2ኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 2
2
ዳዊት የይሁዳ ንጉሥ ሆነ
1ከዚህ በኋላ ዳዊት፥ “ከይሁዳ ከተሞች ወደ አንዲቱ ልውጣን?” ብሎ ጌታን ጠየቀ። ጌታም፥ “አዎን ውጣ” አለው። ዳዊትም፥ “ወደ የትኛዪቱ ልሂድ?” ሲል ጠየቀ። እርሱም፥ “ወደ ኬብሮን” ብሎ መለሰለት። 2#1ሳሙ. 25፥42-43።ስለዚህ ዳዊት ወደዚያ ወጣ፤ ሁለቱ ሚስቶቹ ኢይዝራኤላዊቷ አሒኖዓምና የቀርሜሎሳዊው የናባል ሚስት የነበረችው አቢጌልም ከእርሱ ጋር ነበሩ። 3እንዲሁም ዳዊት አብረውት የነበሩትን ሰዎች ከነቤተሰቦቻቸው አመጣቸው፤ እነርሱም በኬብሮን ከተሞች ተቀመጡ። 4#1ሳሙ. 31፥11-13።የይሁዳም ሰዎች ወደ ኬብሮን መጡ፤ በዚያም ዳዊትን ቀብተው በይሁዳ ቤት ላይ አነገሡት። ሳኦልን የቀበሩት የያቤሽ ገለዓድ ሰዎች መሆናቸውን ለዳዊት በነገሩት ጊዜ፥ 5እርሱም ወደ ያቤሽ ገለዓድ መልእክተኞችን ልኮ እንዲህ አላቸው፥ “በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ ጌታችሁን ሳኦልን በመቅበር በጎነት በማሳየታችሁ ጌታ ይባርካችሁ፤ 6አሁንም ጌታ ጽኑ ፍቅሩንና ታማኝነቱን ይግለጥላችሁ! እናንተ ይህን ስላደረጋችሁ፥ እኔም እንደዚሁ በጎ ነገር አደርግላችኋለሁ፤ 7እንግዲህ ጠንክሩ፤ በርቱ ጌታችሁ ሳኦል ሞቷልና፤ የይሁዳ ቤትም እኔን ቀብተው በላያቸው አንግሠውኛል።”
ጦርነት በዳዊት ቤትና በሳኦል ቤት
8 #
1ሳሙ. 14፥50። በዚህ ጊዜ የሳኦል ሠራዊት አዛዥ የኔር ልጅ አበኔር፥ የሳኦልን ልጅ ኢያቡስቴን ወስዶ ወደ ማሕናይም አሻገረው፤ 9እርሱንም በገለዓድ ላይ፥ በአሴር፥ በኢይዝራኤል፥ በኤፍሬምና በብንያም እንዲሁም በእስራኤል ሁሉ አነገሠው። 10የሳኦል ልጅ ኢያቡስቴ በእስራኤል ላይ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው አርባ ዓመት ነበረ፤ ሁለት ዓመትም ገዛ። የይሁዳ ቤት ግን ዳዊትን ተከተለ። 11#2ሳሙ. 5፥5፤ 1ነገ. 2፥11።ዳዊት በኬብሮን ነግሶ እስራኤልን የገዛው ሰባት ዓመት ከስድስት ወር ነበረ።
12የኔር ልጅ አበኔር፥ ከሳኦል ልጅ ከኢያቡስቴ አገልጋዮች ጋር ሆኖ ከማሕናይም ተነሥተው ወደ ገባዖን ሄዱ። 13እነርሱንም የጽሩያ ልጅ ኢዮአብና የዳዊት ሰዎች ወጥተው በገባዖን ኲሬ አጠገብ ተገናቿቸው፤ አንዱ ወገን በኲሬው ወዲህ ማዶ፥ ሌላው ወገን ደግሞ በኲሬው ወዲያ ማዶ ተቀመጠ። 14ከዚያም አበኔር፥ ኢዮአብን፥ “ጉልማሶች ይነሡና በፊታችን ትግል ይግጠሙ” አለው። ኢዮአብም፥ “ይሁን እሺ ይግጠሙ” ብሎ መለሰ። 15ስለዚህም ለብንያም ወገንና ለሳኦል ልጅ ለኢያቡስቴ ዐሥራ ሁለት፥ ለዳዊት ደግሞ ዐሥራ ሁለት አገልጋዮቹ ተነሥተው ተቆጠሩ። 16ከዚያም እያንዳንዱ ሰው የባለጋራውን ራስ ያዘ፥ ሰይፉንም በጐኑ ሻጠ፥ ተያይዘውም ወደቁ። ስለዚህም በገባዖን የሚገኘው ያ ስፍራ “የስለታም ሰይፍ ምድር” ተባለ። 17የዚያን ዕለት ፍልሚያ እጅግ መራር ነበር፤ በዳዊትም አገልጋዮች ፊት አበኔርና የእስራኤል ሰዎች ተሸነፉ።
18 #
2ሳሙ. 23፥24፤ 1ዜ.መ. 2፥16፤ 27፥7። ሦስቱ የጽሩያ ልጆች ኢዮአብ፥ አቢሳና አሣሄል እዚያው ነበሩ። አሣሄል እንደ ዱር ሚዳቋ በሩጫ ፈጣን ነበረ፤ 19አቤኔርን ለመያዝ ወደ ቀኝ ወይም ወደ ግራ ሳይል ተከተለው። 20አበኔርም ወደ ኋላው ዘወር ብሎ በመመልከት፥ “አሣሄል! አንተ ነህ?” ሲል፥ “አዎን እኔ ነኝ” ብሎ መለሰለት። 21ከዚያም አበኔር፥ “ወደ ቀኝህ ወይም ወደ ግራህ ዘወር በልና አንዱን ጎልማሳ ይዘህ ምርኮውን ውሰድ” አለው። አሣሄል ግን እርሱን ማሳደዱን ቀጠለ። 22#2ሳሙ. 3፥27-28፤30።እንደገናም አበኔር፥ “እኔን ማሳደድህን ተው! እኔስ ስለምን ከመሬት ጋር ላጣብቅህ? ከዚያስ የወንድምህን የኢዮአብን ፊት እንዴት ብዬ አያለሁ?” አለው። 23አሣሄል ግን ማሳደዱን አልተወም፤ ስለዚህ አበኔር በጦሩ ጫፍ ሆዱን ወጋው፥ ጦሩም በጀርባው በኩል ወጣ፤ አሣሄልም እዚያው ወደቀ፤ ወድቆም በነበረበት ስፍራ ሞተ። እያንዳንዱም ሰው አሣሄል ወድቆ ወደ ሞተበት ስፍራ ሲደርስ ይቆም ነበር።
24ኢዮአብና አቢሳ ግን አበኔርን ተከታተሉት፤ ፀሐይ ስትጠልቅ ወደ ገባዖን ምድረ በዳ በሚወስደው መንገድ ከጊያሕ አጠገብ ወዳለው ወደ አማ ኮረብታ ደርሱ። 25ከዚያም የብንያም ሰዎች ተሰብስበው ከአበኔር ጀርባ በመሆን ግንባር ፈጠሩ፤ በኰረብታውም ጫፍ ላይ ተሰለፉ። 26አበኔር ኢዮአብን ጠርቶ፥ “ሰይፍ በውኑ እስከ ዘለዓለም ያጠፋልን? ፍጻሜውሳ መራራ እንደሆነ አታውቅምን? ሰዎችህ ወንድሞቻቸውን ከማሳደድ እንዲገቱ ትእዛዝ የማትሰጣቸውስ እስከ መቼ ነው?” አለው። 27ኢዮአብም፥ “ሕያው እግዚአብሔርን! ይህን ባትናገር ኖሮ፥ ሰዎቹ እስኪ ነጋ ድረስ ወንድሞቻቸውን ማሳደዱን ባላቆሙም ነበር” ብሎ መለሰ። 28ስለዚህ ኢዮአብ ቀንደ መለከቱን ነፋ፤ ከዚያም በኋላ ሰዎቹ በሙሉ እስራኤልን ማሳደዱን ተዉ ውጊያውንም አቆሙ። 29አበኔርና ሰዎቹም ሌሊቱን ዓራባን አልፈው ሄዱ፤ ዮርዳኖስንም በመሻገር ቢትሮንን ሁሉ ዐልፈው ወደ ማሕናይም መጡ።
30ከዚያም ኢዮአብ አበኔርን ማሳደዱን ትቶ ተመለሰ፤ ሰዎቹንም ሁሉ አንድ ላይ በሰበሰባቸው ጊዜ፥ ከዳዊት ሰዎች አሣሄልን ሳይጨምር፥ ዐሥራ ዘጠኝ ሰዎች መጉደላቸው ታወቀ። 31የዳዊት አገልጋዮች ግን ከአበኔር ጋር ከነበሩት ሦስት መቶ ሥልሳ ብንያማውያን ገደሉ። 32አሣሄልንም ከወደቀበት አንሥተው በቤተልሔም በሚገኘው በአባቱ መቃብር ቀበሩት። ከዚያም ኢዮአብና ሰዎቹ ሌሊቱን ሁሉ ሲገሠግሡ አድረው፥ ኬብሮን ንጋት ሆነ።
Currently Selected:
2ኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 2: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ