መጽሐፈ መሳፍንት 5
5
የዲቦራና የባራቅ መዝሙር
1በዚያን ቀን ዲቦራና የአቢኒዓም ልጅ ባራቅ ይህን መዝሙር ዘመሩ፦
2መሪዎች እስራኤልን ስለ መሩ፥
ሕዝቡም በፈቃደኛነት ራሱን ስላቀረበ፤
እግዚአብሔርን አመስግኑ!
3እናንተ ነገሥታት ስሙ!
እናንተም አለቆች አድምጡ!
እኔ ለእግዚአብሔር፥ እዘምራለሁ፤
ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር አዜማለሁ።
4እግዚአብሔር ሆይ!
ከኤዶም ተራራ በተነሣህ ጊዜ፥
በኤዶምም ምድር ላይ በተራመድህ ጊዜ
ምድር ተንቀጠቀጠች፤
ሰማያት ዝናብን አዘነቡ፤
አዎ! ውሃ ከደመናዎች ወደታች ጐረፈ።
5በእስራኤል አምላክ በእግዚአብሔር ፊት፥
በሲናው አምላክ ፊት፥
ተራራዎች ተናወጡ። #ዘፀ. 19፥18።
6በዐናት ልጅ በሻምጋርና በያዔል ዘመን፥
የሲራራ ነጋዴዎች
በምድሪቱ አያልፉም ነበር፤
መንገደኞችም ተደብቀው በዘወርዋራ መንገድ ይሄዱ ነበር፤ #5፥6 ሲራራ፦ በቡድን ተሰባስበው የተለያዩ ሸቀጦችን በእንስሶች በመጫን ከአንድ ክፍል ወደ ሌላ ከፍ አብረው የሚጓዙ ነጋዴዎች።
7አንቺ ዲቦራ ነሽ፥
በእስራኤል መካከል እንደ እናት ሆነሽ እስከ ተነሣሽ ድረስ
በእስራኤል ዘንድ
የተረፉ ኀያላን አልነበሩም።
8እስራኤላውያን ቀድሞ የማያውቁአቸውን
ባዕዳን አማልክትን በመረጡ ጊዜ፥
በምድሪቱ ላይ ጦርነት ሆነ፤
ከአርባ ሺህ እስራኤላውያን
ጋሻና ጦር የያዘ አንድ ሰው እንኳ አልነበረም!
9ልቤ ከእስራኤል የጦር አዛዦች ጋር ነው፤
እንዲሁም ደስ ብሎአቸው በበጎ ፈቃድ ከተነሣሡት ጋር ነው፤
እግዚአብሔር ይመስገን!
10እናንተ ኮርቻ በተጫኑ በነጫጭ አህዮች ላይ ተቀምጣችሁ የምትጓዙ፥
እናንተ በምቹና በአማረ ግላስ ላይ የምትንደላቀቁ፥
እናንተ በእግር የምትንሸራሸሩ፥
ስለዚህ ነገር ተናገሩ።
11እነሆ አድምጡ!
ውሃ በሚቀዳባቸው ጒድጓዶች ዙሪያ የሚሰማው
የብዙ ሰዎች ድምፅ፥
የእግዚአብሔርን ድል ያበሥራል፤
የእስራኤልንም ሕዝብ ድል አድራጊነት ይናገራል።
ከዚህ በኋላ የእግዚአብሔር ሕዝብ፥
ከከተሞቻቸው ተሰልፈው ወረዱ።
12ዲቦራ ሆይ! ንቂ!
ንቂ! ንቂ! መዝሙርም ዘምሪ!
የአቢኒዔም ልጅ ባራቅ ሆይ! ተነሣ!
ምርኮህንም እየመራህ ወደ ፊት ገሥግሥ!
13ከዚህ በኋላ ቀሪዎቹ ወደ መኳንንቱ ወረዱ፤
የእግዚአብሔር ሕዝብ ስለ እኔ ኀያላኑን ለመውጋት ወረዱ።
14ቀድሞ ዐማሌቃውያን ይኖሩበት ከነበረው ከኤፍሬም ወታደሮች መጡ፤
ሌሎችም ከብንያም መጡ።
ከማኪር መሪዎች፥
ከዛብሎንም በትረ መንግሥትን
የሚይዙ መጡ።
15የይሳኮር መሪዎች ከዲቦራ ጋር መጡ፤
አዎ፥ ይሳኮርም ባራቅም መጡ፤
ወደ ሸለቆው ተከተሉት፤
ነገር ግን የሮቤል ነገድ ለሁለት ተከፈለ፤
ለመምጣት ወይም ላለመምጣት አመነታ።
16ለምን በበጎች መካከል ዘገየህ?
ለበጎች የሚደረገውን ፉጨት ለመስማት ነውን?
ለመምጣት ወይም ላለመምጣት አመነታ።
17የጋድ ነገድ ከዮርዳኖስ ማዶ ቈየ፤
የዳን ነገድ ለምን በመርከብ ውስጥ ኖረ?
የአሴር ነገድ በባሕር ጠረፍ ቀረ፤
በወደብ አጠገብም ኖረ።
18የዛብሎን ሕዝቦች፥
ራሳቸውን ለሞት አሳልፈው ሰጡ።
19በመጊዶ ውሃ አጠገብ በታዕናክ፥
ነገሥታቱ መጥተው ተዋጉ፤
ከዚያም የከነዓንን ነገሥታት ተዋጉ፤
የብር ምርኮ አላገኙም።
20በሰማይ ከዋክብት ተዋጉ፤
በሂደታቸው ሲሣራንም ጦርነት ገጠሙት።
21የቂሶን ጐርፍ ጠራረጋቸው፤
የጥንቱ የቂሶን ወንዝ በጐርፉ ወሰዳቸው፤
ነፍሴ ሆይ! በርቺ! ገሥግሺ!
22ፈረሰኞች እየጋለቡ ሲመጡ
የፈረሶቹ ኮቴዎች የነጐድጓድ ድምፅ አሰሙ።
23የእግዚአብሔር መልአክ እንዲህ አለ፤
“ሜሮዝን ርገሙ!
እዚያ የሚኖሩትን ሁሉ ፈጽማችሁ ርገሙ!
እነርሱ በእግዚአብሔር ጐን አልቆሙም፤
ስለ እርሱም ለመዋጋት አልተሰለፉም።”
24የቄናዊው የሔቤር ሚስት ያዔል፥
ከሴቶች ሁሉ ይልቅ የተባረከች ትሁን፤
በድንኳን ከሚኖሩ ሴቶችም ሁሉ ይልቅ የተባረከች ትሁን፤
25ሲሣራ “ውሃ አጠጪኝ” አላት፤
እርስዋ ግን ወተት አቀረበችለት፤
በተከበረ ጽዋ እርጎ አመጣችለት።
26እንዲሁም በአንድ እጅዋ የድንኳን ካስማ፥
በቀኝ እጅዋ የሠራተኛ መዶሻ ያዘች፤
ሲሣራንም መታ የራስ ቅሉን አደቀቀችው፤
ጆሮ ግንዱንም ቸነከረችው።
27በእግሮችዋ ሥር ተዝለፍልፎ ወደቀ፤
በእግሮችዋ ሥር ተደፋ፤
በወደቀበትም በዚያው ሞተ።
28የሲሣራ እናት በመስኮት ሆና ተመለከተች፤
በዐይነ ርግብ ቀዳዳም አተኲራ አየች፤
“የልጄ ሠረገላ ለምን ዘገየ?
የሠረገላዎቹ ፈረሶች የኮቴ ድምፅስ ለምን ዘገየ?” ስትል ጠየቀች።
29ጥበበኞች የሆኑ ወይዛዝሮችዋም መልስ ሰጡአት፤
በእርግጥ እርስዋ ለራስዋ መልስዋን አገኘች።
30“ምርኮ አግኝተው በመካከላቸው እየተከፋፈሉ አይደለምን?
አንድ ወይም ሁለት ቈነጃጅት ለያንዳንዱ ወንድ፥
ለሲሣራ በልዩ ልዩ ቀለማት ያጌጠ የልብስ ምርኮ፥
ለእኔም ለአንገቴ በአንገቴ ላይ
በሁለት እጥፍ የተጠለፈ ዝንጒርጒር ልብስ፥”
31እግዚአብሔር ሆይ!
ጠላቶችህን ሁሉ በዚህ ዐይነት አጥፋ፤
ወዳጆችህ ግን እንደ ንጋት ፀሐይ ይድመቁ።
ከዚህ በኋላ በምድሪቱ ላይ አርባ ዓመት ሙሉ ሰላም ሆነ።
Currently Selected:
መጽሐፈ መሳፍንት 5: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997