መዝሙር 27:1-14

መዝሙር 27:1-14 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

እግዚአብሔር ብርሃኔና መድኅኔ ነው፤ የሚያስፈራኝ ማን ነው? እግዚአብሔር ለሕይወቴ ዐምባዋ ነው፤ ማንን እፈራለሁ? ሥጋዬን ይበሉ ዘንድ፣ ክፉዎች ገፍተው በመጡ ጊዜ፣ ጠላቶቼና ባላጋራዎቼ በተነሡብኝ ጊዜ፣ እነርሱ ተሰነካክለው ወደቁ። ሰራዊት ቢከብበኝ እንኳ፣ ልቤ አይፈራም፤ ጦርነት ቢነሣብኝ እንኳ፣ ልበ ሙሉ ነኝ። እግዚአብሔርን አንዲት ነገር እለምነዋለሁ፤ እርሷንም እሻለሁ፤ ይኸውም በሕይወቴ ዘመን ሁሉ፣ በእግዚአብሔር ቤት እኖር ዘንድ፣ የእግዚአብሔርን ክብር ውበት አይ ዘንድ፣ በመቅደሱም ሆኜ አሰላስል ዘንድ ነው። በመከራ ቀን፣ በድንኳኑ ውስጥ ይሰውረኛልና፤ በተቀደሰ ድንኳኑም ውስጥ ይሸሽገኛል፤ በዐለቱ ላይ ከፍ ያደርገኛል። በዚህ ጊዜ በዙሪያዬ ባሉ ጠላቶቼ ላይ፣ ራሴ ከፍ ከፍ ይላል፤ በድንኳኑም ውስጥ የእልልታ መሥዋዕት እሠዋለሁ፤ ለእግዚአብሔር እቀኛለሁ፤ እዘምርለታለሁም። እግዚአብሔር ሆይ፤ ድምፄን ከፍ አድርጌ ስጮኽ ስማኝ፤ ራራልኝ፤ ስማኝም። “ፊቴን ፈልጉ” ባልህ ጊዜ፤ ልቤ፣ እግዚአብሔር ሆይ፤ ፊትህን እሻለሁ አለች። ፊትህን ከእኔ አትሰውር፤ ተቈጥተህ አገልጋይህን አታርቀው፤ መቼም ረዳቴ ነህና። አዳኝ አምላኬ ሆይ፤ አትጣለኝ፤ አትተወኝም። አባቴና እናቴ ቢተዉኝ እንኳ፣ እግዚአብሔር ይቀበለኛል። እግዚአብሔር ሆይ፤ መንገድህን አስተምረኝ፤ ስለ ጠላቶቼም፣ በቀና መንገድ ምራኝ። ለጠላቶቼ ፍላጎት አሳልፈህ አትስጠኝ፤ የሐሰት ምስክሮች ተነሥተውብኛልና፣ ዐመፃ የሚረጩ ናቸው። የእግዚአብሔርን ቸርነት በሕያዋን ምድር እንደማይ ሙሉ እምነቴ ነው። እግዚአብሔርን ተስፋ አድርግ፤ አይዞህ፣ በርታ፤ እግዚአብሔርን ተስፋ አድርግ።

መዝሙር 27:1-14 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

እግዚአብሔር ብርሃኔና ደኅንነቴ ስለ ሆነ ማንንም አልፈራም እግዚአብሔር የሕይወቴ ከለላ ስለ ሆነ የሚያስፈራኝ ማነው? ክፉ ሰዎች ሲያጠቁኝና ሊገድሉኝ ሲቃጡ እነርሱ ራሳቸው ተሰናክለው ይወድቃሉ። ብዙ ሠራዊት ቢከበኝም አልፈራም፤ ጠላቶቼ በጦርነት ቢያጠቁኝ እንኳ በእግዚአብሔር መተማመኔን አልተውም። እግዚአብሔርን አንድ ነገር እለምነዋለሁ፤ የምለምነውም፦ በሕይወት ዘመኔ ሁሉ በእግዚአብሔር ቤት እኖር ዘንድ የእግዚአብሔርን አስደናቂነት እንድመለከትና በቤተ መቅደሱም መጸለይ እንድችል ነው። በችግር ቀን በጥላው ሥር ይደብቀኛል፤ በመቅደሱ ውስጥ ይሰውረኛል፤ በአለትም ላይ ከፍ አድርጎ ይጠብቀኛል። አሁን ግን በከበቡኝ ጠላቶቼ ላይ ራሴን ከፍ አደረግሁ፤ በደስታ “እልል” እያልኩ በመቅደሱ ውስጥ መሥዋዕት አቀርባለሁ፤ እየዘመርኩም እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ። እግዚአብሔር ሆይ! ወደ አንተ ጮክ ብዬ ስጣራ ስማኝ! ምሕረትን አድርግልኝ፤ ጸሎቴንም ስማ! ልቤ “የእርሱን ፊት ፈልግ” አለኝ፤ እግዚአብሔር ሆይ! የአንተን ፊት እሻለሁ። አምላኬና አዳኜ ሆይ! ፊትህን ከእኔ አትሰውርብኝ፤ ተቈጥተህም እኔን አገልጋይህን ከአንተ እንድርቅ አታድርገኝ፤ ረዳቴም ስለ ሆንክ ከእኔ አትለይ፤ አትተወኝም። አባቴና እናቴ ቢተዉኝ እንኳ እግዚአብሔር ዘወትር ይቀበለኛል። እግዚአብሔር ሆይ! የምመራበትን መንገድ አስተምረኝ፤ በጠላቶቼም ምክንያት በተደላደለ መንገድ ምራኝ። የሐሰት ምስክሮች ዐመፅን እየተናገሩ በእኔ ላይ ስለ ተነሡ ለጠላቶቼ ፍላጎት አሳልፈህ አትስጠኝ። ሕያዋን በሚኖሩባት ምድር እስካለሁ ድረስ የእግዚአብሔርን በጎነት እንደማይ እተማመናለሁ። በእግዚአብሔር ታመን፤ በርታ፤ ተስፋ አትቊረጥ፤ በእግዚአብሔር ታመን።

መዝሙር 27:1-14 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ጌታ ብርሃኔና መድኃኒቴ ነው፥ የሚያስፈራኝ ማን ነው? ጌታ የሕይወቴ ከለላዋ ነው፥ የሚያስደነግጠኝ ማን ነው? ክፉዎች፥ አስጨናቂዎቼ ጠላቶቼም፥ ሥጋዬን ለመብላት በቀረቡ ጊዜ፥ እነርሱ ተሰናከሉና ወደቁ። ሠራዊትም ቢከብበኝ ልቤ አይፈራም፥ ጦርነትም ቢነሣብኝ በዚህ እተማመናለሁ። ጌታን አንዲት ነገር ለመንሁት እርሷንም እሻለሁ፥ በሕይወቴ ዘመን ሁሉ በጌታ ቤት እኖር ዘንድ፥ ጌታን ደስ የሚያሰኘውንም አይ ዘንድ፥ መቅደሱንም እመለከት ዘንድ። በመከራ ቀን በድንኳኑ ሰውሮኛልና፥ በድንኳኑም መሸሸጊያ ሸሽጎኛልና፥ በዓለት ላይ ከፍ ከፍ አድርጎኛልና። እነሆ፥ አሁን በዙሪያ ባሉ በጠላቶቼ ላይ ራሴን ከፍ ከፍ አደረገ፥ በድንኳኑም የእልልታ መሥዋዕትን ሠዋሁ፥ ለጌታ እቀኛለሁ እዘምርለትማለሁ። አቤቱ፥ ወደ አንተ የጮኽሁትን ቃሌን ስማኝ፥ ማረኝና አድምጠኝ። “ፊቴን እሹት” የሚለውን ቃልህን በልቤ አሰብኩኝ፦ አቤቱ፥ ፊትህን እሻለሁ። ፊትህን ከእኔ አትሰውር፥ ተቈጥተህ ከባርያህ ፈቀቅ አትበል፥ ረዳት ሁነኝ፥ አትጣለኝም፥ የመድኃኒቴም አምላክ ሆይ፥ አትተወኝ። አባቴና እናቴ ትተውኛልና፥ ጌታ ግን ተቀበለኝ። አቤቱ፥ መንገድህን አስተምረኝ፥ በጠላቶቼም ምክንያት በቀና መንገድ ምራኝ። የሐሰት ምስክሮችና ዓመፀኞች ተነሥተውብኛልና ለጠላቶቼ ፍላጎት አሳልፈህ አትስጠኝ። የጌታን ቸርነት በሕያዋን ምድር እንደማይ አምናለሁ። በጌታ ተስፋ አድርግ፥ በርታ፥ ልብህም ይጽና፥ በጌታ ተስፋ አድርግ።

መዝሙር 27:1-14

መዝሙር 27:1-14 NASV