ትንቢተ ሕዝቅኤል 24
24
የማፍያ ድስት
1በዘጠነኛው ዓመት፥ በአሥረኛው ወር፥ ከወሩም በአሥረኛው ቀን፥ የጌታ ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 2#2ነገ. 25፥1፤ ኤር. 52፥4።የሰው ልጅ ሆይ፥ የዚህን ቀን፥ የዛሬን ቀን ስም ጻፍ፤ በዛሬዋ ቀን የባቢሎን ንጉሥ ወደ ኢየሩሳሌም ቀረበ። 3ለዓመፀኛውም ቤት ምሳሌን ተናገር፥ እንዲህም በላቸው፥ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ጣደው፥ ድስቱን ጣደው፥ ውኃም ጨምርበት። 4የስጋ ቁራጮች፥ መልካም የሆነው የስጋ ቁራጭ ሁሉ፥ ጭኑንና ወርቹን በውስጡ ጨምር፤ የተመረጡ አጥንቶችንም ሙላበት። 5የተመረጠውን መንጋ ውሰድ፥ አጥንቶቹም እንዲበስሉ ከስሩ ማገዶ ጨምር፤ በደንብ ይንተክተክ፥ አጥንቶቹም በውስጡ ይብሰሉ።
6ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ዝገትዋ ላለባት ዝገትዋም ከእርሷ ላልወጣ ድስት፥ ለደም ከተማ ወዮላት! ቁራጭ ቁራጩን አውጣ፥ ዕጣ አልወደቀባትም። 7ደምዋ በመካከሏ አለና፤ በተራቆተ ድንጋይ ላይ አስቀመጠችው፤ በአፈር እንዲከደን መሬት ላይ አላፈሰሰችውም። 8እንድቆጣና፥ በቀልንም እንድበቀል፥ ደምዋ እንዳይከደን በተራቆተ ድንጋይ ላይ አደረግሁ። 9ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ለደም ከተማ ወዮላት! እኔ ደግሞ ማገዶውን ብዙ አደርገዋለሁ። 10እንጨቶችን ጨምር፥ እሳቱን አንድድ፥ ሥጋውን ቀቅል፥ ማጣፈጫ ጨምረህ አደባልቀው፥ አጥንቶቹ ይቃጠሉ። 11እንድትሞቅ፥ ናስዋም እንድትግል፥ ርኩሰትዋም በውስጧ እንዲቀልጥ ዝገትዋም እንዲጠፋ ባዶዋን ፍም ላይ አስቀምጣት። 12ብዙ ለፍታ ደከመች፥ ሆኖም የዝገቱ ክምር በእሳት እንኳ አልለቀቀም። 13በርኩሰትሽ ሴሰኝነት አለ፥ መዓቴን በአንቺ ላይ እስክጨርስ ድረስ ከእንግዲህ ወዲያ ከርኩሰትሽ ንፁህ አትሆኚም ምክንያቱም አነጻሁሽ ነገር ግን ንፁህ አልሆንሺምና። 14እኔ ጌታ ተናግሬአለሁ፤ ይፈፀማል፥ እኔም አደርገዋለሁ፤ አልቆጠብም፥ አልራራም፥ አልጸጸትም። እንደ መንገድሽና እንደ ሥራሽ ይፈርዱብሻል፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
የሕዝቅኤል በሚስቱ ሞት ማዘን
15የጌታ ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 16የሰው ልጅ ሆይ፥ እነሆ የዐይንህን ምኞት በቅፅበት እወስድብሃለሁ፤ ቢሆንም ግን ዋይታ አታሰማ፥ አታልቅስ፥ እንባህንም አታፍስስ። 17በዝምታ ተክዝ፥ ለሙታን አታልቅስ፤ መጠምጠሚያህን በራስህ ላይ አድርግ፥ ጫማህንም በእግርህ አጥልቅ፤ ከንፈርህን አትሸፍን፥ የዕዝን እንጀራም አትብላ። 18እኔም በማለዳ ለሕዝቡ ተናገርሁ፥ ማታም ሚስቴ ሞተች፤ በማግስቱም እንደ ታዘዝሁ አደረግሁ።
19ሕዝቡም፦ “እነዚህ የምታደርጋቸውው ነገሮች ለእኛ ምን እንደሆነ አትነግረንምን?” አሉኝ። 20እኔም እንዲህ አልኋቸው፦ “የጌታ ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 21ለእስራኤል ቤት እንዲህ በል፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ የኃይላችሁ ትምክሕት፥ የዓይናችሁ ምኞት፥ የነፍሳችሁ ናፍቆት የሆነውን መቅደሴን አረክሳለሁ፤ ትታችኋቸው የሄዳችሁ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁ በሰይፍ ይወድቃሉ። 22እኔ እንዳደረግሁ እናንተም ታደርጋላችሁ፤ ከንፈራችሁን አትሸፍኑም፥ የዕዝን እንጀራም አትበሉም። 23መጠምጠሚያችሁ በራሳችሁ ላይ፥ ጫማችሁም በእግራችሁ ይሆናል፤ ዋይ አትሉም ወይም አታለቅሱም፤ በኃጢአታችሁ ትመነምናላችሁ፥ እርስ በእርሳችሁም ታለቅሳላችሁ። 24እንግዲህ ሕዝቅኤል ምልክት ይሆናችኋል፤ እርሱ ያደረገውን ሁሉ እናንተም ታደርጋላችሁ። ይህ በሚመጣበት ጊዜ እኔ ጌታ እግዚአብሔር እንደሆንሁ ታውቃላችሁ።”
25አንተም የሰው ልጅ ሆይ፥ ምሽጋቸውን፥ የክብራቸውን ደስታ፥ የዓይናቸውን ምኞት፥ የነፍሳቸውን ናፍቆት፥ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውን በወሰድሁባቸው ቀን፥ 26በዚያን ቀን፥ ያመለጠ ሰው ይህን ነገር ጆሮዎችህ እንዲሰሙ ወደ አንተ ይመጣል። 27በዚያን ቀን አፍህ ላመለጠው ሰው ይከፈታል፥ ትናገራለህም፥ ከዚያ በኋላም ድዳ አትሆንም። ስለዚህ ምልክት ትሆናቸዋለህ፤ እኔም ጌታ እንደሆንሁ ያውቃሉ።
Currently Selected:
ትንቢተ ሕዝቅኤል 24: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ