መዝሙር 19
19
መዝሙር 19
ለመዘምራን አለቃ፤ የዳዊት መዝሙር።
1ሰማያት የእግዚአብሔርን ክብር ይናገራሉ፤
የሰማይም ጠፈር የእጁን ሥራ ያውጃሉ።
2ቀን ለሌላው ቀን ይናገራል፤
ሌሊትም ለሌሊት ዕውቀትን ይገልጣል፤
3ንግግር የለም፤ ቃል የለም፤
ድምፃቸው በጆሮ የሚሰማ አይደለም።#19፥3 ወይም የሚናገሩት የላቸውም፤ ቃላት የለም፤ ከርሱ ምንም ድምፅ አይሰማም
4ያም ሆኖ ድምፃቸው በምድር ሁሉ፣
ቃላቸውም#19፥4 ሰብዓ ሊቃናት የሩምና ሱርስት እንዲሁ ሲሆኑ፣ ዕብራይስጡ ግን ድንበራቸው ይላል። እስከ ዓለም ዳርቻ ይወጣል።
እርሱ በሰማያት ለፀሓይ ድንኳን ተክሏል፤
5ፀሓይም ከእልፍኙ እንደሚወጣ ሙሽራ ይወጣል፤
ወደ ግቡም እንደሚሮጥ ብርቱ ሰው ደስ ይለዋል።
6መውጫው ከሰማያት ዳርቻ ነው፤
ዑደቱም እስከ ሌላው ዳርቻ ነው፤
ከትኵሳቱም የሚሰወር የለም።
7የእግዚአብሔር ሕግ ፍጹም ነው፤
ነፍስንም መልሶ ያለመልማል፤
የእግዚአብሔር ሥርዐት የታመነ ነው፤
አላዋቂውን ጥበበኛ ያደርጋል።
8የእግዚአብሔር ሕግጋት ትክክል ናቸው፤
ልብን ደስ ያሰኛሉ።
የእግዚአብሔር ትእዛዝ ብሩህ ነው፤
ዐይንን ያበራል።
9 እግዚአብሔርን መፍራት ንጹሕ ነው፤
ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል።
የእግዚአብሔር ፍርድ የታመነ፣
ሁለንተናውም ጻድቅ ነው።
10ከወርቅ ይልቅ የከበረ፣
እጅግ ከጠራ ወርቅም የተሻለ ነው፤
ከማር ይልቅ ይጣፍጣል፤
ከማር ወለላም ይበልጥ ይጥማል።
11ደግሞም አገልጋይህ በርሱ ጥንቃቄ ያደርጋል፤
እርሱንም መጠበቅ ወሮታ አለው።
12ስሕተቱን ማን ሊያስተውል ይችላል?
ከተሰወረ በደል አንጻኝ።
13ባሪያህን ከድፍረት ኀጢአት ጠብቅ፤
እንዳይሠለጥንብኝም ርዳኝ፤
ያን ጊዜ ያለ እንከን እሆናለሁ፤
ከታላቅ በደልም እነጻለሁ።
14ዐለቴና አዳኜ እግዚአብሔር ሆይ፤
የአፌ ቃልና የልቤ ሐሳብ፣
በፊትህ ያማረ ይሁን።
Currently Selected:
መዝሙር 19: NASV
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.