መዝሙር 119:41-80

መዝሙር 119:41-80 NASV

እግዚአብሔር ሆይ፤ ምሕረትህ ወደ እኔ ይምጣ፤ ማዳንህም እንደ ቃልህ ይላክልኝ። በቃልህ ታምኛለሁና፣ ለሚሰድቡኝ መልስ እሰጣለሁ። ሕግህን ተስፋ አድርጌአለሁና፣ የእውነትን ቃል ከአፌ ፈጽመህ አታርቅ። ከዘላለም እስከ ዘላለም፣ ሕግህን ዘወትር እጠብቃለሁ። ሥርዐትህን እሻለሁና፣ እንደ ልቤ ወዲያ ወዲህ እመላለሳለሁ። ምስክርነትህን በነገሥታት ፊት እናገራለሁ፤ ይህን በማድረግም ዕፍረት አይሰማኝም። እኔ እወድደዋለሁና፣ በትእዛዝህ ደስ ይለኛል። እጆቼን ወደምወዳቸው ትእዛዞችህ አነሣለሁ፤ ሥርዐትህንም አሰላስላለሁ። ለአገልጋይህ የገባኸውን ቃል ዐስብ፤ በዚያ ተስፋ ሰጥተኸዋልና። ቃልህ ሕያው ያደርገኛልና፣ ይህች በመከራዬ መጽናኛዬ ናት። እብሪተኞች እጅግ ተሣለቁብኝ፤ እኔ ግን ከሕግህ ንቅንቅ አልልም። እግዚአብሔር ሆይ፤ ከጥንት የነበረውን ድንጋጌህን አሰብሁ፤ በዚህም ተጽናናሁ። ሕግህን ከተዉ ክፉዎች የተነሣ፣ ቍጣ ወረረኝ። በእንግድነቴ አገር፣ ሥርዐትህ መዝሙሬ ናት። እግዚአብሔር ሆይ፤ ስምህን በሌሊት ዐስባለሁ፤ ሕግህንም እጠብቃለሁ። ሥርዐትህን እከተላለሁ፤ ይህችም ተግባሬ ሆነች። እግዚአብሔር ዕድል ፈንታዬ ነው፤ ቃልህን ለመታዘዝ ቈርጫለሁ። በፍጹም ልቤ ፊትህን ፈለግሁ፤ እንደ ቃልህ ቸርነትህን አሳየኝ። መንገዴን ቃኘሁ፤ አካሄዴንም ወደ ምስክርህ አቀናሁ። ትእዛዝህን ለመጠበቅ፣ ቸኰልሁ፤ አልዘገየሁምም። የክፉዎች ገመድ ተተበተበብኝ፤ እኔ ግን ሕግህን አልረሳሁም። ስለ ጻድቅ ሥርዐትህ፣ በእኩለ ሌሊት ላመሰግንህ እነሣለሁ። እኔ ለሚፈሩህ ሁሉ፣ ሥርዐትህንም ለሚጠብቁ ባልንጀራ ነኝ። እግዚአብሔር ሆይ፤ ምድር በምሕረትህ ተሞላች፤ ሥርዐትህን አስተምረኝ። እግዚአብሔር ሆይ፤ እንደ ቃልህ፣ ለአገልጋይህ በጎ ውለሃል። በትእዛዞችህ አምናለሁና፣ በጎ ማስተዋልንና ዕውቀትን አስተምረኝ። እንዲያው ሳይቸግረኝ መንገድ ስቼ ሄድሁ፤ አሁን ግን ቃልህን እጠብቃለሁ። አንተ መልካም ነህ፤ የምታደርገው መልካም ነው፤ እንግዲህ ሥርዐትህን አስተምረኝ። እብሪተኞች ስሜን በሐሰት አጠፉ፤ እኔ ግን ትእዛዝህን በፍጹም ልብ እጠብቃለሁ። ልባቸው የሠባና የደነደነ ነው፤ እኔ ግን በሕግህ ደስ ይለኛል። ሥርዐትህን እማር ዘንድ፣ በመከራ ውስጥ ማለፌ መልካም ሆነልኝ። ከአእላፋት ብርና ወርቅ ይልቅ፣ ከአፍህ የሚወጣው ሕግ ይሻለኛል። እጆችህ ሠሩኝ፤ አበጃጁኝም፤ ትእዛዞችህን እንድማር ማስተዋልን ስጠኝ። ቃልህን ተስፋ አድርጌአለሁና፣ የሚፈሩህ እኔን አይተው ደስ ይበላቸው። እግዚአብሔር ሆይ፤ ፍርድህ የጽድቅ ፍርድ፣ ያስጨነቅኸኝም በታማኝነት እንደ ሆነ ዐወቅሁ። ለአገልጋይህ በገባኸው ቃል መሠረት፣ ምሕረትህ ለመጽናናት ትሁነኝ። ሕግህ ደስታዬ ነውና፣ በሕይወት እኖር ዘንድ ቸርነትህ ትምጣልኝ። እብሪተኞች ያለ ምክንያት በደል አድርሰውብኛልና ይፈሩ፤ እኔ ግን ትእዛዞችህን አሰላስላለሁ። አንተን የሚፈሩህ፣ ምስክርነትህንም የሚያውቁ ወደ እኔ ይመለሱ። እኔ እንዳላፍር፣ ልቤ በሥርዐትህ ፍጹም ይሁን።