የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኦሪት ዘፀአት 26

26
ድንኳኑ
1“ከተፈተለ ከጥሩ በፍታ፥ ከሰማያዊ፥ ከሐምራዊና ከቀይ ግምጃ የተሠሩ ዐሥር መጋረጆች ያሉበትን ድንኳን ሥራ፤ ብልህ ሠራተኛ እንደሚሠራ ኪሩቤል በእነርሱ ላይ ይሁኑ። 2የእያንዳንዱ መጋረጃ ርዝመት ሀያ ስምንት ክንድ፥ ወርዱም አራት ክንድ ይሁን፤ የመጋረጆቹ ሁሉ መጠን እኩል ይሁን። 3አምስቱ መጋረጆች እርስ በርሳቸው የተጋጠሙ ይሁኑ፤ አምስቱም መጋረጆች እንዲሁ እርስ በርሳቸው የተጋጠሙ ይሁኑ። 4ከሚጋጠሙት መጋረጆች በአንደኛው መጋረጃ ዘርፍ ላይ የሰማያዊውን ግምጃ ቀለበቶች አድርግ፤ ደግሞም ከተጋጠሙት ከሌሎች በአንደኛው መጋረጃ ዘርፍ ላይ እንዲሁ አድርግ። 5አምሳ ቀለበቶችን በአንድ መጋረጃ አድርግ፥ አምሳውንም ቀለበቶች በሁለተኛው መጋረጃ ዘርፍ አድርግ፤ ቀለበቶቹ ሁሉ እርስ በርሳቸው ፊት ለፊት እንዲሆኑ አድርግ። 6አምሳ የወርቅ መያዣዎችን ሥራ፤ ድንኳኑም አንድ ወጥ እንዲሆን መጋረጃዎቹን እርስ በርሳቸው በመያዣዎች አጋጥማቸው። 7ከማደሪያውም በላይ ለመሸፈኛ የሚሆኑ መጋረጆች ከፍየል ጠጉር ሥራ፤ ዐሥራ አንድ መጋረጆች ትሠራለህ። 8የእያንዳንዱ መጋረጃ ርዝመቱ ሠላሳ ክንድ፥ የእያንዳንዱም መጋረጃ ወርድ አራት ክንድ ይሁን፤ የዐሥራ አንዱም መጋረጆች መጠን እኩል ይሁን። 9አምስቱን መጋረጆች ለብቻ፥ ስድስቱንም መጋረጆች ለብቻ አንድ ሆነው ይጋጠሙ፤ ስድስተኛው መጋረጃ በድንኳኑ ፊት ይደረብ። 10በአንደኛው መጋረጃ ዘርፍ ላይ አምሳ ቀለበቶች አድርግ፤ በሁለተኛው መጋረጃ ዘርፍ ላይ እንዲሁ አምሳ ቀለበቶች አድርግ። 11አምሳ የናስ መያዣዎችን ሥራ፥ መያዣዎቹንም ወደ ቀለበቶቹ አስገባቸው፥ ድንኳኑንም አጋጥመው። 12ከድንኳኑ መጋረጆች የቀረ ትርፍ ግማሽ መጋረጃ በማደሪያው ጀርባ ይንጠልጠል። 13ማደሪያውን እንዲሸፍን ከርዝመቱ በአንድ ወገን አንድ ክንድ፥ በአንድ ወገንም አንድ ክንድ ከድንኳኑ መጋረጆች የቀረው ትርፍ በማደሪያው ውጭ በወዲህና በወዲያ ይንጠልጠል። 14ለድንኳኑም መደረቢያ ከቀይ አውራ በግ ቁርበት፥ ከዚያም በላይ ሌላ መደረቢያ ከአስቆጣ ቁርበት አድርግ።
ስለ ሳንቃዎቹ
15“ለማደሪያውም የሚቆሙትን ሳንቃዎች ከግራር እንጨት አድርግ። 16የሳንቃውም ሁሉ ርዝመቱ ዐሥር ክንድ፥ ወርዱም አንድ ክንድ ተኩል ይሁን። 17ለእያንዳንዱም ሳንቃ አንዱን በአንዱ ላይ የሚያያይዙ ሁለት ማጋጠሚያዎች ይሁኑለት፤ ለማደሪያው ሳንቃዎች ሁሉ እንዲሁ አድርግ። 18ለማደሪያውም በደቡብ ወገን ሀያ ሳንቃዎችን አድርግ። 19ከሀያውም ሳንቃዎች በታች አርባ የብር እግሮችን አድርግ፤ ከእያንዳንዱ ሳንቃ በታች ለሁለት ማጋጠሚያዎች ሁለት እግሮች ይሁኑ። 20ለማደሪያው ለሁለተኛው ወገን በሰሜን በኩል ሀያ ሳንቃዎች፥ 21ለእነርሱም አርባ የብር እግሮች ይሁኑ፤ ከእያንዳንዱም ሳንቃ በታች ሁለት እግሮች ይሁኑ። 22ለማደሪያውም በምዕራቡ ወገን በስተ ኋላ ስድስት ሳንቃዎችን አድርግ። 23ለማደሪያውም ለሁለቱ ማዕዘን በስተ ኋላ ሁለት ሳንቃዎችን አድርግ። 24ከታችም እስከ ላይ እስከ አንደኛው ቀለበት ድረስ አንዱ ሳንቃ ድርብ ይሁን፤ እንዲሁም ለሁለቱ ይሁን፤ እነርሱም ለሁለቱ ማዕዘን ይሆናሉ። 25ስምንት ሳንቃዎችና ዐሥራ ስድስት የብር እግሮቻቸው ይሁኑ፥ ከእያንዳንዱም ሳንቃ በታች ሁለት እግሮች ይሆናሉ። 26ከግራርም እንጨት በማደሪያው በአንድ ወገን ላሉት ሳንቃዎች አምስት መወርወሪያዎች፥ 27በማደሪያውም በሁለተኛው ወገን ላሉት ሳንቃዎች አምስት መወርወሪያዎች፥ በማደሪያውም በስተ ኋላ በምዕራብ ወገን ላሉት ሳንቃዎች አምስት መወርወሪያዎች አድርግ። 28መካከለኛውም መወርወሪያ በሳንቃዎች መካከል ከዳር እስከ ዳር ይለፍ። 29ሳንቆቹንም በወርቅ ለብጣቸው፥ ቀለበቶቻቸውንም የመወርወሪያ ቤት እንዲሆኑላቸው ከወርቅ ሥራቸው፥ መወርወሪያዎችንም በወርቅ ለብጣቸው። 30ማደሪያውንም በተራራ እንዳሳየሁህ ምሳሌ አቁም።
መጋረጃው
31“መጋረጃውንም ከሰማያዊ ከሐምራዊም ከቀይም ግምጃ ከተፈተለ ከጥሩ በፍታም አድርግ፤ ብልህ ሠራተኛ እንደሚሠራ ኪሩቤል በእርሱ ላይ ይሁኑ። 32በወርቅ በተለበጡት ከግራር እንጨትም በተሠሩት በአራቱ ምሰሶች ላይ ስቀለው፤ ኩላቦቻቸውም ከወርቅ፥ አራቱም እግሮቻቸው ከብር የተሠሩ ይሁኑ። 33#ዕብ. 6፥19፤ 9፥3-5።መጋረጃውንም ከመያዣዎቹ በታች ታንጠለጥለዋለህ፥ በመጋረጃውም ውስጥ የምስክርን ታቦት አግባው፤ መጋረጃውም በቅድስቱና በቅድስተ ቅዱሳኑ መካከል መለያ ይሁናችሁ። 34በቅድስተ ቅዱሳኑም ውስጥ የስርየት መክደኛውን በምስክሩ ታቦት ላይ አድርግ። 35ገበታውንም በመጋረጃው ውጭ፥ መቅረዙንም በገበታው ፊት ለፊት በማደሪያው በደቡብ ወገን አድርግ፤ ገበታውንም በሰሜን ወገን አድርገው። 36ለድንኳኑም ደጃፍ ከሰማያዊ ከሐምራዊም ከቀይም ግምጃ ከተፈተለ ከጥሩ በፍታም በጥልፍ አሠራር የተሠራ መጋረጃ አድርግለት። 37ለመጋረጃውም አምስት ምሰሶች ከግራር እንጨት አድርግ፤ በወርቅም ለብጣቸው፤ ኩላቦቻቸውም ከወርቅ የተሠሩ ይሁኑ፤ አምስትም እግሮች አድርግላቸው።”

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ