ቲቶ 3
3
በጎ የሆነውን ማድረግ
1ሰዎች ለገዦችና ለባለሥልጣናት እንዲገዙ፣ እንዲታዘዙና መልካም የሆነውን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ እንዲሆኑ አሳስባቸው። 2እንዲሁም በማንም ላይ ክፉ እንዳይናገሩ፣ ሰላማውያን እንዲሆኑ፣ ለሰዎችም ሁሉ ከልብ የመነጨ ትሕትና እንዲያሳዩ አስገንዝባቸው።
3ቀደም ሲል እኛ ራሳችን ማስተዋል የጐደለን፣ የማንታዘዝ፣ የተታለልን፣ ለተለያየ ምኞትና ምቾት ባሪያ ሆነን የተገዛን ነበርን፤ እየተጣላንና እርስ በርስ እየተጠላላን በክፋትና በምቀኛነት እንኖር ነበር። 4ነገር ግን የአዳኛችን የእግዚአብሔር ቸርነትና ፍቅር በተገለጠ ጊዜ፣ 5ስላደረግነው የጽድቅ ሥራ ሳይሆን፣ ከምሕረቱ የተነሣ አዳነን። ያዳነንም ዳግም ልደት በሆነው መታጠብና በመንፈስ ቅዱስ መታደስ ነው፤ 6ይህንም መንፈስ እግዚአብሔር በአዳኛችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በእኛ ላይ አትረፍርፎ አፈሰሰው፤ 7ይኸውም በጸጋው ጸድቀን የዘላለምን ሕይወት ተስፋ ይዘን ወራሾች እንድንሆን ነው። 8ይህም የታመነ ቃል ነው። በእግዚአብሔር ያመኑቱ መልካሙን ነገር ለማድረግ ራሳቸውን አሳልፈው ይሰጡ ዘንድ እነዚህን ነገሮች አስረግጠህ እንድትናገር እፈልጋለሁ። ይህ መልካምና ለማንኛውም ሰው የሚጠቅም ነው።
9ነገር ግን ከንቱ ከሆነ ክርክርና ከትውልድ ሐረግ ቈጠራ፣ ከጭቅጭቅና ስለ ሕግ ከሚነሣ ጠብ ራቅ፤ ይህ ዋጋ ቢስና ከንቱ ነውና። 10መከፋፈል የሚያመጣን ሰው አንድ ጊዜ ምከረው፤ ለሁለተኛ ጊዜ አስጠንቅቀው፤ ከዚያ ካለፈ ከርሱ ጋራ አንዳች ነገር አይኑርህ። 11እንዲህ ዐይነቱ ሰው የሳተና ኀጢአተኛ ነው፤ ራሱንም እንደሚኰንን ዕወቅ።
የመጨረሻ ምክር
12አርጢሞንን ወይም ቲኪቆስን ወደ አንተ እንደ ላክሁ እኔ ወዳለሁበት ወደ ኒቆጵልዮን ለመምጣት የተቻለህን ሁሉ አድርግ፤ ክረምቱን በዚያ ላሳልፍ ወስኛለሁ። 13ሕግ ዐዋቂውን ዜማስንና አጵሎስን በጕዟቸው ለመርዳት የተቻለህን ሁሉ አድርግ፤ የሚያስፈልጋቸውንም ሁሉ አሟላላቸው።
14ከእኛ ወገን የሆኑት ለዕለት የሚያስፈልጋቸውን እንዲያገኙና ኑሯቸውም ፍሬ የሌለው እንዳይሆን ለመልካም ሥራ መትጋትን ይማሩ ዘንድ ይገባቸዋል።
15ከእኔ ጋራ ያሉት ሁሉ ሰላምታ ያቀርቡላችኋል።
ከእምነት የተነሣ ለሚወድዱን ሰላምታ አቅርቡልን።
ጸጋ ከሁላችሁ ጋራ ይሁን።
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.