የዮሐንስ ራእይ 22:1-21

የዮሐንስ ራእይ 22:1-21 አማ05

ከዚህ በኋላ መልአኩ ከእግዚአብሔርና ከበጉ ዙፋን የሚወጣውን እንደ ብሩህ መስተዋት ጥርት ያለውን የሕይወት ውሃ ወንዝ አሳየኝ፤ ይህ ወንዝ በከተማይቱ ዋና መንገድ መካከል ሰንጥቆ ያልፋል፤ በወንዙ ግራና ቀኝ በየወሩ እያፈራ በዓመት ዐሥራ ሁለት ጊዜ ፍሬ የሚሰጥ የሕይወት ዛፍ ነበረ፤ የዛፉም ቅጠሎች ሕዝቦችን ለመፈወስ ያገለግላሉ። ከእንግዲህም ወዲህ ምንም ዐይነት ርግማን አይኖርም፤ የእግዚአብሔርና የበጉ ዙፋን በከተማይቱ ውስጥ ይሆናል፤ አገልጋዮቹም ያመልኩታል። ፊቱን ያያሉ፤ ስሙም በየግምባራቸው ላይ ይሆናል። ከእንግዲህ ወዲህ ሌሊት አይኖርም፤ ጌታ አምላክ ስለሚያበራላቸው የመብራት ወይም የፀሐይ ብርሃን አያስፈልጋቸውም፤ ለዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ይነግሣሉ። ከዚህ በኋላ መልአኩ እንዲህ አለኝ፦ “እነዚህ ቃላት የታመኑና እውነተኞች ናቸው፤ ነቢያትን የሚያናግር አምላክ በቅርብ ጊዜ የሚሆነውን ነገር ለአገልጋዮቹ ለመግለጥ መልአኩን ላከ።” ኢየሱስም “እነሆ! እኔ በቶሎ እመጣለሁ! የዚህን መጽሐፍ የትንቢት ቃል የሚጠብቅ የተመሰገነ ነው!” አለ። እነዚህን ነገሮች የሰማሁና ያየሁ እኔ ዮሐንስ ነኝ፤ እነዚህን ነገሮች በሰማሁና ባየሁ ጊዜ እነዚህን ነገሮች ላሳየኝ መልአክ ልሰግድለት በእግሩ ሥር ወደቅኩ። መልአኩ ግን “ተው ይህን አታድርግ! እኔ ከአንተና ከወንድሞችህ ከነቢያት ጋር የዚህን መጽሐፍ ቃል ከሚፈጽሙ ሰዎች ጋር አገልጋይ ነኝ፤ ለእግዚአብሔር ስገድ!” አለኝ። ቀጥሎም እንዲህ አለኝ፤ “ጊዜው የቀረበ ስለ ሆነ የዚህን መጽሐፍ የትንቢት ቃል በማኅተም አትዝጋው፤ ከእንግዲህ ወዲህ ዐመፀኛው ማመፁን ይቀጥል፤ ርኩሱም ይርከስ፤ ጻድቁም ይጽደቅ፤ ቅዱሱም ይቀደስ።” “እነሆ! እኔ በቶሎ እመጣለሁ! ለእያንዳንዱ እንደ ሥራው የምሰጠውን ዋጋ ይዤአለሁ፤ አልፋና ዖሜጋ፥ ፊተኛውና ኋለኛው፥ መጀመሪያውና መጨረሻው እኔ ነኝ።” ከሕይወት ዛፍ ፍሬ ለመብላትና በደጃፎችዋም ወደ ከተማይቱ ለመግባት መብት እንዲኖራቸው ልብሳቸውን ያጠቡ የተባረኩ ናቸው። እንደ ውሻ የሚልከፈከፉ፥ አስማተኞች፥ አመንዝሮች፥ ነፍሰ ገዳዮች፥ ጣዖት አምላኪዎች፥ ውሸትን የሚወዱና በሐሰት መንገድ የሚሄዱ ሁሉ ከከተማይቱ ውጪ ይሆናሉ። “እኔ ኢየሱስ ይህን ምስክርነት እንዲሰጣችሁ መልአኬን ለአብያተ ክርስቲያን ልኬአለሁ፤ እኔ የዳዊት የትውልድ ሐረግና ዘር ነኝ፤ የሚያበራ የንጋት ኮከብ ነኝ።” መንፈስ ቅዱስና ሙሽራይቱ “ና!” ይላሉ፤ የሚሰማም “ና!” ይበል፤ የተጠማም ይምጣ፤ የፈለገም የሕይወትን ውሃ ያለ ምንም ዋጋ በነጻ ይጠጣ። እነሆ፥ በዚህ መጽሐፍ የተጻፈውን የትንቢት ቃል የሚሰማውን ሁሉ አስጠነቅቃለሁ፤ ማንም በዚህ ቃል ላይ አንዳች ነገር ቢጨምር፥ በዚህ መጽሐፍ የተጻፉትን መቅሠፍቶች እግዚአብሔር ይጨምርበታል። ማንም በዚህ በትንቢት መጽሐፍ ከተጻፉት ቃሎች አንዳች ነገር ቢያጐድል፥ በዚህ መጽሐፍ ከተነገሩት ከሕይወት ዛፍ ፍሬና ከቅድስቲቱ ከተማ እግዚአብሔር ድርሻውን ያጐድልበታል። የእነዚህ ነገሮች ምስክር የሆነው “በእርግጥ፥ በቶሎ እመጣለሁ!” ይላል። አሜን፥ ጌታ ኢየሱስ ሆይ ና! የጌታ የኢየሱስ ጸጋ ከሁላችሁ ጋር ይሁን፤ አሜን።