የዮሐንስ ወንጌል 11:24-45

የዮሐንስ ወንጌል 11:24-45 አማ54

ማርታም፦ “በመጨረሻው ቀን በትንሣኤ እንዲነሣ አውቃለሁ” አለችው። ኢየሱስም፦ “ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ የሚያምንብኝ ቢሞት እንኳ ሕያው ይሆናል፤ ሕያው የሆነም የሚያምንብኝ ሁሉ ለዘላለም አይሞትም፤ ይህን ታምኚያለሽኝ?” አላት። እርስዋም፦ “አዎን ጌታ ሆይ፤ አንተ ወደ ዓለም የሚመጣው ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆንህ እኔ አምናለሁ” አለችው። ይህንም ብላ ሄደች እኅትዋንም ማርያምን በስውር ጠርታ፦ “መምህሩ መጥቶአል ይጠራሽማል” አለቻት። እርስዋም በሰማች ጊዜ ፈጥና ተነሣች ወደ እርሱም መጣች፤ ኢየሱስም ማርታ በተቀበለችበት ስፍራ ነበረ እንጂ ገና ወደ መንደሩ አልገባም ነበር። ሲያጽናኑአት ከእርስዋ ጋር በቤት የነበሩ አይሁድም ማርያም ፈጥና እንደ ተነሣችና እንደ ወጣች ባዩ ጊዜ፥ ወደ መቃብር ሄዳ በዚያ ልታለቅስ መስሎአቸው ተከተሉአት። ማርያምም ኢየሱስ ወዳለበት መጥታ ባየችው ጊዜ በእግሩ ላይ ወድቃ፦ “ጌታ ሆይ፥ አንተ በዚህ ኖረህ ብትሆን ወንድሜ ባልሞተም ነበር” አለችው። ኢየሱስም እርስዋ ስታለቅስ ከእርስዋም ጋር የመጡት አይሁድ ሲያለቅሱ አይቶ በመንፈሱ አዘነ በራሱም ታወከ፤ “ወዴት አኖራችሁት?” አለም። እነርሱም፦ “ጌታ ሆይ፥ መጥተህ እይ” አሉት። ኢየሱስም እንባውን አፈሰሰ። ስለዚህ አይሁድ፦ “እንዴት ይወደው እንደ ነበረ እዩ” አሉ። ከእነርሱ ግን አንዳንዶቹ፦ “ይህ የዕውሩን ዓይኖች የከፈተ ይህን ደግሞ እንዳይሞት ያደርግ ዘንድ ባልቻለም ነበርን?” አሉ። ኢየሱስም በራሱ አዝኖ ወደ መቃብሩ መጣ፤ እርሱም ዋሻ ነበረ፤ ድንጋይም ተገጥሞበት ነበር። ኢየሱስ፦ “ድንጋዩን አንሡ” አለ። የሞተውም እኅት ማርታ፦ “ጌታ ሆይ፥ ከሞተ አራት ቀን ሆኖታልና አሁን ይሸታል” አለችው። ኢየሱስ፦ “ብታምኚስ የእግዚአብሔርን ክብር እንድታዪ አልነገርሁሽምን?” አላት። ድንጋዩንም አነሡት። ኢየሱስም ዓይኖቹን ወደ ላይ አንሥቶ፦ “አባት ሆይ፥ ስለ ሰማኸኝ አመሰግንሃለሁ። ሁልጊዜም እንድትሰማኝ አወቅሁ፤ ነገር ግን አንተ እንደ ላኸኝ ያምኑ ዘንድ በዚህ ዙሪያ ስለ ቆሙት ሕዝብ ተናገርሁ” አለ። ይህንም ብሎ በታላቅ ድምፅ፦ “አልዓዛር ሆይ፥ ወደ ውጭ ና” ብሎ ጮኸ። የሞተውም እጆቹና እግሮቹ በመግነዝ እንደ ተገነዙ ወጣ፤ ፈቱም በጨርቅ እንደ ተጠመጠመ ነበር። ኢየሱስም፦ “ፍቱትና ይሂድ ተዉት” አላቸው። ስለዚህ ወደ ማርያም ከመጡት፥ ኢየሱስም ያደረገውን ካዩት ከአይሁድ ብዙዎች በእርሱ አመኑ፤