ወደ ዕብራውያን የተላከ መልእክት መግቢያ
መግቢያ
ይህ መልእክት የተጻፈው ከባድ ተቃውሞ ስለ ደረሰባቸው እምነታቸውን ሊተዉ ወደተቃረቡ ክርስቲያኖች ነበር፤ ጸሐፊው ለዕብራውያን አማኞች የሚያረጋግጥላቸው ኢየሱስ ክርስቶስ እውነተኛና የመጨረሻው የእግዚአብሔር መገለጥ መሆኑን በማሳየት ነው። እነዚህ ክርስቲያኖች በእምነታቸው እንዲጸኑ ያበረታታቸዋል፤ ይህንንም በሚያደርግበት ጊዜ ሦስት እውነቶችን አጒልቶ ያሳያል፦
1. በተቀበለው መከራ አማካይነት ለአብ እውነተኛ ታዛዥ የሆነው ኢየሱስ ዘለዓለማዊ የእግዚአብሔር ልጅ ነው፤ የእግዚአብሔር ልጅ በመሆኑም ከብሉይ ኪዳን ነቢያት፥ ከሙሴና ከመላእክት እጅግ የላቀ ነው።
2. ኢየሱስ ከብሉይ ኪዳን ካህናት እጅግ የላቀ ዘለዓለማዊ ካህን መሆኑን እግዚአብሔር ራሱ ተናግሮአል።
3. በኢየሱስ በኩል አማኙ ከኃጢአት፥ ከፍርሃትና ከሞት ይድናል፤ ኢየሱስ ሊቀ ካህናት እንደ መሆኑ በዕብራውያን እምነት ሥርዓቶችና የእንስሳት መሥዋዕት እንደ ጥላ ይታይ የነበረው መዳን እውነተኛ እንዲሆን አድርጎታል።
ጸሐፊው በእስራኤል ታሪክ ዝነኞች የሆኑ ሰዎችን እምነት እንደ ምሳሌ በመጠቀም (ም. 11) አንባቢዎቹ በእምነታቸው እንዲጸኑ ያሳስባቸዋል፤ እንዲሁም በም. 12 አንባቢዎቹ ዐይኖቻቸውን በኢየሱስ ላይ በማተኰር በእምነታቸው እንዲጸኑና ማንኛውም ዐይነት መከራና ሥቃይ ቢደርስባቸው እንዲታገሡ ይመክራቸዋል፤ በመጨረሻም የምክርና የማስጠንቀቂያ ቃል በመስጠት ይደመድማል።
አጠቃላይ የመጽሐፉ ይዘት
መግቢያ፦ እግዚአብሔር በክርስቶስ መገለጡ 1፥1-3
ክርስቶስ ከመላእክት በላይ መሆኑ 1፥4—2፥18
ክርስቶስ ከሙሴና ከኢያሱ በላይ መሆኑ 3፥1—4፥13
የክርስቶስ ክህነት በላይነት 4፥14—7፥28
የክርስቶስ ቃል ኪዳን በላይነት 8፥1—9፥22
የክርስቶስ መሥዋዕትነት ብልጫ 9፥23—10፥39
የእምነት ታላቅነት 11፥1—12፥29
እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት 13፥1-19
የመዝጊያ ጸሎት 13፥20-21
ማጠቃለያ 13፥22-25
Currently Selected:
ወደ ዕብራውያን የተላከ መልእክት መግቢያ: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997