ትንቢተ ሕዝቅኤል 41
41
1ወደ መቅደሱም አገባኝ፥ የድንኳኑን አዕማድ ወርድ በዚህ ወገን ስድስት ክንድ በዚያም ወገን ስድስት ክንድ አድርጎ ለካ። 2የመግቢያው ወርድ ዐሥር ክንድ ነበረ፥ የመግቢያው መቃኖች በዚህ ወገን አምስት ክንድ በዚያ ወገን ደግሞ አምስት ክንድ ነበሩ፤ ርዝመቱን አርባ ክንድ ወርዱን ደግሞ ሀያ ክንድ አድርጎ ለካ።
3ወደ ውስጥም ገብቶ የመግቢያውን ዓምድ ወርድ ሁለት ክንድ፥ የመግቢያውም ወርድ ስድስት ክንድ ነበረ፥ የመግቢያውም ግንብ ወርድ ሰባት ክንድ ነበረ። 4በመቅደሱ ፊት ያለውን ርዝመቱን ሀያ ክንድ ወርዱንም ሀያ ክንድ አድርጎ ለካና፦ “ይህ ቅድስተ ቅዱሳን ነው” አለኝ።
5የቤቱን ግንብ ስድስት ክንድ፥ በቤቱ ዙሪያ ሁሉ ያሉትን የጓዳዎቹን ሁሉ ወርድ አራት ክንድ አድርጎ ለካ። 6ጓዳዎቹም አንዱ ከአንዱ በላይ ሆነው የተሠሩ በሦስት ደርብ ነበሩ፥ በእያንዳንዱም ደርብ ላይ ሠላሳ ጓዳዎች ነበሩ። በቤቱ ግንብ ውስጥ የተደገፉ ስላልነበሩ፥ ቤቱ በዙሪያው ላሉት ጓዳዎች ያለው ግንብ ውስጥ እንዲደገፉ ግንቡ ውስጥ ገቡ። 7በቤቱም ዙሪያ ባለ ግንብ ውስጥ በነበሩት አረፍቶች ምክንያት ላይኞቹ ጓዳዎች ከታችኞቹ ጓዳዎች ይበልጡ ነበር፤ ከታችኛውም ደርብ ወደ መካከለኛው ከመካከለኛውም ደርብ ወደ ላይኛው የሚወጣበት ደረጃ ነበረ። 8ቤቱም ከፍ ያለ ወለል በዙሪያው እንዳለው አየሁ፤ የጓዳዎቹም መሠረት ቁመቱ ሙሉ ዘንግ የሚያህል ስድስት ትልቅ ክንድ ነበረ። 9የጓዳዎቹም የውጭው ግንብ ውፍረት አምስት ክንድ ነበረ፤ በቤቱ ጓዳዎች አጠገብ የቀረ ባዶ ስፍራ ነበረ። 10በቤቱም ዙሪያ ወርዱ ሀያ ክንድ የሆነ በጓዳዎቹ መካከል ባዶ ስፍራ ነበረ። 11የጓዳዎቹም መግቢያ በባዶው ስፍራ አንዱ በሰሜን በኩል አንዱም በደቡብ በኩል ነበረ፤ የባዶውም ስፍራ ወርድ ዙሪያው አምስት ክንድ ነበረ።
12በባሕር መንገድ#41፥12 አንዳንድ ትርጉሞች “ምዕራብ” ይላሉ። በኩል በተለየው ስፍራ አንጻር የነበረው ሕንጻ ስፋቱ ሰባ ክንድ ነበረ። የሕንጻው ግንብ ዙሪያ ውፍረቱ አምስት ክንድ ርዝመቱ ደግሞ ዘጠና ክንድ ነበረ።
13ቤቱንም ለካው፥ ርዝመቱ መቶ ክንድ ሆነ፥ የተለየው ስፍራ፥ ሕንጻውና ግንቡ አንድ መቶ ክንድ ሆነ። 14የቤቱና በምሥራቅ በኩል የነበረው የተለየው ስፍራ ስፋት አንድ መቶ ክንድ ሆነ። 15ወደ ኋላውም ባለው በተለየው ስፍራ አንጻር የነበረውን የሕንጻውን ርዝመት በዚህና በዚያ የነበሩትን መተላለፊያዎች ጨምሮ ለካ፥ አንድ መቶ ክንድ ነበር። የቤተ መቅደሱ ውስጠኛው ክፍል፥ የአደባባዩ መተላለፊያዎች፥ 16የቤቱ መግቢያዎች፥ ጠባቦቹ መስኮቶች፥ በዙሪያቸው የነበሩ ሦስት መተላለፊያዎች፥ የቤቱ መግቢያ ዙሪያውን ከመሬት ጀምሮ እስከ መስኮቶቹ ድረስ በእንጨት ተለብጦ ነበር፤ መስኮቶቹም የተሸፈኑ ነበሩ፤ 17ከበሩ በላይ እስከ ውስጠኛው ቤት ድረስ፥ በዙሪያውም የነበረው ግንብ ሁሉ ውጭውም ውስጡም ተለካ። 18በኪሩቤልና በዘንባባ ዛፎች የተሠራ ነበር፤ በኪሩብና በኪሩብ መካከል የዘንባባ ዛፍ ነበረ፤ እያንዳንዱም ኪሩብ ሁለት ፊቶች ነበሩት።
19የሰው ፊት በአንድ ወገን ወዳለው የዘንባባ ዛፍ ይመለከት ነበር፥ የአንበሳ ፊት ደግሞ በሌላው ወገን ወዳለው የዘንባባ ዛፍ ይመለከት ነበር፤ በቤቱ ሁሉ ዙሪያ እንደዚህ ተቀርጾ ነበር።
20ከመሬት አንሥቶ እስከ መግቢያው ድረስ ኪሩቤልና የዘንባባ ዛፎች ተቀርጸው ነበር። የመቅደሱም ግንብ እንደዚህ ነበረ።
21የመቅደሱ መቃኖችም አራት ማዕዘን ነበሩ፥ የተቀደሰው ሥፍራም የፊት ለፊት ገፅታው እንዲሁ ነበረ። 22ከእንጨት የተሠራው መሠዊያ ቁመቱ ሦስት ክንድ ርዝመቱ ሁለት ክንድ ነበር፥ ማዕዘኖቹ፥ እግሩና#41፥22 ዕብራይስጡ “ቁመቱ” ይላል። ግድግዳው ከእንጨት የተሠሩ ነበሩ፤ እርሱም፦ “ይህ በጌታ ፊት ያለ ገበታ ነው” አለኝ። 23መቅደሱና የተቀደሰው ስፍራ ሁለት በሮች ነበሩአቸው። 24እያንዳንዱ በር ሁለት ተዘዋዋሪ#41፥24 ወደፊትም ወደ ኋላም የሚከፈት። ሳንቃዎች ነበሩት፤ አንዱ በር ሁለት ሌላውም በር ሁለት ሳንቃዎች ነበሩት። 25በእነርሱም ላይ፥ በመቅደሱ በሮች ላይ በግንቡ ላይ እንደተቀረጸው ዓይነት ኪሩቤልና የዘንባባ ዛፎች ተቀርጸው ነበር፤ በውጭ ባለው መተላለፊያ ፊት ወፍራም እንጨት ነበረ። 26በመተላለፊያው በዚህና በዚያ ወገን ጠባብ መስኮቶችና የተቀረጹ የዘንባባ ዛፎች ነበሩበት፤ የመቅደሱም ጓዳዎች ወፍራም ነበሩ።
Currently Selected:
ትንቢተ ሕዝቅኤል 41: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ