ትንቢተ ሕዝቅኤል 34
34
የእስራኤል ሐሰተኛ እረኞች
1የጌታ ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 2የሰው ልጅ ሆይ፥ ትንቢት ተናገር፥ በእስራኤል እረኞች ላይ ትንቢት ተናገር፥ እረኞቹንም እንዲህ በላቸው፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ራሳቸውን ለመገቡ ለእስራኤል እረኞች ወዮላቸው! እረኞች በጎችን ማሰማራት አይገባቸውምን? 3ጮማውን ትበላላችሁ ሱፉንም ትለብሳላችሁ፥ የሰቡትን ታርዳላችሁ፤ መንጋውን ግን አትጠብቁም። 4የደከሙትን አላበረታችሁም፥ የታመመውን አላከማችሁትም፥ የተሰበረውን አልጠገናችሁትም፥ የባዘነውን አልመለሳችሁትም፥ የጠፋውንም አልፈለጋችሁትም በኃይልና በጭቆና ገዛችኋቸው። 5#ዘኍ. 27፥17፤ 1ነገ. 22፥17፤ ማቴ. 9፥36፤ ማር. 6፥34።እረኛ ስለ ሌለ ተበተኑ፥ ለምድርም አራዊት ሁሉ መብል ሆኑ፥ ተበተኑም። 6በጎቼ በተራሮች ሁሉና በረዘሙ ኮረብቶች ሁሉ ላይ ተቅበዝብዘዋል፥ በጎቼም በምድር ፊት ሁሉ ላይ ተበትነዋል፤ የሚሻም የሚፈልግም የለም።
7ስለዚህ እረኞች ሆይ፥ የጌታን ቃል ስሙ፤ 8ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እኔም ሕያው ነኝና እረኛ ስለ ሌለ እረኞቼም በጎቼን ስላልፈለጉ እረኞችም ራሳቸውን እንጂ በጎቼን ስላላሰማሩ፥ በጎቼ ንጥቂያ ሆነዋልና፥ በጎቼም ለምድር አራዊት ሁሉ መብል ሆነዋልና 9ስለዚህ እረኞች ሆይ፥ የጌታን ቃል ስሙ፤ 10ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ በእረኞች ላይ ነኝ፥ መንጋዎቼን ከእጃቸው እፈልጋለሁ፥ መንጋዎቼን ከማሰማራት አስተዋቸዋለሁ። ከዚያም ወዲያ እረኞች ራሳቸውን አያስማሩም፤ በጎቼንም ከአፋቸው አድናለሁ፥ መብልም አይሆኑላቸውም።
እውነተኛው እረኛ እግዚአብሔር
11ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፦ እነሆ እኔ ራሴ በጎቼን እሻለሁ እፈልጋቸዋለሁም። 12እረኛ በተበተኑት መንጋዎቹ መካከል ሳለ መንጋውን እንደሚፈልግ፥ እንዲሁ በጎቼን እፈልጋለሁ፤ በደመናና በጨለማ ቀን፥ ከተበተኑት ስፍራ ሁሉ አድናቸዋለሁ። 13ከሕዝቦች አወጣቸዋለሁ፥ ከአገሮች እሰበስባቸዋለሁ፥ ወደ ገዛ አገራቸውም አመጣቸዋለሁ፤ በእስራኤል ተራሮች ላይ፥ በፈሳሾች አጠገብ፥ በምድሪቱም መኖሪያ በሚሆኑ ስፍራዎች ሁሉ አሰማራቸዋለሁ። 14በመልካም ማሰማርያ አሰማራቸዋለሁ ጋጣቸውም በእስራኤል ተራሮች ከፍታ ላይ ይሆናል፤ በዚያ በመልካም ጋጣ ውስጥ ይመሰጋሉ፥ በእስራኤልም ተራሮች ላይ በለመለመ ማሰማርያ ይሰማራሉ። 15እኔ ራሴ በጎቼን አሰማራለሁ አስመስጋቸዋለሁም፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 16የጠፋውን እፈልጋለሁ፥ የባዘነውን እመልሳለሁ፥ የተሰበረውንም እጠግናለሁ የደከመውንም አበረታለሁ፤ የወፈረውንና የበረታውን አጠፋለሁ፤ በፍትሕም እጠብቀዋለሁ።
17ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እናንተም መንጋዬ ሆይ፥ እነሆ በበግና በበግ መካከል፥ በአውራ በግና በአውራ ፍየል መካከል እፈርዳለሁ። 18የቀረውን ማሰማርያችሁን በእግራችሁ የረገጣችሁት፥ በመልካሙ ማሰማርያ መሰማራታችሁ ባይበቃችሁ ነውን? የቀረውንስ ውኃ በእግራችሁ ያደፈረሳችሁት፥ ጥሩውን ውኃ መጠጣታችሁ ባይበቃችሁ ነውን? 19መንጋዎቼ በእግራችሁ በረገጣችሁት ይሰማራሉ በእግራችሁም ያደፈረሳችሁትን ይጠጣሉ።
20ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላቸዋል፦ እነሆ እኔ በወፈረ በግና በከሳ በግ መካከል እፈርዳለሁ። 21ወደ ውጭ እስክትበትኑአቸው ድረስ በጎንና በትከሻ ስለምትገፉ፥ የደከሙትን ሁሉ በቀንዳችሁ ስለምትወጉአቸው፥ 22ስለዚህ መንጋዬን አድናለሁ፥ ከእንግዲህ ወዲህም ንጥቂያ አይሆኑም፤ በበግና በበግ መካከልም እፈርዳለሁ። 23#ራእ. 7፥17።በላያቸውም አንድ እረኛ አቆማለሁ እርሱም ያሰማራቸዋል፥ እርሱም ባርያዬ ዳዊት ነው፤ ያሰማራቸዋል እረኛም ይሆናቸዋል። 24#ሕዝ. 37፥24።እኔም ጌታ፥ አምላክ እሆናቸዋለሁ፥ ባርያዬ ዳዊትም በመካከላቸው አለቃ ይሆናል፤ እኔ ጌታ ተናግሬአለሁ።
25ከእነርሱ ጋር የሰላምን ቃል ኪዳን እገባለሁ፥ ክፉ አራዊትን ከምድሪቱ አጠፋለሁ፤ በሰላምም በምድረ በዳ ይኖራሉ በዱርም ውስጥ ይተኛሉ። 26እነርሱንና በኮረብታዬ ዙሪያ ያሉትን ስፍራዎች ለበረከት አደርጋቸዋለሁ፥ ዝናቡንም በጊዜው አወርዳለሁ፤ የበረከት ዝናቦችም ይሆናሉ። 27የሜዳ ዛፍም ፍሬውን ይሰጣል፥ ምድርም ቡቃያዋን ትሰጣለች፥ በምድራቸውም በሰላም ይኖራሉ፤ የቀንበራቸውንም ዘንግ ስሰብር ከሚገዙአቸውም እጅ ሳድናቸው፥ እኔ ጌታ እንደሆንሁ ያውቃሉ። 28ከእንግዲህም ለሕዝቦች ብዝበዛ አይሆኑም፥ የምድርም አራዊት አይበሉአቸውም፤ በሰላም ይኖራሉ የሚያስፈራቸውም አይኖርም። 29የታወቀ#34፥29 ዝና ያለው የተክል ቦታ አቆምላቸዋለሁ፥ ከእንግዲህ ወዲያ በምድሪቱ ላይ በረሃብ አይሰበሰቡም፤ ከእንግዲህም ወዲያ የሕዝቦችን ስድብ አይሸከሙም። 30እኔ ጌታ አምላካቸው ከእነርሱ ጋር እንዳለሁ፥ እነዚያ የእስራኤል ቤትም ሕዝቤ እንደ ሆኑ ያውቃሉ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 31እናንተም በጎቼ፥ የማሰማርያዬ በጎች፥ ሰዎች ናችሁ እኔም አምላካችሁ ነኝ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
Currently Selected:
ትንቢተ ሕዝቅኤል 34: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ