ትንቢተ ሆሴዕ መግቢያ
መግቢያ
ነቢዩ ሆሴዕ፥ ከክርስቶስ ልደት በፊት ሰማርያ በሰባት መቶ ኻያ አንድ ዓመት ከመፍረስዋ ቀደም ብሎ የነበረ ነቢይ ነው። እርሱም ሁኔታዎች አስቸጋሪ በነበሩበት ጊዜ ከነቢዩ አሞጽ በኋላ በሰሜናዊው የእስራኤል መንግሥት የትንቢት ቃል አስተላልፎአል። ሆሴዕ በጣም አጒልቶ ያሳየው ሕዝቡ የጣዖት አምልኮን ስለ መከተላቸውና በእግዚአብሔር ላይ የነበራቸውን እምነት ስለ ማጓደላቸው ነው፤ ሆሴዕ ይህንን የሕዝቡን አለመታመን ለማስረዳት ታማኝ ካልሆነች ሴት ጋር የነበረውን ጋብቻ እንደ ምሳሌ አድርጎ ይጠቀማል፤ ልክ ሚስቱ ጎሜር ለእርሱ ታማኝ እንዳልሆነች ሁሉ የእግዚአብሔርም ሕዝብ አምላካቸውን ትተዋል፤ በዚህም ምክንያት ፍርድ በእስራኤል ላይ ሊመጣ ነው፤ ይሁን እንጂ በመጨረሻ እግዚአብሔር ለሕዝቡ ያለው የማያቋርጥ ፍቅር ስለሚልቅ፥ እግዚአብሔር ሕዝቡን ወደ ራሱ መልሶ በእርሱና በሕዝቡ መካከል ያለውን ኅብረት ያድሳል፤ ይህም ታላቅ ፍቅር በሚከተለው ቃል ተገልጦአል፦ “እስራኤል ሆይ! እንዴት እተውሃለሁ? እንዴትስ አሳልፌ እሰጥሃለሁ? ... ለአንተ ያለኝ ፍቅር ታላቅ ስለ ሆነ፥ ይህን ሁሉ እንዳደርግ ልቤ አይፈቅድልኝም!” ም. 11፥8።
አጠቃላይ የመጽሐፉ ይዘት
1. የሆሴዕ ቤተሰብ እምነተቢስ ለሆኑት የጌታ ሕዝብ ምሳሌ መሆናቸው (1፥1—3፥5)
2. እግዚአብሔር እስራኤልን፥ ይሁዳንና መሪዎቻቸውን መውቀሱ (4፥1—5፥15)
3. ሕዝቡ ወደ እግዚአብሔር የተመለሰ ማስመሰሉ (6፥1—7፥10)
4. የእስራኤል ሕዝብ በእግዚአብሔር ላይ አለመተማመኑ (7፥11—8፥14)
5. የእስራኤል ሕዝብ የሚገባውን ቅጣት የሚያገኝ መሆኑ (9፥1- 16)
6. ለእስራኤል ሕዝብ የተሰጠ ማስጠንቀቂያ (10፥1-15)
7. እግዚአብሔር ለሕዝቡ ያለው ፍቅር (11፥1-11)
8. እግዚአብሔር በሕዝቡ ላይ ያሳለፈው ፍርድ (11፥12—13፥16)
9. የኃጢአት ይቅርታና የበረከት ተስፋ (14፥1-9)
Currently Selected:
ትንቢተ ሆሴዕ መግቢያ: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997