መዝሙር 122
122
መዝሙር 122
የዳዊት መዝሙረ መዓርግ።
1“ወደ እግዚአብሔር ቤት እንሂድ”
ባሉኝ ጊዜ፣ ደስ አለኝ።
2ኢየሩሳሌም ሆይ፤
እግሮቻችን ከደጅሽ ውስጥ ቆመዋል።
3ኢየሩሳሌም እጅግ እንደ ተጠጋጋች፣
ከተማ ሆና ተሠርታለች።
4ለእስራኤል በተሰጠው ሥርዐት መሠረት፣
የእግዚአብሔርን ስም ለማመስገን፣
የእግዚአብሔር ነገዶች
ወደዚያ ይመጣሉ።
5በዚያም የፍርድ ዙፋኖች የሆኑት፣
የዳዊት ቤት ዙፋኖች ተዘርግተዋል።
6እንዲህ ብላችሁ ለኢየሩሳሌም ሰላም ጸልዩ፤
“የሚወድዱሽ ይለምልሙ፤
7በቅጥርሽ ውስጥ ሰላም ይሁን፤
በምሽግሽም ውስጥ መረጋጋት ይስፈን”።
8ስለ ወንድሞቼና ስለ ባልንጀሮቼ፣
“በውስጥሽ ሰላም ይስፈን” እላለሁ።
9ስለ አምላካችን ስለ እግዚአብሔር ቤት፣
በጎነትሽን እሻለሁ።
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.