የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኦሪት ዘኊልቊ 18

18
የካህናትና የሌዋውያን ተግባር
1እግዚአብሔር አሮንን እንዲህ አለው፤ “በመገናኛው ድንኳን ውስጥ በሚከናወነው አገልግሎት ስለሚፈጸመው በደል ሁሉ አንተና ልጆችህ፥ ሌዋውያንም ኀላፊነቱን ትሸከማላችሁ፤ በክህነት አገልግሎት ለሚፈጸመው በደል ግን ኀላፊነቱን የምትሸከሙት በተለይ አንተና ልጆችህ ብቻ ናችሁ። 2አንተና ልጆችህ በምስክሩ ድንኳን ፊት በምታገለግሉበት ጊዜ ከእናንተ ጋር በመሥራት ይረዱአችሁ ዘንድ፥ የሌዊ ነገድ የሆኑትን ወገኖችህን ውሰድ፤ 3እነርሱም እናንተን የመርዳት ተግባራቸውን እያከናወኑ ድንኳኑንም የመንከባከብ ኀላፊነት ይወስዳሉ፤ ይሁን እንጂ በተቀደሰው ስፍራና በመሠዊያው ላይ ያሉትን ንዋያተ ቅድሳት መንካት አይኖርባቸውም፤ ነክተው ቢገኙ ግን እነርሱም እናንተም በአንድነት ትሞታላችሁ። 4እነርሱ ዘወትር ከእናንተ ጋር መሥራትና በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ስለ ተሰጣቸው አገልግሎት ሁሉ ኀላፊነታቸውን መፈጸም አለባቸው፤ ነገር ግን ሌዋዊ ያልሆነ ማንኛውም ሰው ለመሥራት ወደ እናንተ መቅረብ የለበትም። 5ቊጣዬ በእስራኤል ሕዝብ ላይ እንደገና እንዳይገለጥ በተቀደሰው ስፍራና በመሠዊያው ላይ ያለውን የአገልግሎት ኀላፊነት የምትፈጽሙት እናንተና ልጆቻችሁ ብቻ ናችሁ። 6ዘመዶቻችሁን ሌዋውያንን ከእስራኤላውያን መካከል የመረጥኩና ለእናንተም ስጦታ አድርጌ የመደብኩ እኔ ነኝ፤ እነርሱ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ የተመደቡበትን ተግባር ያከናውኑ ዘንድ ለእኔ የተለዩ ናቸው። 7ነገር ግን መሠዊያውንና ከመጋረጃው በስተውስጥ በኩል ያለውን ቅድስተ ቅዱሳኑን የሚመለከተውን የክህነት አገልግሎት የምትፈጽሙ አንተና ልጆችህ ብቻ ናችሁ፤ የክህነትን አገልግሎት ዕድል ፈንታ አድርጌ ስለ ሰጠኋችሁ ይህ ሁሉ ኀላፊነት የእናንተ ነው፤ ካህን ያልሆነ ማንኛውም ሰው ወደዚያ ቢቀርብ ይሞታል።”
የካህናቱ ድርሻ
8ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር አሮንን እንዲህ አለው፦ “ለእኔ የሚቀርበውን የማይቃጠለውን ልዩ መባ ሁሉ ለአንተ የሰጠሁህ መሆኑን አስታውስ፤ እርሱ ለዘለዓለም ለአንተና ለዘሮችህ ሁሉ ድርሻ እንዲሆን ሰጥቻችኋለሁ፤ 9ለእኔ ከሚቀርበው እጅግ ከተቀደሰ መባ ሁሉ፥ ከእህል ቊርባን፥ ስለ ኃጢአት ስርየትና ስለ በደል ካሣ ከሚቀርበውም መባ ሁሉ፥ በእሳት የማይቃጠለው የመባ ድርሻ የአንተና የልጆችህ ነው። 10በተቀደሰው ስፍራ ሆናችሁ እነዚህን ሁሉ ትበላላችሁ፤ የተቀደሱ ናቸው፤ ወንዶች ሁሉ ይመገቡት።
11“በተጨማሪም እስራኤላውያን በእኔ ፊት በመወዝወዝ የሚያቀርቡአቸው ልዩ ስጦታዎች ሁሉ የእናንተ ይሆናሉ፤ እነርሱን ለአንተ፥ ለወንዶችና ለሴቶች ልጆችህ ለሚመጡት ዘመናት ሁሉ ቋሚ ድርሻ አድርጌ ሰጥቻለሁ፤ ንጹሕ የሆነ ማንኛውም የቤተሰብህ አባል ሊመገባቸው ይችላል።
12“እስራኤላውያን የሚሰጡኝን ምርጥ የሆነ በኲራት፥ ይኸውም የወይራ ዘይት፥ የወይን ጠጅና እህል ለእናንተ እሰጣችኋለሁ። 13ከምድራቸው ለእኔ ለእግዚአብሔር የሚያመጡት በኲራት ሁሉ የእናንተ ዕድል ፈንታ ስለሚሆን ንጹሕ የሆነ የቤተሰባችሁ አባል ሁሉ ሊመገበው ይችላል።
14“በእስራኤል ውስጥ ሙሉ በሙሉ ለእኔ የተለየ ነገር ሁሉ ለእናንተ ይሆናል። #ዘሌ. 27፥28።
15“እስራኤላውያን ለእኔ የሚያቀርቡት የሰውም ሆነ የእንስሳ በኲር ሁሉ የእናንተ ይሆናል፤ ነገር ግን የሰውን የበኲር ልጅ ለመዋጀት ዋጋውን በጥሬ ገንዘብ መቀበል አለባችሁ፤ እንዲሁም ንጹሕ ስላልሆነው የእንስሳ በኲር ምትክ ዋጋውን በጥሬ ገንዘብ መቀበል ትችላላችሁ፤ 16አንድ ወር የሞላቸው ሕፃናት በይፋ በተመደበው ዋጋ መሠረት አምስት ሰቅል ጥሬ ብር የቤዛ ዋጋ ተከፍሎላቸው ሊዋጁ ይችላሉ። 17የላም፥ የበግና የፍየል በኲር ግን መዋጀት የለባቸውም፤ እነርሱ በፍጹም የእኔ ስለ ሆኑ መሥዋዕት ሆነው መቅረብ ይኖርባቸዋል፤ ደማቸውን በመሠዊያው ላይ አፍስሱት፤ ስባቸውንም መዓዛው እኔን ደስ የሚያሰኝ መሥዋዕት እንዲሆን በእሳት አቃጥሉት። 18ከእነርሱ የሚገኘውም ሥጋ በመወዝወዝ ልዩ መባ ሆኖ እንደሚቀርበው እንደ ፍርምባውና እንደ ቀኙ ወርች ለእናንተ ይሰጣል።
19“እስራኤላውያን ለእኔ የሚያቀርቡአቸውን ልዩ ስጦታዎች ሁሉ ለእናንተ፥ ለወንዶችና ለሴቶች ልጆቻችሁ ለሚመጡት ዘመናት ሁሉ ቋሚ ድርሻ አድርጌ ሰጥቻችኋለሁ፤ ይህም ከእናንተና ከዘሮቻችሁ ሁሉ ጋር የምገባው የማይሻር የጨው ቃል ኪዳን ነው።”
20እግዚአብሔር አሮንን እንዲህ አለው፦ “ለትውልድ የሚተላለፍ ምንም ዐይነት ርስት አትቀበልም፤ ከእስራኤልም ምድር የትኛውም ክፍል ለአንተ አይሆንም፤ እኔ እግዚአብሔር ራሴ ለአንተ ርስትህ ነኝ።”
21እግዚአብሔር እንዲህ አለ፤ “የእስራኤል ሕዝብ ለእኔ የሚያመጡትን ዐሥራት ሁሉ የሌዋውያን ድርሻ እንዲሆን ሰጥቻቸዋለሁ፤ ይህም በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ለሚሰጡት አገልግሎት ደመወዝ ይሆንላቸዋል። #ዘሌ. 27፥30-33፤ ዘዳ. 14፥22-29። 22ሌሎች እስራኤላውያን ግን በራሳቸው ላይ የሞት ቅጣት እንዳያስከትሉ ዳግመኛ ወደ መገናኛው ድንኳን መቅረብ የለባቸውም፤ 23ከእንግዲህ ወዲህ ለመገናኛው ድንኳን እንክብካቤ የሚያደርጉትና ለእርሱም ሙሉ ኀላፊነት የሚኖራቸው ሌዋውያን ብቻ ናቸው፤ ይህም ለዘሮቻችሁ የሚተላለፍ የማይሻር ሕግ ሆኖ ይኖራል፤ ሌዋውያን ዘላቂነት ያለው ቋሚ ርስት በእስራኤል ምድር አይኖራቸውም። 24እስራኤላውያን ልዩ መባ አድርገው ለእኔ የሚያመጡትን ዐሥራት ለእነርሱ ስለ መደብኩላቸው፤ በእስራኤል ዘላቂነት ያለው ቋሚ ርስት እንደማይኖራቸው ነግሬአቸዋለሁ።”
ሌዋውያን ለእግዚአብሔር የሚያቀርቡት ዐሥራት
25እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ 26“ለሌዋውያን እንዲህ ብለህ ንገራቸው፦ ‘እግዚአብሔር ድርሻችሁ አድርጎ የሚሰጣችሁን ዐሥራት ከእስራኤላውያን በምትቀበሉበት ጊዜ፥ እናንተም በበኩላችሁ ከዚያው ከተቀበላችሁት የዐሥራት ዐሥራት በማውጣት ለእግዚአብሔር ልዩ መባ አድርጋችሁ አቅርቡ። 27ይህም ልዩ መባ አንድ ገበሬ ከአዲስ እህል ወይም የወይን ጠጅ ዐሥራት አውጥቶ እንደሚሰጠው ዐይነት ሆኖ ይቈጠርላችኋል። 28በዚህ ዐይነት እናንተም ከእስራኤላውያን ከምትቀበሉት ዐሥራት ሁሉ፥ ለእግዚአብሔር የሚሆነውን ልዩ መባ ታቀርባላችሁ፤ ለእግዚአብሔር የምታመጡትን ይህን ልዩ መባ ለካህኑ አሮን ታስረክቡታላችሁ። 29ለእግዚአብሔር የምታቀርቡት ከምትቀበሉት በረከት ሁሉ በተለይ ምርጥ የሆነ ነገር መሆን አለበት። 30ምርጥ የሆነውን ነገር በምትሰጡበት ጊዜ ገበሬ መባውን ከሰጠ በኋላ የተረፈውን ለራሱ እንደሚያስቀር እናንተም የተረፈውን ለራሳችሁ ታስቀራላችሁ። 31እርሱ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ለምትሰጡት አገልግሎት የድካም ዋጋችሁ ስለ ሆነ የተረፈውንም እናንተና ቤተሰቦቻችሁ በየትኛውም ስፍራ ሆናችሁ መመገብ ትችላላችሁ፤ 32ምርጥ የሆነውን ነገር ለእግዚአብሔር ካቀረባችሁ በኋላ በምትመገቡበት ጊዜ በደል አይኖርባችሁም፤ ነገር ግን ምርጥ የሆነው ነገር ከእርሱ ላይ ሳይነሣ ከስጦታው በመመገብ የእስራኤላውያንን የተቀደሰ ስጦታ እንዳታስነውሩ ተጠንቀቁ፤ ይህን ብታደርጉ ግን ትሞታላችሁ።’ ”

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ