ማርታም “በመጨረሻው ቀን በትንሣኤ ጊዜ ከሞት እንደሚነሣ ዐውቃለሁ” አለችው። ኢየሱስም “ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ በእኔ የሚያምን ቢሞት እንኳ በሕይወት ይኖራል፤ በሕይወት የሚኖርና በእኔም የሚያምን ሁሉ ፈጽሞ አይሞትም፤ ይህን ታምኛለሽ?” አላት። እርስዋም “አዎ ጌታ ሆይ! አንተ ወደ ዓለም የሚመጣው መሲሕ የእግዚአብሔር ልጅ መሆንህን አምናለሁ” አለችው። ማርታ ይህን ከተናገረች በኋላ ሄደችና እኅትዋን ማርያምን “መምህር መጥቶአል፤ አንቺንም ይጠራሻል” ብላ በስውር ጠራቻት። ማርያም ይህን በሰማች ጊዜ በፍጥነት ተነሥታ ወደ እርሱ ሄደች። ያን ጊዜ ኢየሱስ ማርታ እርሱን ባገኘችበት ስፍራ ነበር እንጂ ወደ መንደር ገና አልገባም ነበር። እርስዋን ለማጽናናት መጥተው በቤት ውስጥ አብረዋት የነበሩ አይሁድ ማርያም በፍጥነት ተነሥታ ስትወጣ አይተው ወደ አልዓዛር መቃብር ሄዳ የምታለቅስ መስሎአቸው ተከተሉአት። ማርያም ኢየሱስ ወደ ነበረበት መጥታ ባየችው ጊዜ በእግሩ ሥር ወደቀችና “ጌታ ሆይ፥ አንተ እዚህ ብትሆን ኖሮ ወንድሜ ባልሞተም ነበር” አለችው። ኢየሱስ እርስዋ ስታለቅስና አብረዋት የመጡትም አይሁድ ሲያለቅሱ ባየ ጊዜ በመንፈሱ እጅግ አዝኖ በመታወክ፥ “የት ነው የቀበራችሁት?” አለ። እነርሱም “ጌታ ሆይ! ና እይ” አሉት። ኢየሱስም እንባውን አፈሰሰ። ስለዚህ አይሁድ “እንዴት ይወደው እንደ ነበረ ተመልከቱ” አሉ። ከእነርሱ አንዳንዶቹ ግን፥ “የዕውርን ዐይኖች ያበራ፥ ይህ ሰው እንዳይሞት ሊያደርግ አይችልም ነበርን?” አሉ። ኢየሱስ በጣም እያዘነ ወደ መቃብሩ ሄደ፤ መቃብሩ በድንጋይ የተዘጋ ዋሻ ነበር። ኢየሱስ “ድንጋዩን አንሡት” አለ። የሟቹ እኅት ማርታ፥ “ጌታ ሆይ፥ ከሞተ አራት ቀን ሆኖታል፤ አሁን ይሸታል” አለችው። ኢየሱስም “ካመንሽ የእግዚአብሔርን ክብር ታያለሽ ብዬሽ አልነበረምን?” አላት። ሰዎቹም ድንጋዩን አነሡት፤ ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ወደ ላይ ተመልክቶ፥ “አባት ሆይ! ስለ ሰማኸኝ አመሰግንሃለሁ፤ ሁልጊዜም እንደምትሰማኝ ዐውቃለሁ፤ ነገር ግን ይህን ያልኩት፥ እዚህ የቆሙት ሰዎች አንተ እንደ ላክኸኝ እንዲያምኑ ብዬ ነው” አለ። ኢየሱስ ይህን ከተናገረ በኋላ “አልዓዛር! ና ውጣ!” ብሎ በታላቅ ድምፅ ተናገረ። ሟቹ አልዓዛርም እጆቹና እግሮቹ በመገነዣ እንደ ተገነዙ ከመቃብሩ ወጣ፤ ፊቱም በጨርቅ እንደ ተጠመጠመ ነበር፤ ኢየሱስም “ፍቱትና ተዉት ይሂድ!” አላቸው። ማርያምን ለማጽናናት መጥተው ከነበሩት አይሁድ ብዙዎቹ ያደረገውን አይተው በኢየሱስ አመኑ።
የዮሐንስ ወንጌል 11 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የዮሐንስ ወንጌል 11:24-45
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች