መጽሐፈ መሳፍንት 12
12
ዮፍታሔና ኤፍሬማውያን
1የኤፍሬም ሰዎች ለጦርነት ተዘጋጅተው የዮርዳኖስን ወንዝ በመሻገር ወደ ጻፎን በደረሱ ጊዜ ዮፍታሔን “ዐሞናውያንን ለመውጋት ወሰን አልፈህ ስትሄድ እኛን ያልጠራኸን ለምንድን ነው? እንግዲህ እኛም ቤትህን በላይህ እናቃጥለዋለን!” አሉት።
2ዮፍታሔም እንዲህ አላቸው፤ “እኔና ሕዝቤ ከዐሞናውያን ጋር በብርቱ ተጣልተን በነበረበት ጊዜ እናንተን ጠርቼአችሁ ነበር፤ ነገር ግን ከእነርሱ ጥቃት አላዳናችሁኝም፤ 3እናንተ እኔን ለመርዳት አለመፈለጋችሁን ባየሁ ጊዜ ለሕይወቴ ሳልሳሳ እነርሱን ለመውጋት ወሰኑን ተሻግሬ ሄድሁ፤ እግዚአብሔርም በእነርሱ ላይ ድልን አቀዳጀኝ። ታዲያ፥ አሁን እኔን ለመውጋት የተነሣችሁበት ምክንያት ምንድን ነው?” 4ከዚህ በኋላ ዮፍታሔ የገለዓድን ሰዎች አሰባስቦ በኤፍሬም ሰዎች ላይ አደጋ በመጣል ድል አደረጋቸው፤ የኤፍሬም ሰዎች “እናንተ በኤፍሬምና በምናሴ ግዛት ውስጥ የምትኖሩ ገለዓዳውያን ኤፍሬምን ከድታችሁ የመጣችሁ ናችሁ!” ይሉአቸው ነበር። 5የኤፍሬም ሰዎች እንዳያመልጡ ለማድረግ ገለዓዳውያን የዮርዳኖስን መሻገሪያ ቦታዎች ሁሉ ዘግተው ያዙ፤ ለማምለጥ የሚሞክር ማንኛውም የኤፍሬም ሰው ለመሻገር ፈቃድ ቢጠይቅ ገለዓዳውያን “አንተ የኤፍሬም ሰው ነህን?” ብለው ይጠይቁት ነበር፤ “አይደለሁም!” ካለ፥ 6“እስቲ ሺቦሌት” በል ይሉታል፤ እርሱ ግን “ሺ” የሚለውን ፊደል አስተካክሎ መናገር ስለማይችል “ሲቦሌት” ይላል፤ ከዚህ በኋላ እርሱን ይዘው የዮርዳኖስ መሸጋገሪያ ከሆኑት ስፍራዎች በአንዱ ይገድሉታል፤ ያንጊዜም በዚሁ ዐይነት አርባ ሁለት ሺህ የኤፍሬም ሰዎች ተገደሉ።
7ዮፍታሔ ስድስት ዓመት ሙሉ የእስራኤል መሪ ከሆነ በኋላ ሞተ፤ በትውልድ አገሩ በገለዓድ በምትገኘው በአንዲት ከተማ ተቀበረ።
ኢብጻን፥ ኤሎን፥ ዓብዶን
8ከዮፍታሔ ቀጥሎ የቤተልሔም ተወላጅ የሆነው ኢብጻን የእስራኤል መሪ ሆነ፤ 9ኢብጻን ሠላሳ ወንዶችና ሠላሳ ሴቶች ልጆች ነበሩት፤ ሴቶች ልጆቹን ከጐሣው ውጪ ከሆኑ ወንዶች ጋር አጋባቸው፤ እንዲሁም ከጐሣው ውጪ የሆኑ ሴቶች ልጆችን አምጥቶ ከወንዶች ልጆቹ ጋር እንዲጋቡ አደረገ፤ ኢብጻን ሰባት ዓመት የእስራኤል መሪ ሆነ። 10ኢብጻንም ሞቶ በቤተልሔም ተቀበረ።
11ከኢብጻን ቀጥሎ የዛብሎን ወገን የሆነው ኤሎን እስራኤልን ዐሥር ዓመት መራ፤ 12ከዚያም በኋላ ሞተ፤ በዛብሎን ግዛት በምትገኘው በአያሎንም ምድር ተቀበረ።
13ከኤሎን ቀጥሎ የፒርዓቶን ተወላጅ የሆነው የሂሌል ልጅ ዓብዶን የእስራኤል መሪ ሆነ፤ 14ዓብዶን በሰባ አህዮች ላይ ተቀምጠው የሚጋልቡ አርባ ወንዶች ልጆችና ሠላሳ የልጅ ልጆች ነበሩት፤ ዓብዶን ስምንት ዓመት የእስራኤል መሪ ሆነ። 15ከዚያም በኋላ ዓብዶን ሞተ፤ ኮረብታማም በሆነው በዐማሌቃውያን አገር በኤፍሬም ግዛት በምትገኘውም በፒርዓቶን ተቀበረ።
Currently Selected:
መጽሐፈ መሳፍንት 12: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997