ትንቢተ ሕዝቅኤል 38
38
በጎግ የተደረገ ወረራ
1የጌታ ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 2#ራእ. 20፥8።የሰው ልጅ ሆይ፥ የማጎግ ምድር፥ በሮሽ፥ በሜሼኽና በቱባል ላይ አለቃ ወደ ሆነው ወደ ጎግ ፊትህን አቅና፥ ትንቢትም ተናገርበት፥ 3እንዲህም በል፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የሮሽ፥ የሜሼኽና የቱባል አለቃ ጎግ ሆይ፥ እነሆ እኔ በአንተ ላይ ነኝ። 4ወደ ኋላ እመልስሃለሁ፥ መንጠቆ በመንጋጋህ አስገባሃለሁ፥ አንተንና ሠራዊትህን ሁሉ፥ ፈረሶችን፥ ፈረሰኞችን፥ የጦር ልብስ የለበሱትን ሁሉ፥ ሁሉም ሰይፍ የያዙ ጋሻና ራስ ቁርን ካደረጉ ታላቅ ጉባኤ ጋር አወጣሃለሁ፥ 5ሁሉም ጋሻና የራስ ቁር የለበሱ ፋርስ፥ ኢትዮጵያና ፉጥም ከእነርሱ ጋር። 6ጎሜርንና ሠራዊቱ ሁሉ፥ በሰሜን ዳርቻ ያለው የቶጋርማ ቤትና ሠራዊቱ ሁሉ፥ ብዙ ሕዝቦችም ከአንተ ጋር አወጣለሁ።
7ተዘጋጅ፥ አንተና ወደ አንተ የተሰበሰቡ ጉባኤ ሁሉ ተዘጋጁ፥ አንተም ጠባቂ ሁናቸው። 8ከብዙ ዘመንም በኋላ ትፈለጋለህ፤ በኋለኛውም ዘመን፥ የዘለዓለም ባድማ በነበሩ በእስራኤል ተራሮች ላይ ከብዙ ሕዝብ ውስጥ ወደ ተሰበሰበች፥ ከሰይፍ ወደ ተመለሰች ምድር ትገባለህ፤ እርሷም ከሕዝብ ውስጥ ወጥታለች ሁሉም ሳይፈሩ ይቀመጡባታል። 9አንተም ወደ ላይ ትወጣለህ፥ እንደ ማዕበል ትመጣለህ፤ አንተና ሠራዊትህ ሁሉ፥ ብዙ ሕዝብም ከአንተ ጋር ሆነው ምድርን እንደ ደመና ትሸፍናላችሁ።
10ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በዚያ ቀን ነገር#38፥10 ዕብራይስጡ ቃላት ወይም ንግግር ይለዋል። ወደ ልብህ ይመጣል፥ ክፉ ሐሳብንም ታስባለህ፤ 11እንዲህም ትላለህ፦ ቅጥር ወደሌላቸው መንደሮች እወጣለሁ፤ ያለ ሥጋት በሰላም ወደሚኖሩ፥ ሁሉም ሳይፈሩ ያለ ቅጥር፥ ያለ መወርወሪያና ያለ በር ወደሚቀመጡ እሄዳለሁ፤ 12ምርኮን ልትማርክ፥ ብዝበዛን ልትበዘብዝ፤ ባድማም በነበሩ አሁንም ሰዎች በሚኖሩባቸው ስፍራዎች ላይ፥ ከአሕዛብም በተሰበሰበ፥ ከብትና ዕቃንም ባገኘ፥ በምድርም መካከል በተቀመጠ ሕዝብ ላይ እጅህን ትዘረጋ ዘንድ። 13ሳባ፥ ድዳን፥ የተርሴስ ነጋዴዎች፥ መንገዶችዋም ሁሉ እንዲህ ይሉሃል፦ ምርኮን ትማርክ ዘንድ መጥተሃልን? ብዝበዛንስ ትበዘብዝ ዘንድ ብርንና ወርቅንስ ትወስድ ዘንድ ከብትንና ዕቃንስ ትወስድ ዘንድ እጅግስ ብዙ ምርኮ ትማርክ ዘንድ ወገንህን ሰብስበሃልን?
14ስለዚህ የሰው ልጅ ሆይ፥ ትንቢት ተናገር፥ ጎግንም እንዲህ በለው፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ሕዝቤ እስራኤል በሰላም በተቀመጠ ጊዜ በዚያ ቀን አንተ አታውቀውምን?#38፥14 አንዳንድ ትርጉሞች “ራስህን ታስነሣለህ” ይላሉ። 15በስተ ሰሜን ርቆ ከሚገኘው ስፍራህ አንተ፥ ከአንተም ጋር ሁሉም በፈረሶች ላይ የተቀመጡ ብዙ ሕዝብ፥ ታላቅ ጉባኤና ብርቱ ሠራዊት ጋር ሆነህ ትመጣለህ። 16ምድርን እንደሚሸፍን ደመና በሕዝቤ በእስራኤል ላይ ትወጣለህ። ጎግ ሆይ፥ በአንተ በኩል ቅድስናዬን በፊታቸው በምገልጥበት ጊዜ፥ አሕዛብ እንዲያውቁኝ፥ በኋለኛው ዘመን በምድሬ ላይ አመጣሃለሁ።
ፍርድ በጎግ ላይ
17ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በእነርሱ ላይ እንደማመጣህ፥ ለብዙ ዓመት በተነበዩ በአገልጋዮቼ በእስራኤል ነቢያት እጅ በቀደመው ዘመን ስለ እርሱ የተናገርሁ አንተ ነህን? 18በዚያም ቀን ጎግ በእስራኤል ምድር ላይ በመጣ ጊዜ፥ ቁጣዬ ከፊቴ ይወጣል፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 19በቅንዓቴና በቁጣዬ እሳት ተናግሬአለሁ፦ በዚያ ቀን በእስራኤል ምድር ጽኑ መናወጥ ይሆናል፤ 20የባሕር ዓሣዎች፥ የሰማይ ወፎች፥ የምድር አራዊት፥ በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱ ተንቀሳቃሾች ሁሉ፥ በምድር ላይ የሚኖሩ ሰዎች ሁሉ በፊቴ ይንቀጠቀጣሉ፥ ተራሮች ይገለባበጣሉ፥ ገደሎች ይወድቃሉ፥ ቅጥርም ሁሉ ወደ ምድር ይወድቃል። 21በተራሮቼ ሁሉ ላይ ሰይፍን እጠራለሁ፥ የሰውም ሁሉ ሰይፍ በወንድሙ ላይ ይሆናል፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 22በቸነፈርና በደም እፈርድበታለሁ፤ ዶፍና የበረዶ ድንጋይ፥ እሳትና ዲን በእርሱና በወታደሮቹ ከእርሱም ጋር ባሉት ብዙ ሕዝቦች ላይ አዘንባለሁ። 23ታላቅ እሆናለሁ፥ እቀደሳለሁም፥ በብዙ አሕዛብ ዐይን የታወቅሁ እሆናለሁ፥ እኔ ጌታ እንደሆንሁ ያውቃሉ።
Currently Selected:
ትንቢተ ሕዝቅኤል 38: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ