የሐዋርያት ሥራ 21
21
ጳውሎስ ወደ ኢየሩሳሌም መሄዱ
1ከእነርሱ ከተለየን በኋላ በመርከብ ተሳፈርንና በቀጥታ ቆስ ወደምትባል ደሴት ሄድን፤ በማግስቱም ወደ ሩድ ደሴት ደረስን፤ ከዚያም ወደ ጳጥራ ከተማ ሄድን። 2እዚያም ወደ ፊንቄ አገር የምትሄድ መርከብ አገኘንና በእርስዋ ተሳፍረን፤ ጒዞአችንን ቀጠልን። 3የቆጵሮስን ደሴት በስተግራችን ትተን ወደ ሶርያ አገር ተጓዝንና ወደ ጢሮስ ወደብ ሄድን፤ መርከቡ ጭነቱን እዚያ ማራገፍ ነበረበት። 4እዚያ ምእመናንን ፈልገን አገኘንና ከእነርሱ ጋር ሰባት ቀን ቈየን። እነርሱም በመንፈስ ቅዱስ ተመርተው ጳውሎስን “ወደ ኢየሩሳሌም አትሂድ” ብለው ነገሩት። 5እዚያ የምንቈይበት ጊዜ ሲያልቅ ተለይተናቸው ጒዞአችንን ቀጠልን፤ ሁሉም ከሚስቶቻቸውና ከልጆቻቸው ጋር ሆነው እስከ ከተማው ውጪ ድረስ ሸኙን፤ በባሕሩም ዳር ተንበርክከን ከጸለይን በኋላ ተሰነባበትን። 6ከዚህ በኋላ እኛ በመርከብ ስንሳፈር እነርሱ ወደ ቤታቸው ተመለሱ።
7ከጢሮስ ተነሥተን ወደ ጴጤሌማይስ ደረስን፤ እዚያ ከአማኞች ጋር ተገናኝተን ሰላምታ ከተለዋወጥን በኋላ ከእነርሱ ጋር አንድ ቀን አሳለፍን። 8በማግስቱ ከዚያ ወጥተን ወደ ቂሳርያ ሄድን፤ እዚያ ከሰባቱ ዲያቆናት አንዱ ወደ ሆነው ወደ ወንጌላዊው ፊልጶስ ቤት ገባንና ከእርሱ ጋር ተቀመጥን። #ሐ.ሥ. 6፥5፤ 8፥5። 9እርሱ ትንቢት የመናገር ስጦታ ያላቸው አራት ያላገቡ ሴቶች ልጆች ነበሩት። 10ለብዙ ቀኖች እዚያ በተቀመጥንበት ጊዜ አጋቦስ የሚባል ነቢይ ከይሁዳ ምድር መጣ። 11ይህ ነቢይ ወደ እኛ ቀረበ፤ የጳውሎስን መታጠቂያ ወስዶ የገዛ እጆቹንና እግሮቹን አሰረና “መንፈስ ቅዱስ የዚህን መታጠቂያ ባለቤት በኢየሩሳሌም ያሉ አይሁድ እንደዚህ አስረው ለአሕዛብ አሳልፈው ይሰጡታል ይላል” አለ።
12ይህንን በሰማን ጊዜ እኛም እዚያ የነበሩ ሰዎችም ጳውሎስ ወደ ኢየሩሳሌም እንዳይሄድ ለመንነው። 13ጳውሎስ ግን “እንደዚህ እያለቀሳችሁ ስለምን ልቤን በሐዘን ትሰብሩታላችሁ? እኔ ስለ ጌታ ኢየሱስ ስም በኢየሩሳሌም ለመታሰር ብቻ ሳይሆን ለመሞትም ዝግጁ ነኝ” ሲል መለሰ።
14ምክራችንን አልቀበልም ባለን ጊዜ “እንግዲህ የጌታ ፈቃድ ይሁን” ብለን ተውነው።
15እዚያ ጥቂት ቀኖች ከቈየን በኋላ ዕቃችንን አዘጋጅተን ወደ ኢየሩሳሌም ሄድን። 16በቂሳርያ የነበሩ አንዳንድ ምእመናን አብረውን መጡ፤ እነርሱም በምናሶን ቤት እንድናርፍ ወደ እርሱ ቤት መሩን፤ ይህ ሰው ቀደም ብሎ ያመነ፥ የቆጵሮስ ተወላጅ ነበር።
ጳውሎስ በኢየሩሳሌም ያዕቆብን መጐብኘቱ
17ኢየሩሳሌም በደረስን ጊዜ ምእመናን በደስታ ተቀበሉን። 18በማግስቱ ጳውሎስ ከእኛ ጋር ወደ ያዕቆብ ሄደ፤ የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎች ሁሉ እዚያ ነበሩ። 19ጳውሎስ ለሁሉም ሰላምታ ከሰጠ በኋላ በእርሱ አማካይነት እግዚአብሔር በአሕዛብ መካከል ያደረገውን ሁሉ አንድ በአንድ ተረከላቸው። 20ይህን በሰሙ ጊዜ ሁሉም ጌታን አመሰገኑ፤ ጳውሎስንም እንዲህ አሉት፦ “ወንድም ሆይ! በብዙ ሺህ የሚቈጠሩ ምእመናን በአይሁድ መካከል እንዳሉና ሁሉም ለሕግ ቀናተኞች እንደ ሆኑ ታውቃለህ፤ 21አንተ በአሕዛብ መካከል የሚኖሩትን አይሁድ ሁሉ ‘ልጆቻችሁን አትግረዙ ወይም ሥርዓቶችን አትፈጽሙ’ እያልክ በማስተማር የሙሴን ሕግ እንዲሽሩ ታደርጋለህ እየተባለ የሚወራውን ሰምተዋል። #11፥28። 22እንግዲህ ምን ማድረግ ይሻላል? መምጣትህን በእርግጥ ይሰማሉ፤ 23ስለዚህ እኛ የምንልህን አድርግ፤ በእኛ መካከል ስለት ያለባቸው አራት ሰዎች አሉ። #ዘኍ. 6፥13-21። 24እነርሱን ውሰድና ከእነርሱ ጋር ሆነህ ራስህን አንጻ፤ ጠጒራቸውንም እንዲላጩ ለቤተ መቅደስ የሚሰጠውን የመባ ገንዘብ ክፈልላቸው፤ ይህን ብታደርግ በአንተ ላይ የተወራው ሁሉ ከንቱ መሆኑንና አንተም ራስህ ለሕግ ታዛዥ መሆንክህን ሁሉም ያውቃሉ። 25ከአሕዛብ ወገን ያመኑት ግን ‘ለጣዖት በመሠዋቱ ምክንያት የረከሰ ምግብ አትብሉ፤ ደምም አትብሉ፤ ታንቆ የሞተ እንስሳ ሥጋ አትብሉ፤ ከዝሙት ራቁ’ የሚለውን ውሳኔ የያዘ ደብዳቤ ጽፈን ልከንላቸዋል።” #ሐ.ሥ. 15፥29።
26ከዚህ በኋላ ጳውሎስ ሰዎቹን ወሰደና በማግስቱ ከእነርሱ ጋር ራሱን አነጻ፤ የሚነጹባቸው ቀኖች መቼ እንደሚሆንና ስለ እያንዳንዱም የሚሰጠው የመባ ገንዘብ የሚከፈልበት ጊዜ መቼ እንደሚሆን ለማስታወቅ ወደ ቤተ መቅደስ ገባ።
ጳውሎስ በቤተ መቅደስ መያዙ
27ሰባቱ ቀን ሊፈጸም ሲቃረብ ከእስያ የመጡ አይሁድ ጳውሎስን በቤተ መቅደስ በማየታቸው ሕዝቡን ሁሉ አሳድመው ያዙት፤ 28“የእስራኤል ሰዎች ሆይ! እርዱን! ሕዝባችንንና ሕጋችንን፥ ይህንንም ስፍራ እየተሳደበ በየአገሩ ያለውን ሕዝብ ሁሉ የሚያስተምር ይህ ሰው ነው፤ ይህም አልበቃ ብሎት አሕዛብን ወደ ቤተ መቅደስ በማስገባት ይህን የተቀደሰ ስፍራ አርክሶአል!” እያሉ ጮኹ። 29ይህንንም ያሉበት ምክንያት ከዚህ ቀደም የኤፌሶኑን ተወላጅ ጥሮፊሞስን ከእርሱ ጋር በከተማ አይተውት ስለ ነበር እርሱን ጳውሎስ ወደ ቤተ መቅደስ ይዞት የገባ መስሎአቸው ነበር። #ሐ.ሥ. 20፥4።
30ከተማዋ በሙሉ ታወከች፤ ሕዝቡም ሁሉ እየሮጡ በአንድነት መጡና ጳውሎስን ይዘው እየጐተቱ ከቤተ መቅደስ አወጡት፤ የቤተ መቅደሱ በሮችም ወዲያውኑ ተዘጉ። 31ሰዎቹ ጳውሎስን ሊገድሉት በፈለጉ ጊዜ “የኢየሩሳሌም ከተማ በሙሉ ታውካለች” የሚል መልእክት ለሮማውያኑ ጦር አዛዥ ደረሰ። 32ስለዚህ እርሱ ወታደሮችንና የመቶ አለቆችን አስከትሎ በፍጥነት እየሮጠ ወደ ሰዎቹ ሄደ። ሰዎቹም አዛዡንና ወታደሮቹን ባዩ ጊዜ ጳውሎስን መደብደብ ተዉ። 33አዛዡም ቀርቦ ጳውሎስን ያዘውና በሁለት ሰንሰለት እንዲታሰር አዘዘ፤ ከዚህ በኋላ ማን መሆኑንና ምን እንዳደረገ ለማወቅ ፈልጎ ጠየቀ። 34ሕዝቡም አንዳንዶቹ አንድ ነገር ሲሉ፥ ሌሎች ሌላ ነገር ይሉ ነበር፤ አዛዡ ከሕዝቡ ጩኸት የተነሣ እርግጠኛውን ነገር ለማወቅ ስላልቻለ ጳውሎስን ወደ ወታደሮቹ ሰፈር እንዲወስዱት አዘዘ። 35ጳውሎስ ወደ ደረጃው በደረሰ ጊዜ ሕዝብ ሁሉ በብርቱ ቊጣ ተነሣሥቶ አደጋ ሊያደርስበት በመፈለጉ ወታደሮቹ ተሸክመውት ሄዱ። 36ሕዝቡም “ይገደል!” እያሉ በመጮኽ ይከተሉት ነበር።
ጳውሎስ የመከላከያ ንግግር ማድረጉ
37ወታደሮች ወደ ጦር ሰፈራቸው ሊያስገቡት በቀረቡ ጊዜ ጳውሎስ የጦር አዛዡን “አንድ ነገር እንድነግርህ ትፈቅድልኛለህን?” አለው። አዛዡም “የግሪክ ቋንቋ ታውቃለህን? 38ታዲያ፥ አሁን በቅርቡ ብጥብጥ አስነሥቶና አራት ሺህ ነፍሰ ገዳዮች ይዞ ወደ በረሓ የሸሸው ግብጻዊው አንተ አይደለህምን?” አለ።
39ጳውሎስም “እኔ በኪልቅያ በምትገኘውና ዝነኛ በሆነችው በጠርሴስ ከተማ የተወለድኩ አይሁዳዊ ነኝ፤ እባክህ ለሕዝቡ እንድናገር ፍቀድልኝ” አለው።
40እንዲናገር በፈቀደለት ጊዜ ጳውሎስ በደረጃ ላይ ቆሞ ሕዝቡ ዝም እንዲል በእጁ ጠቀሰ፤ ሕዝቡ ጸጥ ባለ ጊዜ በዕብራይስጥ ቋንቋ እንዲህ ሲል መናገር ጀመረ፤
Currently Selected:
የሐዋርያት ሥራ 21: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997