የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መዝሙር 18

18
መዝሙር 18
18 ርእስ-50 ተጓ ምብ – 2ሳሙ 22፥1-51
ለመዘምራን አለቃ፤ የእግዚአብሔር ባሪያ የዳዊት መዝሙር፤ እግዚአብሔር ከጠላቶቹ ሁሉና ከሳኦል እጅ በታደገው ጊዜ፣ የዚህን መዝሙር ቃል ለእግዚአብሔር ዘመረ፤
1ጕልበቴ እግዚአብሔር ሆይ፤ እወድድሃለሁ።
2 እግዚአብሔር ዐለቴ፣ መጠጊያዬና ታዳጊዬ ነው፤
አምላኬ የምሸሸግበት ዐለቴ፤
እርሱ ጋሻዬ፣ የድነቴ ቀንድና#18፥2 ቀንድ በዚህ ቦታ ብርታትን ያመለክታል። ዐምባዬ ነው።
3ምስጋና የሚገባውን እግዚአብሔርን እጠራለሁ፤
ከጠላቶቼም እድናለሁ።
4የሞት ገመድ ዐነቀኝ፤
ምናምንቴ ነገርም አጥለቀለቀኝ።
5የሲኦል#18፥5 ወይም የመቃብር ገመድ ተጠመጠመብኝ፤
የሞት ወጥመድም ተጋረጠብኝ።
6በተጨነቅሁ ጊዜ እግዚአብሔርን ጠራሁት፤
እንዲረዳኝም ወደ አምላኬ ጮኽሁ፤
እርሱም ከመቅደሱ ድምፄን ሰማ፤
ጩኸቴም በፊቱ ከጆሮው ደረሰ።
7ምድር ተንቀጠቀጠች፤ ተናወጠችም፤
የተራሮችም መሠረቶች ተናጉ፤
እርሱ ተቈጥቷልና ተንቀጠቀጡ።
8ከአፍንጫው ጢስ ወጣ፤
ከአፉ የሚባላ እሳት ነደደ፤
ከውስጡም ፍሙ ጋለ።
9ሰማያትን ሰንጥቆ ወረደ፤
ከእግሩም በታች ጥቅጥቅ ያለ ደመና ነበረ።
10በኪሩቤል ላይ ተቀምጦ በረረ፤
በነፋስም ክንፍ መጠቀ።
11ጨለማን መሰወሪያው፣ በዙሪያውም አጐበሩ አደረገው፤
በዝናብ ዐዘል ጥቍር ደመናም ተሸፈነ።
12በፊቱ ካለው ብርሃን የተነሣ፣
ደመናት፣ የበረዶ ድንጋይና መብረቅ ወጡ።
13 እግዚአብሔር ከሰማያት አንጐደጐደ፤
የልዑልም ድምፅ አስተጋባ።#18፥13 አንዳንድ የዕብራይስጥ የጥንት ቅጆችና ሰብዓ ሊቃናት (በተጨማሪ 2ሳሙ 22፥14 ይመ፤) እንዲሁ ሲሆኑ፣ አብዛኛዎቹ የዕብራይስጥ የጥንት ቅጆች ግን …አስተጋባ፤ በድንጋይ ዝናብ በድንገተኛ መብረቅ መካከል የሚለውን ይጨምራሉ።
14ፍላጻውን ሰድዶ በተናቸው፤
ታላቅ መብረቆቹንም ልኮ አወካቸው።
15 እግዚአብሔር ሆይ፤ ከተግሣጽህ የተነሣ፣
ከአፍንጫህም እስትንፋስ የተነሣ፣
የባሕር ወለል ታየ፤
የምድር መሠረቶችም ተገለጡ።
16ከላይ እጁን ዘርግቶ ያዘኝ፤
ከጥልቅ ውሆችም ውስጥ አወጣኝ፤
17ከብርቱ ጠላቶቼ አዳነኝ፤
ከሚበረቱብኝ ባላጋሮቼም ታደገኝ።
18እነርሱ በመከራዬ ቀን መጡብኝ፤
እግዚአብሔር ግን ድጋፍ ሆነኝ።
19ወደ ሰፊ ስፍራ አወጣኝ፤
ደስ ተሰኝቶብኛልና አዳነኝ።
20 እግዚአብሔር እንደ ጽድቄ መለሰልኝ፤
እንደ እጄም ንጽሕና ከፈለኝ፤
21እግዚአብሔርን መንገድ ጠብቄአለሁና፤
አምላኬንም በመተው ክፉ አላደረግሁም።
22ሕጎቹ ሁሉ በፊቴ ናቸው፤
ከሥርዐቱም ዘወር አላልሁም።
23በፊቱ ነቀፋ አልነበረብኝም፤
ራሴንም ከኀጢአት ጠብቄአለሁ።
24 እግዚአብሔር እንደ ጽድቄ መጠን፣
በፊቱ እንደ እጄም ንጽሕና ከፈለኝ።
25ለታማኝ ሰው ታማኝ መሆንህን፣
ለፍጹም ሰው ፍጹም መሆንህን ታሳያለህ።
26ለንጹሕ ሰው አንተም ንጹሕ መሆንህን፣
ለጠማማ ሰው ግን አንተም ጠማማ መሆንህን ታሳያለህ።
27አንተ ትሑታንን ታድናለህ፤
ትዕቢተኛውን ዐይን ግን ታዋርዳለህ።
28 እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ መብራቴን ታበራለህ፤
አምላኬ፤ ጨለማዬን ያበራል።
29በአንተ ጕልበት በሰራዊት ላይ እረማመዳለሁ፤#18፥29 ወይም …በመሰናክል ውስጥ መሮጥ እችላለሁ
በአምላኬም ኀይል ቅጥር እዘላለሁ።
30የአምላክ መንገዱ ፍጹም ነው፤
እግዚአብሔርም ቃል የነጠረ ነው።
መጠጊያ ለሚያደርጉት ሁሉ፣ ጋሻ ነው።
31እግዚአብሔር በቀር ማን አምላክ አለ?
ከአምላካችንስ በቀር ዐለት ማን ነው?
32ኀይልን የሚያስታጥቀኝ፣
መንገዴንም የሚያቀና እርሱ እግዚአብሔር ነው።
33እግሮቼን እንደ ብሖር እግሮች ያደርጋል፤
በከፍታዎችም ላይ አጽንቶ ያቆመኛል።
34እጆቼን ለጦርነት ያሠለጥናቸዋል፤
ክንዶቼም የናስ ቀስት መገተር ይችላሉ።
35የማዳንህን ጋሻ ሰጥተኸኛል፤
ቀኝ እጅህም ደግፋ ይዛኛለች፤
ድጋፍህ ታላቅ አድርጎኛል።
36ከሥሬ ያለውን ስፍራ ለአረማመዴ አሰፋህልኝ፤
እግሬም አልተንሸራተተም።
37ጠላቶቼን አሳድጄ ያዝኋቸው፤
እስኪጠፉም ድረስ ወደ ኋላ አልተመለስሁም።
38እንዳያንሰራሩ አድርጌ አደቀቅኋቸው፤
ከእግሬም ሥር ወደቁ።
39አንተ ለጦርነት ኀይልን አስታጠቅኸኝ፤
ባላንጦቼ እግሬ ላይ እንዲደፉ አደረግህ።
40ጠላቶቼ ወደ ኋላቸው እንዲሸሹ አደረግህ፤
እኔም የሚጠሉኝን አጠፋኋቸው።
41ለርዳታ ጮኹ፤ የሚያስጥላቸው ግን አልነበረም፤
ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፤ እርሱ ግን አልመለሰላቸውም።
42ነፋስ ጠርጎ እንደሚወስደው ትቢያ አደቀቅኋቸው፤
እንደ መንገድ ላይ ጭቃም ረገጥኋቸው።
43በሕዝብ ከተቃጣብኝ አደጋ አዳንኸኝ፤
የሕዝቦች መሪ አድርገህ አስቀመጥኸኝ፤
የማላውቀውም ሕዝብ ተገዛልኝ።
44የባዕድ አገር ሰዎች ይፈሩኛል፤
እንደ ሰሙኝም ወዲያውኑ ይታዘዙኛል።
45ባዕዳን ፈሩ፤
ከምሽጋቸውም እየተንቀጠቀጡ ወጡ።
46 እግዚአብሔር ሕያው ነው! ዐለቴ የተባረከ ይሁን!
የድነቴ አምላክ ከፍ ከፍ ይበል።
47እርሱ በቀሌን የሚመልስልኝ፣
አሕዛብንም የሚያስገዛልኝ አምላክ ነው፤
48ከጠላቶቼም የሚታደገኝ እርሱ ነው።
አንተ ከባላንጦቼ በላይ ከፍ ከፍ አደረግኸኝ፤
ከጨካኞች አዳንኸኝ።
49ስለዚህ እግዚአብሔር ሆይ፤ በአሕዛብ መካከል አመሰግንሃለሁ፤
ስምህንም በመዝሙር እወድሳለሁ።
50እርሱ ላነገሠው ታላላቅ ድሎችን ይሰጣል፤
ጽኑ ፍቅሩንም ለቀባው፣
ለዳዊትና ለዘሩ ለዘላለም ይገልጣል።

Currently Selected:

መዝሙር 18: NASV

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ