ትንቢተ ኤርምያስ 27

27
ኤርምያስ የተሸከመው ቀንበር
1የኢዮስያስ ልጅ ሴዴቅያስ በይሁዳ ከነገሠ በኋላ ወዲያውኑ እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፦ #2ነገ. 24፥18-20፤ 2ዜ.መ. 36፥11-13። 2“የጠፍር ማሰሪያና ማነቆ ያለው ቀንበር ከእንጨት ሠርተህ በጫንቃህ ላይ ተሸከም። 3በኢየሩሳሌም ወደሚኖረው ወደ ይሁዳ ንጉሥ ሴዴቅያስ በመጡት መልእክተኞች በኩል ወደ ኤዶም፥ ሞአብ፥ ዐሞን፥ እንዲሁም ወደ ጢሮስና ሲዶና ነገሥታት መልእክት ላከ። 4ለጌቶቻቸው የሚያደርሱትን ይህን የእኔን የሠራዊት ጌታ የእስራኤል አምላክን መልእክት እንዲያደርሱ ንገራቸው! 5‘በታላቁ ኀይሌና ብርታቴ ዓለምንና የሰውን ዘር እንዲሁም በምድር ላይ የሚኖሩ እንስሶችን ሁሉ ፈጠርኩ፤ ምድርንም የሚገዛ ማን እንደሚሆን እወስናለሁ። 6እነዚህ ሕዝቦች ሁሉ የባቢሎን ንጉሥ በሆነው በአገልጋዬ በናቡከደነፆር ሥልጣን ሥር እንዲገዙለት ያደረግኹ እኔ ነኝ፤ የምድር አራዊትም ሳይቀሩ ይገዙለታል። 7ሕዝቦች ሁሉ ያገለግሉታል፤ እንዲሁም የገዛ ሕዝቡ የሚወድቅበት ዘመን እስኪመጣ ድረስ ለልጁና ለልጅ ልጁ ጭምር ተገዢዎች ይሆናሉ፤ ከዚያም በኋላ የእርሱ ሕዝብ ለኀያላን ሕዝቦችና ለታላላቅ ነገሥታት አገልጋዮች ይሆናሉ።’
8“ነገር ግን ማንኛውም ሕዝብ ወይም መንግሥት ‘እርሱን አላገለግልም፤ በቀንበሩም ሥር ሆኜ አልገዛም’ ቢል ናቡከደነፆር ራሱ እንዲደመስሰው እስከ ፈቀድኩለት ድረስ፥ በጦርነት፥ በራብና በወረርሽኝ እንዲቀጡ አደርጋለሁ። 9ነቢያታችሁንና በጥንቈላ፥ በመተት፥ ወይም የሙታን መናፍስትን በመሳብና ሕልም በማየት ወደ ፊት የሚሆነውን ነገር ሁሉ እናውቃለን የሚሉትን ሁሉ አትስሙአቸው፤ እነርሱ ሁሉ የሚመክሩአችሁ ለባቢሎን ንጉሥ አትገዙም ብለው ነው፤ 10እነርሱ ለእናንተ የሚናገሩት ትንቢት የሐሰት ትንቢት ነው፤ ከትውልድ አገራችሁ ወደ ሩቅ አገር ትወሰዳላችሁ፤ እኔም ስለማሳድዳችሁ ትጠፋላችሁ። 11ነገር ግን በባቢሎን ንጉሥ ቀንበር ሥር ሆኖ የሚገዛለትና የሚያገለግለው ሕዝብ በገዛ ምድሩ እያረሰ እንዲኖር እፈቅድለታለሁ፤ እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።”
12ለይሁዳ ንጉሥ ሴዴቅያስም ይህንኑ ቃል እንዲህ ብዬ ነገርኩት፦ “ለባቢሎን ንጉሥ ብትገብር፥ እርሱንና ሕዝቡንም ብታገለግል በሕይወት መኖር ትችላለህ፤ 13ለምንስ አንተና ሕዝብህ በጦርነት፥ በራብና በቸነፈር ታልቃላችሁ? ለባቢሎን ንጉሥ በማይገዛ በማናቸውም ሕዝብ ላይ ይደርስበታል ብሎ እግዚአብሔር የተናገረውም ይህንኑ ነው። 14ለባቢሎን ንጉሥ አትገዙም፥ ብለው የሚነግሩአችሁን የነቢያት ቃል አትስሙ፤ እነርሱ የሚናገሩት የሐሰት ትንቢት ነው። 15እርሱ ያልላካቸው መሆኑንና እነርሱ በስሙ የሚነግሩአችሁ ሁሉ ውሸት መሆኑን እግዚአብሔር ራሱ ነግሮአችኋል። ስለዚህ እርሱ ያሳድዳችኋል፤ እናንተና ይህን ውሸት የሚነግሩአችሁ ነቢያት ሁሉ ትጠፋላችሁ።”
16ከዚህ በኋላ ለካህናቱና ለሕዝቡ እንዳስታውቅ እግዚአብሔር የሚከተለውን ነገረኝ፤ እንዲህ ብዬም ነገርኳቸው፦ “ ‘የቤተ መቅደሱ ዕቃ ሁሉ ከባቢሎን ተመልሶ በፍጥነት ይመጣል’ እያሉ የሚነግሩአችሁን ነቢያት ሁሉ አትስሙአቸው፤ እነርሱ የሚናገሩት የሐሰት ትንቢት ነው፤ 17ስለዚህ እነርሱን መስማት ትታችሁ ለባቢሎን ንጉሥ ብትገዙለት በሕይወት ትኖራላችሁ፤ ይህችስ ከተማ ስለምን የፍርስራሽ ክምር ሆና ትቀራለች? 18እነርሱ ነቢያት ከሆኑና እኔም የሰጠኋቸው የትንቢት ቃል በእነርሱ ዘንድ ካለ፥ ገና ያልተወሰደው በቤተ መቅደስ፥ በይሁዳ ቤተ መንግሥትና በኢየሩሳሌም የቀረው ዕቃ ሁሉ ወደ ባቢሎን እንዳይወሰድ አደርግ ዘንድ እየተማጠኑ ሁሉን ቻይ የሆንኩትን እኔን እግዚአብሔርን ይጠይቁኝ።”
19-20የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር የይሁዳ ንጉሥ የሆነውን የኢዮአቄምን ልጅ ኢኮንያንን ከይሁዳና ከኢየሩሳሌም ታላላቅ ሰዎች ጋር ወደ ባቢሎን ማርኮ በወሰደው ጊዜ ዐምዶችን፥ ከነሐስ የተሠራውን የውሃ ማጠራቀሚያ፥ የብረት ማስቀመጫዎችንና ሌሎችንም የቤተ መቅደስ ዕቃዎች በኢየሩሳሌም ትቶአቸው ሄዶ ነበር።
21“በኢየሩሳሌም፥ በቤተ መቅደሱና በቤተ መንግሥቱ ስለ ቀሩት ዕቃዎች ሁሉ የእስራኤል አምላክ የሆንኩ እኔ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር የምናገረውን ቃል ስሙ፤ 22ሐሳቤን ወደ እነርሱ እስከምመልስበት ጊዜ ድረስ፥ እነዚህ ዕቃዎች ሁሉ ወደ ባቢሎን ተወስደው በዚያ ይኖራሉ። ከዚያም በኋላ እንደገና መልሼ ወደዚህ ስፍራ አመጣቸዋለሁ፤ እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።”

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ