መጽሐፈ መዝሙር 56
56
በእግዚአብሔር የመታመን ጸሎት
1አምላክ ሆይ! ሰዎች ስለሚያስጨንቁኝና
ጠላቶቼም ዘወትር ስለሚያሳድዱኝ ማረኝ።
2ጠላቶቼ ቀኑን ሙሉ ያጠቁኛል፤
ልዑል እግዚአብሔር ሆይ፥ የሚያሳድዱኝ ብዙዎች ናቸው።
3ፍርሀት ቢይዘኝ እንኳ
በአንተ እተማመናለሁ።
4በእግዚአብሔር ስለምታመን አልፈራም፤
ስለ ሰጠኝም ተስፋ አመሰግነዋለሁ፤
በእግዚአብሔር ስለምታመን
ከቶ ሰው ምን ሊያደርገኝ ይችላል?
5ጠላቶቼ ቀኑን ሙሉ በእኔ ላይ ስሕተት ለማግኘት ይጥራሉ፤
ዘወትር እኔን ለመጒዳት ያሤራሉ።
6ተሰባስበው ይሸምቁብኛል፤
እርምጃዬን ሁሉ ይከታተላሉ፤
ሕይወቴንም ለማጥፋት ያደባሉ።
7አምላክ ሆይ! በምንም መንገድ እንዲያመልጡ አታድርጋቸው!
በቊጣህ ሕዝቦችን አዋርዳቸው።
8የመንከራተት ቀኖቼን ቈጥረሃል፤
እንባዎቼንም በጠርሙስ ውስጥ አስቀምጠሃል፤
እያንዳንዳቸውንም መዝግበሃል።
9እኔ ወደ አንተ በምጣራበት ቀን፥
ጠላቶቼ ወደ ኋላቸው ይመለሳሉ፤
እግዚአብሔር ከእኔ ጋር መሆኑንም
በዚህ ዐውቃለሁ።
10ይህም ከእኔ ጋር የሆነው እግዚአብሔር፥
ቃሉን የማመሰግነውና የማከብረው አምላክ ነው።
11በእርሱም ስለምታመን አልፈራም፤
ሰውስ ከቶ ምን ሊያደርገኝ ይችላል?
12አምላክ ሆይ!
እኔ ራሴ ለአንተ የስእለት ግዴታ ገብቼአለሁ፤
ስእለቴን ከምስጋና መሥዋዕት ጋር አቀርባለሁ። #1ሳሙ. 21፥13-15።
13አንተ ከሞት አድነኸኛል፤
ተሰናክዬ እንዳልወድቅም ረድተኸኛል፤
ስለዚህ በሕያዋን ላይ በሚያበራው ብርሃን
በእግዚአብሔር ፊት እመላለሳለሁ።
Currently Selected:
መጽሐፈ መዝሙር 56: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997