ትንቢተ ሕዝቅኤል 20
20
እስራኤል በአመፀኝነት ቀጠለች
1እንዲህም ሆነ በሰባተኛው ዓመት፥ በአምስተኛው ወር፥ ከወሩም በአሥረኛው ቀን፥ ከእስራኤል ሽማግሌዎች ሰዎች ጌታን ሊጠይቁ#20፥1 የጌታን ሐሳብ ሊጠይቁ መጡ፥ በፊቴም ተቀመጡ። 2የጌታም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 3የሰው ልጅ ሆይ፥ የእስራኤልን ሽማግሌዎች ተናገራቸው፥ እንዲህም በላቸው፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እናንተ እኔን ልትጠይቁ መጣችሁን? እኔ ሕያው ነኝ፥ ለእናንተ አልጠየቅም፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 4ትፈርድባቸዋለህን? የሰው ልጅ ሆይ፥ ትፈርድባቸዋለህን? የአባቶቻቸውን ርኩሰት አስታውቃቸው፤ 5#ዘፀ. 6፥2-8።እንዲህም በላቸው፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እስራኤልን በመረጥሁበት ቀን፥ ለያዕቆብ ቤት ዘር ማልሁላቸው፥ በግብጽም ምድር ራሴን ገለጥሁላቸው፦ እኔ ጌታ አምላካችሁ ነኝ ብዬ ማልሁላቸው። 6በዚያ ቀን ከግብጽ ምድር ወዳዘጋጀሁላችሁ፥ ወተትና ማር ወደምታፈስሰው፥ የምድርም ሁሉ ጌጥ ወደምትሆን ምድር አወጣቸው ዘንድ ማልሁላቸው። 7እኔም፦ ከእናንተ እያንዳንዱ የዓይኑን ርኩሰት ይጣል፥ በግብጽም ጣዖታት አትርከሱ፤ እኔ ጌታ አምላካችሁ ነኝ አልኋቸው። 8እነርሱ ግን ዐመፁብኝ ይሰሙኝም ዘንድ አልወደዱም፥ ሁሉም እያንዳንዱ የዓይኑን ርኩሰት አልጣለም የግብጽንም ጣዖታት አልተወም፤ በዚህም ጊዜ፦ በግብጽ ምድር መካከል ቁጣዬን እፈጽምባቸው ዘንድ መዓቴን አፈስስባቸዋለሁ አልሁ። 9ነገር ግን በመካከላቸው ባሉ ከግብጽም ምድር አወጣቸው ዘንድ በፊታቸው በተገለጥሁላቸው በአሕዛብ ፊት ስሜ እንዳይረክስ ብዬ ስለ ስሜ ሠራሁ።
10ከግብጽም ምድር አወጣኋቸው ወደ ምድረ በዳም አመጣኋቸው። 11#ዘሌ. 18፥5።ሰው ቢያደርገው ኖሮ በሕይወት የሚኖርበትን ሥርዓቴንም ሰጠኋቸው፥ ፍርዴንም አስታወቅኋቸው። 12#ዘፀ. 31፥13-17።የምቀድሳቸውም እኔ ጌታ እንደሆንሁ ያውቁ ዘንድ፥ በእኔና በእነርሱ መካከል ምልክት ይሆኑ ዘንድ ሰንበታቴን ሰጠኋቸው። 13ነገር ግን የእስራኤል ቤት በምድረ በዳ ዐመፁብኝ፤ ሰው ቢያደርገው ኖሮ በሕይወት የሚኖርበትንም ፍርዴን ጣሱ፥ በትእዛዜም አልሄዱም፥ ሰንበታቴንም ፈጽመው አረከሱ። በዚህም ጊዜ፦ አጠፋቸው ዘንድ ቁጣዬን በምድረ በዳ አፈስስባቸዋለሁ አልሁ። 14ነገር ግን በፊታቸው ባወጣኋቸው በአሕዛብ ፊት ስሜ እንዳይረክስ ብዬ ስለ ስሜ ሠራሁ። 15#ዘኍ. 14፥26-35።ወተትና ማርም ወደምታፈስሰው የምድር ሁሉ ጌጥ ወደምትሆን ወደ ሰጠኋቸው ምድር አላመጣቸውም ብዬ በምድረ በዳ ማልሁባቸው። 16ልባቸው ጣዖቶቻቸውን ተከትሎአልና፥ ፍርዴንም ጥሰዋልና፥ በሥርዓቴም አልሄዱምና፥ ሰንበታቴንም አርክሰዋልና። 17ነገር ግን ዓይኔ ራራችላቸው እኔም አላጠፋኋቸውም፥ በምድረ በዳም ፈጽሜ አልፈጀኋቸውም።
18ለልጆቻቸውም በምድረ በዳ እንዲህ አልኋቸው፦ በአባቶቻችሁ ሥርዓት አትሂዱ ወጋቸውንም አትጠብቁ በጣዖቶቻቸውም አትርከሱ። 19እኔ ጌታ አምላካችሁ ነኝ፤ በትእዛዜ ሂዱ ፍርዴንም ጠብቁ አድርጓትም። 20ሰንበታቴንም ቀድሱ፤ እኔም ጌታ አምላካችሁ እንደሆንሁ እንድታውቁ በእኔና በእናንተ መካከል ምልክት ይሆናሉ። 21ልጆች ግን ዐመፁብኝ፥ ሰው ቢያደርገው ኖሮ በሕይወት የሚኖርባትን ፍርዴን ጠብቀው አላደረጓትም በሥርዓቴም አልሄዱም፥ ሰንበታቴንም አረከሱ፤ በዚህም ጊዜ፦ መዓቴን አፈስስባቸዋለሁ ቁጣዬንም በምድረ በዳ እፈጽምባቸዋለሁ አልሁ። 22ነገር ግን እጄን መለስሁ፥ በፊታቸውም ባወጣኋቸው በአሕዛብ ፊት ስሜ እንዳይረክስ ብዬ ስለ ስሜ ሠራሁ። 23#ዘሌ. 26፥33።ደግሞም ወደ አሕዛብ እበትናቸው ዘንድ፥ በአገሮችም እበትናቸው ዘንድ በምድረ በዳ ማልሁባቸው፤ ፍርዴን አላደረጉምና፤ 24ሥርዓቴንም ጥሰዋልና፤ ሰንበታቴንም አርክሰዋልና፤ ዓይናቸውም የአባቶቻቸውን ጣዖታቶች ተከትለዋልና። 25ደግሞም መልካም ያልሆነውን ሥርዓት በሕይወት የማይኖሩበትንም ፍርድ ሰጠኋቸው። 26እኔም ጌታ እንደሆንሁ እንዲያውቁ አጠፋቸው ዘንድ፥ ማኅፀን የሚከፍተውን ሁሉ በእሳት ባሳለፉ ጊዜ፥ በመባቸው አረከስኋቸው።
27ስለዚህ፥ የሰው ልጅ ሆይ፥ ለእስራኤል ቤት ተናገር እንዲህም በላቸው፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በዚህም ደግሞ አባቶቻችሁ ባደረጉት ዓመጽ አስቆጡኝ። 28እሰጣቸውም ዘንድ ወደ ማልሁላቸው ምድር ባገባኋቸው ጊዜ፥ ከፍ ያለውን ኮረብታ ሁሉ ቅጠልማውንም ዛፍ ሁሉ አዩ፥ በዚያም መሥዋዕታቸውን ሠዉ በዚያም የሚያስቆጣኝን ቁርባናቸውን አቀረቡ በዚያም ደግሞ ጣፋጩን ሽታቸውን አደረጉ በዚያም የመጠጥ ቁርባናቸውን አፈሰሱ። 29እኔም፦ እናንተ ወደ እርሱ የምትሄዱበት ከፍታ ምንድነው? አልኋቸው። እስከ ዛሬም ድረስ ስሙ ባማ#20፥29 ለጣዖት የሚሰዉበት ከፍታ ነው። ተብሎ ተጠርቶአል። 30ስለዚህ ለእስራኤል ቤት እንዲህ በላቸው፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እንደ አባቶቻችሁ ልማድ ትረክሳላችሁን? ርኩሰታቸውንም ተከትላችሁ ታመነዝራላችሁን? 31ቁርባናችሁን ባቀረባችሁ ጊዜ፥ ልጆቻችሁንም በእሳት ባሳለፋችሁ ጊዜ፥ እስከ ዛሬ ድረስ በጣዖቶቻችሁ ትረክሳላችሁን የእስራኤል ቤት ሆይ፥ ከእናንተስ ዘንድ እጠየቃለሁን? እኔ ሕያው ነኛና ከእናንተ ዘንድ አልጠየቅም፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ 32ለእናንተም፦ እንደ አሕዛብና እንደ ምድር ወገኖች እንሆናለን፥ እንጨትና ድንጋይም እናመልካለን የሚል ከልባችሁ የወጣ አሳብ አይፈጸምላችሁም።
እግዚአብሔር እስራኤልን ያድሳል
33እኔ ሕያው ነኝና በበረታች እጅና በተዘረጋች ክንድ በፈሰሰችም መዓት እነግሥባችኋለሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 34ከአሕዛብም ዘንድ አወጣችኋለሁ ከተበተናችሁባትም አገር ሁሉ በበረታች እጅና በተዘረጋች ክንድ በፈሰሰችም መዓት እሰበስባችኋለሁ። 35ወደ አሕዛብም ምድረ በዳ አመጣችኋለሁ በዚያም ፊት ለፊት ከእናንተ ጋር እፋረዳለሁ። 36በግብጽ ምድረ በዳ ከአባቶቻችሁ ጋር እንደ ተፋረድሁ እንዲሁ ከእናንተ ጋር እፋረዳለሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 37ከበትርም በታች አሳልፋችኋለሁ ወደ ቃል ኪዳንም እስራት አገባችኋለሁ፤ 38ከእናንተም ዘንድ ዓመፀኞችንና የበደሉኝን እለያለሁ። ከኖሩባትም ምድር አወጣቸዋለሁ፥ ወደ እስራኤል ምድር ግን አይገቡም፥ እኔም ጌታ እንደሆንሁ ታውቃላችሁ። 39ጌታ እግዚአብሔርም እንዲህ ይላል፦ እናንተ የእስራኤል ቤት ሆይ፥ ሂዱ፥ ከዚህም በኋላ ትሰሙኝ ዘንድ ባትወድዱ ሁላችሁ ጣዖቶቻችሁን አምልኩ። ነገር ግን ከእንግዲህ ወዲህ በቁርባናችሁና በጣዖቶቻችሁ ቅዱሱን ስሜን አታረክሱም።
40በቅዱሱ ተራራዬ፥ ከፍ ባለው በእስራኤል ተራራ ላይ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፥ በዚያ የእስራኤል ቤት ሁሉ ሁላቸው በምድሩ ላይ ያመልኩኛል፤ በዚያም እቀበላቸዋለሁ፥ በዚያም ቁርባናችሁን በኩራታችሁንም የቀደሳችሁትንም ነገር ሁሉ እፈልጋለሁ። 41ከአሕዛብም ዘንድ ባወጣኋችሁ ጊዜ ከተበተናችሁባትም አገር ሁሉ በሰበሰብኋችሁ ጊዜ እንደ ጣፋጭ ሽታ እቀበላችኋለሁ፥ በአሕዛብም ፊት እቀደስባችኋለሁ። 42ለአባቶቻችሁም እሰጣት ዘንድ ወደ ማልሁላቸው ምድር ወደ እስራኤል አገር ባገባኋችሁ ጊዜ፥ እኔ ጌታ እንደሆንሁ ታውቃላችሁ። 43በዚያም የረክሳችሁባትን መንገዳችሁንና ሥራችሁን ሁሉ ታስባላችሁ፤ ስለ ሠራችሁትም ክፋታችሁ ሁሉ ራሳችሁን ትጸየፋላችሁ። 44የእስራኤል ቤት ሆይ፥ እንደ ክፉ መንገዳችሁና እንደ ርኩስ ሥራችሁ ሳይሆን ስለ ስሜ ስል በሠራሁላችሁ ጊዜ፥ እኔ እግዚአብሔር እንደሆንሁ ታውቃላችሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
በደቡብ ላይ የተነገረ ትንቢት
45የጌታ ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 46የሰው ልጅ ሆይ፥ ፊትህን ወደ ደቡብ አቅና ወደ ደቡብም ተናገር በደቡብም ባለው ዱር ላይ ትንቢት ተናገር፤ 47ለደቡብም ዱር፦ የጌታን ቃል ስማ፤ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ በአንተ ውስጥ እሳት አነድዳለሁ፤ በውስጥህም ያለውን የለመለመውንና የደረቀውን ዛፍ ሁሉ ይበላል፤ የሚቃጠል ነበልባል አይጠፋም፤ ከደቡብም ጀምሮ እስከ ሰሜን ድረስ ፊት ሁሉ ይቃጠልበታል። 48እኔ ጌታ እንዳነደድሁት ሥጋ ለባሽ ሁሉ ያያል፥ እርሱም አይጠፋም በለው። 49እኔም፦ ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፥ ወዮ! እነርሱ ስለ እኔ፦ ይህ ምሳሌን የሚመስል አይደለምን? ብለዋል አልሁ።
Currently Selected:
ትንቢተ ሕዝቅኤል 20: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ