አዝዝህ ዘንድ በክርስቶስ ድፍረት ቢኖረኝም፣ 9በፍቅር እለምንሃለሁ፤ እንግዲህ ሽማግሌና አሁን ደግሞ የክርስቶስ ኢየሱስ እስረኛ የሆንሁት እኔ ጳውሎስ፣ 10በእስር እያለሁ ስለ ወለድሁት ልጄ ስለ አናሲሞስ#1፥10 አናሲሞስ ማለት የሚጠቅም ማለት ነው። እለምንሃለሁ። 11አስቀድሞ የሚጠቅምህ አልነበረም፤ አሁን ግን ለአንተም ሆነ ለእኔ የሚጠቅም ሰው ሆኗል።
12የልቤ የሆነውን እርሱን መልሼ ወደ አንተ ልኬዋለሁ። 13ስለ ወንጌል በታሰርሁበት ጊዜ በአንተ ፈንታ ሆኖ እንዲያገለግለኝ ለራሴ ላስቀረው ፈልጌ ነበር። 14ነገር ግን አንተ የምታደርገውን መልካም ነገር ሁሉ በውዴታ እንጂ በግዴታ እንዳይሆን ሳላማክርህ ምንም ማድረግ አልፈልግም። 15ምናልባት ለጥቂት ጊዜ ከአንተ የተለየው፣ ተቀብለህ ለዘለቄታው አንተ ዘንድ እንድታቈየው ነው፤ 16ከእንግዲህ ወዲህ ግን እንደ ባሪያ ሳይሆን ከባሪያ በላይ የሆነ ተወዳጅ ወንድም ነው። ለእኔ ተወዳጅ ነው፤ ለአንተ ግን በሥጋም በጌታም ይበልጥ ተወዳጅ ነው።
17እንግዲህ እንደ ባልንጀራ ከቈጠርኸኝ እኔን እንደምትቀበለኝ አድርገህ ተቀበለው። 18አንተን የበደለህ ነገር ቢኖር ወይም የአንተ ብድር ቢኖርበት በእኔ ላይ ቍጠረው። 19እኔ ጳውሎስ ይህን በገዛ እጄ ጽፌልሃለሁ፤ ያለበትን እኔው እከፍልሃለሁ። አንተም ራስህ የእኔ ስለ መሆንህ ምንም አልናገርም። 20ወንድሜ ሆይ፤ በጌታ እንድትጠቅመኝ እፈልጋለሁ፤ በክርስቶስ ልቤን አሳርፍልኝ። 21ታዛዥ መሆንህን በመተማመን፣ ከምጠይቀውም በላይ እንደምታደርግ በማወቅ እጽፍልሃለሁ።
22ከዚህም ሌላ፣ ጸሎታችሁ መልስ አግኝቶ ወደ እናንተ ለመምጣት ተስፋ ስለማደርግ ማረፊያ አዘጋጁልኝ።
23ከእኔ ጋራ የክርስቶስ ኢየሱስ እስረኛ የሆነው ኤጳፍራ ሰላምታ ያቀርብልሃል።
24እንዲሁም ዐብረውኝ የሚሠሩት ማርቆስ፣ አርስጥሮኮስ፣ ዴማስና ሉቃስ ሰላምታ ያቀርቡልሃል።
25የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ#1፥25 በአንዳንድ ቅጆች ክርስቶስ የሚለው ቃል የለም። ጸጋ ከመንፈሳችሁ ጋራ ይሁን።

Currently Selected:

ፊልሞና 1: NASV

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ