መዝሙረ ዳዊት 27:1-14

መዝሙረ ዳዊት 27:1-14 መቅካእኤ

ጌታ ብርሃኔና መድኃኒቴ ነው፥ የሚያስፈራኝ ማን ነው? ጌታ የሕይወቴ ከለላዋ ነው፥ የሚያስደነግጠኝ ማን ነው? ክፉዎች፥ አስጨናቂዎቼ ጠላቶቼም፥ ሥጋዬን ለመብላት በቀረቡ ጊዜ፥ እነርሱ ተሰናከሉና ወደቁ። ሠራዊትም ቢከብበኝ ልቤ አይፈራም፥ ጦርነትም ቢነሣብኝ በዚህ እተማመናለሁ። ጌታን አንዲት ነገር ለመንሁት እርሷንም እሻለሁ፥ በሕይወቴ ዘመን ሁሉ በጌታ ቤት እኖር ዘንድ፥ ጌታን ደስ የሚያሰኘውንም አይ ዘንድ፥ መቅደሱንም እመለከት ዘንድ። በመከራ ቀን በድንኳኑ ሰውሮኛልና፥ በድንኳኑም መሸሸጊያ ሸሽጎኛልና፥ በዓለት ላይ ከፍ ከፍ አድርጎኛልና። እነሆ፥ አሁን በዙሪያ ባሉ በጠላቶቼ ላይ ራሴን ከፍ ከፍ አደረገ፥ በድንኳኑም የእልልታ መሥዋዕትን ሠዋሁ፥ ለጌታ እቀኛለሁ እዘምርለትማለሁ። አቤቱ፥ ወደ አንተ የጮኽሁትን ቃሌን ስማኝ፥ ማረኝና አድምጠኝ። “ፊቴን እሹት” የሚለውን ቃልህን በልቤ አሰብኩኝ፦ አቤቱ፥ ፊትህን እሻለሁ። ፊትህን ከእኔ አትሰውር፥ ተቈጥተህ ከባርያህ ፈቀቅ አትበል፥ ረዳት ሁነኝ፥ አትጣለኝም፥ የመድኃኒቴም አምላክ ሆይ፥ አትተወኝ። አባቴና እናቴ ትተውኛልና፥ ጌታ ግን ተቀበለኝ። አቤቱ፥ መንገድህን አስተምረኝ፥ በጠላቶቼም ምክንያት በቀና መንገድ ምራኝ። የሐሰት ምስክሮችና ዓመፀኞች ተነሥተውብኛልና ለጠላቶቼ ፍላጎት አሳልፈህ አትስጠኝ። የጌታን ቸርነት በሕያዋን ምድር እንደማይ አምናለሁ። በጌታ ተስፋ አድርግ፥ በርታ፥ ልብህም ይጽና፥ በጌታ ተስፋ አድርግ።