መኃልየ መኃልይ 1
1
ፍቅር ከወይን ጠጅ ይሻላል
1ከሰሎሞን መዝሙሮች መካከል በጣም ውብ የሆነው መዝሙር። #1ነገ. 4፥32።
ሙሽራይቱ
2ፍቅርህ ከወይን ጠጅ ይልቅ ጣዕም ያለው ስለ ሆነ፥
ከንፈሮችህ ይሳሙኝ።
3የምትቀባው ሽቱ መልካም መዓዛ አለው፤
ስምህን መጥራት ሽቱን እንደ መርጨት ነው፤
ቈነጃጅትም የሚያፈቅሩህ ስለዚህ ነው።
4እጄን ይዘህ ሳበኝ፤ አብረን እንሩጥ።
ንጉሡ ወደ እልፍኙ አስገባኝ፤
በዚያም አብረን ደስ ይለናል፤
ፍቅርህ ከወይን ጠጅ ይልቅ ያስደስታል፤
ስለዚህ ቈነጃጅት ሁሉ እጅግ ያፈቅሩሃል።
5እናንተ የኢየሩሳሌም ቈነጃጅት ሆይ! ስሙኝ፤
እኔ ጥቊር ነኝ፤
ይሁን እንጂ ውብ ነኝ፤
የመልኬ ጥቊረት እንደ ቄዳር ድንኳን ነው፤
ውበቴ ግን እንደ ሰሎሞን ቤተ መንግሥት መጋረጃዎች ነው።
6መልኬን ያጠቈረው የፀሐይ ቃጠሎ ነው፤
ስለዚህ ጥቊር በመሆኔ አትናቁኝ፤
የእናቴ ልጆች የሆኑ ወንድሞቼ ስለ ተጣሉኝ
የወይን ተክል ጠባቂ አደረጉኝ፤
ስለዚህ የግሌ የወይን ተክል ለመጠበቅ ጊዜ አልነበረኝም።
7ውዴ ሆይ! እስቲ ንገረኝ፤
የበጎችህን መንጋ የምታሰማራው የት ነው?
በቀትርስ ጊዜ ዕረፍት ያገኙ ዘንድ እንዲመሰጉ
የምታደርገው የት ነው?
አንተን በመፈለግ የጓደኞችህን መንጋ በመከተል
ፊትዋን እንደ ሸፈነች ሴት
የምቅበዘበዘው ለምንድን ነው?
ሙሽራው
8አንቺ ከሴቶች ሁሉ ያማርሽ ውብ ሆይ!
ቦታውን የማታውቂው ከሆነ
የበጎቹን ዱካ ተከትለሽ ሂጂ፤
የፍየል ግልገሎችሽንም
በእረኞቹ ድንኳኖች አጠገብ አሰማሪ።
9ውዴ ሆይ! የፈርዖንን ሠረገሎች በሚስቡ ፈረሶች መካከል
ያለችውን ውብ ባዝራ ትመስያለሽ፤
10የጉንጮችሽ ውበት እንደ ከበረ ሉል ነው፤
አንገትሽም በዕንቊ ጌጥ የተዋበ ነው።
11እኛ ግን የብር ፈርጥ ያለው
የወርቅ ጌጥ እናሠራልሻለን።
ሙሽራይቱ
12ንጉሡ በድንክ አልጋው ላይ ዐረፍ ብሎ ሳለ
የሽቶዬ መዓዛ ቤቱን ሁሉ ሞላው።
13ውዴ በጡቶቼ መካከል እንደሚያርፍ፥
መዓዛው እንደ ተቋጠረ ከርቤ ነው።
14ውዴ፥ ዔንገዲ ተብሎ በሚጠራው የወይን ተክል ቦታ
እንደ በቀለ የበረሓ አበባ ነው።
ሙሽራው
15ፍቅሬ ሆይ! እንዴት የተዋብሽ ነሽ!
እንዴትስ ያማርሽ ነሽ!
ዐይኖችሽ እንደ ርግብ ውብ ናቸው።
ሙሽራይቱ
16ውዴ ሆይ! አንተም እኮ ውብ ነህ፤
እጅግም ደስ ታሰኛለህ፤
አልጋችንም እንደ ለምለም ሣር ደስ የሚያሰኝ ነው።
17የቤታችን ምሰሶ የሊባኖስ ዛፍ ነው፤
ጣራውም በጥድ እንጨት የተዋቀረ ነው።
Currently Selected:
መኃልየ መኃልይ 1: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997