መዝሙር 105
105
መዝሙር 105
105፥1-15 ተጓ ምብ – 1ዜና 16፥8-22
1 እግዚአብሔርን አመስግኑ፤ ስሙንም ጥሩ፤
ሥራውንም በሕዝቦች መካከል አሳውቁ።
2ተቀኙለት፤ ዘምሩለት፤
ድንቅ ሥራዎቹንም ሁሉ ተናገሩ።
3በቅዱስ ስሙ ተጓደዱ፤
እግዚአብሔርን የሚፈልጉ ሁሉ፣ ልባቸው ሐሤት ያድርግ።
4 እግዚአብሔርንና ብርታቱን ፈልጉ፤
ፊቱንም ዘወትር ፈልጉ።
5ያደረጋቸውን ድንቅ ሥራዎች፣
ታምራቱንና የሰጠውንም ፍርድ አስታውሱ፤
6እናንተ የአገልጋዩ የአብርሃም ዘሮች፣
ለራሱም የመረጣችሁ የያዕቆብ ልጆች ሆይ፤ አስታውሱ።
7እርሱ እግዚአብሔር አምላካችን ነው፤
ፍርዱም በምድር ሁሉ ላይ ነው።
8ኪዳኑን ለዘላለም፣
ያዘዘውንም ቃል እስከ ሺሕ ትውልድ ያስባል።
9ከአብርሃም ጋራ የገባውን ቃል ኪዳን፣
ለይሥሐቅም የማለውን መሐላ አይረሳም።
10ይህንም ለያዕቆብ ሥርዐት አድርጎ፣
ለእስራኤልም የዘላለም ኪዳን አድርጎ አጸናለት፤
11እንዲህም አለ፤ “የርስትህ ድርሻ አድርጌ፣
የከነዓንን ምድር እሰጥሃለሁ።”
12ቍጥራቸው ገና ጥቂት ሳለ፣
በርግጥ ጥቂትና መጻተኞች ሳሉ፣
13ከአንዱ ሕዝብ ወደ ሌላው ሕዝብ፣
ከአንዱም መንግሥት ወደ ሌላው ተንከራተቱ፣
14ማንም እንዲጨቍናቸው አልፈቀደም፤
ስለ እነርሱም ነገሥታትን ገሠጸ፤
15“የቀባኋቸውን አትንኩ፤
በነቢያቴም ላይ ክፉ አታድርጉ።”
16በምድሪቱ ላይ ራብን ጠራ፤
የምግብንም አቅርቦት ሁሉ አቋረጠ፤
17በባርነት የተሸጠውን ሰው፣
ዮሴፍን ከእነርሱ አስቀድሞ ላከ።
18እግሮቹ በእግር ብረት ተላላጡ፤
በዐንገቱም የብረት ማነቆ ገባ።
19የተናገረው ቃል እስኪፈጸምለት፣
የእግዚአብሔር ቃል ፈተነው።
20ንጉሥ ልኮ አስፈታው፤
የሕዝቦችም ገዥ ነጻ አወጣው።
21የቤቱ ጌታ፣
የንብረቱም ሁሉ አስተዳዳሪ አደረገው፤
22ይኸውም ሹማምቱን በራሱ መንገድ ይመራ ዘንድ፣
ሽማግሌዎቹንም ጥበብ ያስተምር ዘንድ ነበር።
23እስራኤል ወደ ግብጽ ገባ፤
ያዕቆብ በካም ምድር መጻተኛ ሆነ።
24 እግዚአብሔር ሕዝቡን እጅግ አበዛ፤
ከጠላቶቻቸውም ይልቅ አበረታቸው፤
25ሕዝቡን እንዲጠሉ፣
በባሪያዎቹም ላይ እንዲያሤሩ ልባቸውን ለወጠ።
26ባሪያውን ሙሴን፣
የመረጠውንም አሮንን ላከ።
27እነርሱም ታምራታዊ ምልክቶችን በመካከላቸው፣
ድንቅ ነገሮቹንም በካም ምድር አደረጉ።
28ጨለማን ልኮ ምድሪቱን ጽልመት አለበሰ፤
እነርሱም በቃሉ ላይ ማመፅን ተዉ።
29ውሃቸውን ወደ ደም ለወጠ፤
ዓሦቻቸውንም ፈጀ።
30ምድራቸውም፣ የነገሥታታቸው እልፍኝ ሳይቀር፣
ጓጕንቸር ተርመሰመሰባቸው።
31እርሱ በተናገረ ጊዜ የዝንብ መንጋ መጣ፤
ትንኞችም ምድራቸውን ወረሩ።
32ዝናባቸውን በረዶ አደረገው፤
ምድራቸውም ሁሉ መብረቅ አወረደ።
33ወይናቸውንና በለሳቸውን መታ፤
የአገራቸውንም ዛፍ ከተከተ።
34እርሱ በተናገረ ጊዜ አንበጣ መጣ፤
ስፍር ቍጥር የሌለውም ኵብኵባ ከተፍ አለ፤
35የምድሪቱንም ዕፀዋት ሁሉ በላ፤
የመሬታቸውንም ፍሬ ሙጥጥ አደረገ፤
36ደግሞም በአገራቸው ያለውን በኵር ሁሉ፣
የኀይላቸውንም ሁሉ በኵራት መታ።
37የእስራኤልንም ሕዝብ ብርና ወርቅ ጭኖ እንዲወጣ አደረገ፤
ከነገዶቻቸውም አንድም አልተደናቀፈም።
38እጅግ ፈርተዋቸው ነበርና፣
ወጥተው ሲሄዱ ግብጽ ደስ አላት።
39ደመናን እንደ መጋረጃ ዘረጋላቸው፤
እሳትም በሌሊት አበራላቸው።
40በለመኑትም ጊዜ፣ ድርጭት አመጣላቸው፤
የሰማይንም እንጀራ አጠገባቸው።
41ዐለቱን ሰነጠቀ፤ ውሃም ተንዶለደለ፤
እንደ ወንዝም በበረሓ ፈሰሰ።
42ለባሪያው ለአብርሃም የሰጠውን፣
ቅዱስ የተስፋ ቃሉን አስቧልና።
43ሕዝቡን በደስታ፣
ምርጦቹንም በእልልታ አወጣቸው።
44የሌሎችን ሕዝቦች ምድር ሰጣቸው፤
የእነዚህንም የድካም ፍሬ ወረሱ፤
45ይህም ሥርዐቱን ይጠብቁ ዘንድ፣
ሕጉንም ይፈጽሙ ዘንድ ነው።
ሃሌ ሉያ።#105፥45 እግዚአብሔር ይመስገን የሚሉ ትርጕሞች አሉ።
Currently Selected:
መዝሙር 105: NASV
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.