መጽሐፈ መዝሙር 27:1-14

መጽሐፈ መዝሙር 27:1-14 አማ05

እግዚአብሔር ብርሃኔና ደኅንነቴ ስለ ሆነ ማንንም አልፈራም እግዚአብሔር የሕይወቴ ከለላ ስለ ሆነ የሚያስፈራኝ ማነው? ክፉ ሰዎች ሲያጠቁኝና ሊገድሉኝ ሲቃጡ እነርሱ ራሳቸው ተሰናክለው ይወድቃሉ። ብዙ ሠራዊት ቢከበኝም አልፈራም፤ ጠላቶቼ በጦርነት ቢያጠቁኝ እንኳ በእግዚአብሔር መተማመኔን አልተውም። እግዚአብሔርን አንድ ነገር እለምነዋለሁ፤ የምለምነውም፦ በሕይወት ዘመኔ ሁሉ በእግዚአብሔር ቤት እኖር ዘንድ የእግዚአብሔርን አስደናቂነት እንድመለከትና በቤተ መቅደሱም መጸለይ እንድችል ነው። በችግር ቀን በጥላው ሥር ይደብቀኛል፤ በመቅደሱ ውስጥ ይሰውረኛል፤ በአለትም ላይ ከፍ አድርጎ ይጠብቀኛል። አሁን ግን በከበቡኝ ጠላቶቼ ላይ ራሴን ከፍ አደረግሁ፤ በደስታ “እልል” እያልኩ በመቅደሱ ውስጥ መሥዋዕት አቀርባለሁ፤ እየዘመርኩም እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ። እግዚአብሔር ሆይ! ወደ አንተ ጮክ ብዬ ስጣራ ስማኝ! ምሕረትን አድርግልኝ፤ ጸሎቴንም ስማ! ልቤ “የእርሱን ፊት ፈልግ” አለኝ፤ እግዚአብሔር ሆይ! የአንተን ፊት እሻለሁ። አምላኬና አዳኜ ሆይ! ፊትህን ከእኔ አትሰውርብኝ፤ ተቈጥተህም እኔን አገልጋይህን ከአንተ እንድርቅ አታድርገኝ፤ ረዳቴም ስለ ሆንክ ከእኔ አትለይ፤ አትተወኝም። አባቴና እናቴ ቢተዉኝ እንኳ እግዚአብሔር ዘወትር ይቀበለኛል። እግዚአብሔር ሆይ! የምመራበትን መንገድ አስተምረኝ፤ በጠላቶቼም ምክንያት በተደላደለ መንገድ ምራኝ። የሐሰት ምስክሮች ዐመፅን እየተናገሩ በእኔ ላይ ስለ ተነሡ ለጠላቶቼ ፍላጎት አሳልፈህ አትስጠኝ። ሕያዋን በሚኖሩባት ምድር እስካለሁ ድረስ የእግዚአብሔርን በጎነት እንደማይ እተማመናለሁ። በእግዚአብሔር ታመን፤ በርታ፤ ተስፋ አትቊረጥ፤ በእግዚአብሔር ታመን።