የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኦሪት ዘኊልቊ 30

30
ስለ ስእለት የተሰጠ መመሪያ
1ሙሴ ለእስራኤል የነገድ መሪዎች አላቸው፤ እግዚአብሔር ያዘዘው ነገር ይህ ነው፦ 2አንድ ሰው ለእግዚአብሔር አንድ ነገር ለመስጠት ቢሳል ወይም ከአንድ ነገር ራሱን ለመከልከል በመሐላ ቃል ቢገባ፥ አደርጋለሁ ያለውን ሁሉ መፈጸም አለበት እንጂ የሰጠውን የተስፋ ቃል ማስቀረት አይገባውም። #ዘዳ. 23፥21-23፤ ማቴ. 5፥33።
3ገና በአባትዋ ቤት የምትኖር ልጃገረድ ለእግዚአብሔር አንድ ነገር ለመስጠት ብትሳል፥ ወይም ከአንድ ነገር ራስዋን ለመከልከል ቃል ብትገባ፥ 4አባትዋ ስለዚህ ጉዳይ ሰምቶ ካልተቃወማት በቀር ስእለትዋን ወይም የገባችውን ቃል መፈጸም አለባት። 5አባትዋ ስለ ጉዳዩ ሰምቶ ስእለትዋን እንዳትፈጽም የሚቃወማት ከሆነ ግን ስእለትዋን የመፈጸም ግዴታ አይኖርባትም፤ ስእለትዋን ለመፈጸም ያልቻለችው አባትዋ ስለ ከለከላት በመሆኑ እግዚአብሔር ይቅርታ ያደርግላታል።
6ባል ያላገባች ሴት አስባም ሆነ በግድየለሽነት ስእለት ካደረገች ወይም ከአንድ ነገር ለመከልከል ቃል ከገባች በኋላ ባል ብታገባ፥ 7ባልዋ ስለ ጉዳዩ ሰምቶ ካልከለከላት በቀር ስእለትዋንም ሆነ የገባችውን ቃል መፈጸም አለባት። 8ባልዋ ስለ ጉዳዩ ሰምቶ ከከለከላት ግን የመፈጸም ግዴታ የለባትም፤ ስእለትዋን ለመፈጸም ያልቻለችው ባልዋ ስለ ከለከላት በመሆኑ እግዚአብሔር ይቅርታ ያደርግላታል።
9ባልዋ የሞተባት ሴት ወይም ከባልዋ የተፋታች ሴት ማንኛቸውንም ስእለት ሆነ ወይም ከአንድ ነገር ለመከልከል የገባችውን ቃል መፈጸም አለባት።
10ባል ያገባች ሴት ስእለት ብትሳል ወይም ከአንድ ነገር ለመከልከል በመሐላ ቃል ብትገባ፥ 11ባልዋ ስለ ጉዳዩ ሰምቶ ካልተቃወማት በቀር ስእለትዋንም ሆነ ከአንድ ነገር ለመከልከል የገባችውን መሐላ መፈጸም ይኖርባታል፤ 12ባልዋ ስለ ጉዳዩ ሰምቶ ስእለትዋን እንዳትፈጽም ቢከለክላት ግን የመፈጸም ግዴታ የለባትም፤ ስእለትዋን ለመፈጸም ያልቻለችው ባልዋ ስለ ከለከላት በመሆኑ እግዚአብሔር ይቅርታ ያደርግላታል። 13ባልዋ ማንኛውንም ስእለት ሆነ መሐላ የመፍቀድ ወይም የመቃወም መብት አለው። 14ነገር ግን ባልዋ ስለ ጉዳዩ በሰማበት ቀን ማግስት ምንም ተቃውሞ ያላቀረበ ከሆነ ስእለትዋንና በመሐላ የገባችውን ቃል ሁሉ መፈጸም ይኖርባታል፤ ስለ ጉዳዩ በሰማበት ቀን ተቃውሞ አለማቅረቡ ፈቃደኛ መሆኑን ያረጋግጣል። 15ነገር ግን ቈየት ብሎ ስእለቱን የሚቃወም ከሆነ ለስእለቱ አለመፈጸም ኀላፊ ይሆናል።
16ሳታገባ በአባትዋ ቤት የምትኖር ልጃገረድ ወይም ያገባች ሴት ስእለት ወይም የመሐላ ቃል በምትገባበት ጊዜ የአባት ወይም የባል ኀላፊነትንና መብትን በተመለከተ እግዚአብሔር ለሙሴ የሰጠው ደንብ ይህ ነው።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ